Sunday, 31 January 2016

በሰሜን ጎንደር የወያኔ አፈና ቀጥሏል

ዛሬም በሰሜን ጎንደር የወያኔ አፈና ቀጥሏል ‪#‎AmharaProtests‬
‪#‎ETHIOPIA‬ | ህወሃት መራሹ የወያኔ ቡድን በሰሜን ጎንደር ሽንፋ እና አካባቢው ላይ የሚገኙ በህብረተሰቡ ተሰሚነት ያላቸውን የአማራና ቅማንት ማህበረሰብ አካል የሆኑ ሰዎችን እያፈነ ወደ ማጎሪያ ቤቶቹ ማጋዝ ቀጥሏል፡፡
ታሳሪዎቹ ለዕስራት የተጋለጡበት ምክንያት የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ከለላውን አንቀበልም ልንዋጋው ይገባል በማለታቸው እና በተጨማሪ አማራና ቅማንት ማህበረሰቦች ላይ እየሰራ የሚገኘውን የወያኔ ሴራ ለህብረተሰቡ እያጋለጡ በመሆኑ እንደሆነ ከቦታው የመረጃው ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡
ከታፈኑት ሰዎች መካከል
-መ/አለቃ ደጀኔ ወርቁ
-አቶ አታላይ ደምሴ
-አቶ ጋሹ ጌጡ
-አቶ ነጋ አቤ፥አቶ አስቻለው እና ሌሎች በርካቶች ይገኙበታል፡፡
©

Wednesday, 20 January 2016

አቶ ኦባንግ የኢህአዴግ ደጋፊ ስደተኞችን አስጠነቀቁ

 ኦባንግ የኢህአዴግ ደጋፊ ስደተኞችን አስጠነቀቁ “በአስመሳይ ስደተኞች ላይ በቂ መረጃ አለ” “ክፉን በክፉ መመከት ባያስደስትም ወቅቱ ያስገድደናል” ሲሉ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ በተለይ ለጎልጉል ተናገሩ። አገዛዙን ሸሽተው በተለያዩ አገራት ከለላ አግኝተው በስደት የሚኖሩም ሆኑ ጉዳያቸው እየታየ ያሉ ወገኖች አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ህግ አውጪዎች፣ የጀርመን የኢሚግሬሽን ሃላፊዎችና ከፍተኛ የፖለቲካ ሰዎች፣ ከኖርዌይ የኢሚግሬሽን ጉዳይ ሃላፊዎችና ተዛማጅ ሃላፊነት ካላቸው የህግ ክፍሎች፣ በካናዳ በተለያዩ ደረጃ ካሉ ባለስልጣናትና ወትዋቾች (አክቲቪስቶች)፣ በስዊድን አንዲሁም በእንግሊዝ በተመሳሳይ ግንኙነት ፈጥረው እየሰሩ መሆኑንን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “አገራቱ የስደት ፈቃድ ካገኙ በኋላ ለስደት ዳረገን ከሚሉት መንግሥት ጋር በቅርብ እየሰሩ ስላሉ አስመሳይ ስደተኞች አስገራሚ መረጃዎች መሰብሰባቸውን አውቃለሁ” ብለዋል።
አቶ መለስ በሞቱ በወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በካናዳ ቫንኮቨር 27 አንድ አይነት ቋንቋ ብቻ የሚናገሩ ወጣቶች ጥገኛነት መጠየቃቸውን ጉዳዩን በጥብቅ እየመረመሩት ካሉ ክፍሎች ማረጋገጣቸውንና የምርመራውን ውጤት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ ኦባንግ፣ “ወጣቶቹ ካናዳ የገቡት ለእያንዳንዳቸው 75 ሺህ ዶላር በማውጣት ነው። ይህን ገንዘብ ማን ሰጣቸው? እንዴት አገኙት? እንዴት ከአንድ አካባቢ (ክልል) ብቻ ሊሆኑ ቻሉ? የሚሉት ጉዳዮች ምርመራውን በያዙት ወገኖች ላይ ግራሞት የፈጠረ ትልቅ ጉዳይ ነው” በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት ከገንዘብ ማሸሽ ጋር በማያያዝ አመላክተዋል። ለምሳሌ አንድ ጉዳይ አነሱ እንጂ በመላው ካናዳ በተመሳሳይ የምርመራ ስራ እየተሰራ መሆኑንን ተናግረዋል።
የካናዳው አንድ ማሳያ ሲሆን በአሜሪካ ግዙፍ ቪላዎችን እየገዙ ያሉት ክፍሎች ጉዳይ ከገንዘብ ማሸሽ ጋር ተያይዞ እየተመረመረ እንደሆነ አቶ ኦባንግ አስረድተዋል። ጥገኝነት ካገኙ በኋላ “ሊገለን ሲል አመለጥነው” ያሉትን ኢህአዴግን የሚደግፉ ክፍሎች ላይም ለሚመለከታቸው ባለስልጣናትና ተቋማት ከሚቀርበው መረጃ በተጨማሪ ከፍትህ ወዳድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር ድርጅታቸው በጥምረት እየሰራ መሆኑን አቶ ኦባንግ አልሸሸጉም፡፡
በጀርመን ኑረንበርግ በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰሩ ባለስልጣናት በተመሳሳይ የምርመራ ስራ እያከናወኑ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ኦባንግ፣ በግል በጉዳዩ ዙሪያ መነጋገራቸውን አስታውቀዋል። የጥገኝነት ፈቃድ ካገኙ በኋላ ዲያስፖራውን በመከታተልና አገር ቤት የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ለችግር እንዲዳረጉ የሚያደርጉትን ክፍሎች ማንነት ነቅሰው እንደሚያውቋቸው ባለሥልጣናቱ በግንኙነታቸው ወቅት እንዳረጋገጡላቸው አመልክተዋል።
“ኢህአዴግ ለጊዜው የጠመንጃ ሃይል አለው። የገንዘብ አቅም አለው። ወዳጆችም አሉት። እኛ ደግሞ በየአቅጣጫው ፍትህ ወዳድ አጋሮች አሉን። ከነሱ ጋር እየሰራን ነው” በማለት አስረግጠው የተናገሩት ኦባንግ በማንኛውም መስፈርት ስደት ላይ ያሉ ወገኖችን መከታተልና መሰለል ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
“አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ስዊድንና ጀርመን አገር ባለስልጣናቱ ከበቂ በላይ መረጃ አግኝተዋል። እኛም እየሰራንበት ያለ ተከታታይ ስራ አለ። በየአቅጣጫው የሚደረገው ትግል በቅርቡ ፍሬው መታየት ይጀምራል” የሚሉት ኦባንግ ርምጃው መወሰድ ሲጀምር ከስድስት እስከ አስራ ሁለት ዓመት እስር እንደሚያስከትል፣ ከዚያም የከፋ አደጋ እንዳለው ጠቁመዋል።
በትምህርትና በተለያዩ ስልጠናዎች ወደ ተለያዩ ዓለማት የሚሰማሩ የአገዛዙ አገልጋዮችም ቢሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው የሚያሳስቡት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር “አገዛዙ መድቧቸው በየኤምባሲው ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች፣ የስለላ ሰዎች፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት ምስላቸውንና ማንነታቸውን ባደባባይ አይገልጹም። በኤምባሲዎች ድረ ገጽ ላይ እንኳ ስለማንነታቸው በቂ መረጃ ለመስጠት ድፍረት የላቸውም። የስርዓቱ ባህሪና የወንጀለኛነቱ መጠን ራሳቸውን እንዲገልጹ አይፈቅድላቸውም” በማለት በተራ መደለያና ጥቅማ ጥቅም ደረታቸውን እየሰጡ ያሉ ወገኖች አካሄዳቸውን በመመርመርና የሚያስከብራቸውን ተግባር እንዲፈጽሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
“ምክር በመለገስ ሰፊ ጊዜ የወሰድነው ክፉን በክፉ የመመለስ እምነት፣ ክፉ እንድናደርግ የሚገፋን ድርጅታዊ አቋም ስለሌለንና የሚጠሉንን ጭምር ነጻ የሚያወጣ ግዙፍ ራዕይ ስላለን ነው” የሚል ጥልቅ አስተያየት የሰነዘሩት አቶ ኦባንግ፣ በአገራቸው መኖር ያልቻሉ ወገኖች ተሰደውም ሰላም ሲያጡ መመልከት ግን የማይቻልበት ደረጃ መድረሱን አመልክተዋል። ከዚህም በተጨማሪ እሳቸው በግል፣ ድርጅታቸው በመርህ የሚታገሉለት የሰዎች መብት መከበር ብሩህ አጀንዳ በዝምታ እንዲቀመጡ እንደማይፈቅድላቸው ተናግረዋል።
ከኖርዌይ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ጋር በተገናኙባቸው ወቅቶች ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ በግልጽ እንደነገሯቸው ያመለከቱት ኦባንግ ሜቶ፣ አሁን ስሙንና ዝርዝር ጉዳዩን ለመናገር ፈቃደኛ ካልሆኑት ክፍል ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑንን ጠቁመዋል። አኢጋን ያቋቋመው የግልጽነትና የተጠያቂነት ግብረ ሃይል አንዱና ትልቁ ስራው እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን መርምሮና አጣርቶ ለሚመለከታቸው በማቅረብ ፍትህን መጠየቅ መሆኑንን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “ዝርዝሩን መናገር ቢከብድም ብዙ ስራ እየሰራንበት ያለው የስደተኞች ጉዳይ የሌሎችንም ተሳትፎና ትብብር ይጠይቃል” ብለዋል።
“በስሜት መታገል አያዋጣም” የሚል የትግል ማስተካከያ ሃሳብ ፈንጠቅ ያደረጉት አቶ ኦባንግ የስደት ማመልከቻቸው ተቀባይነት አግኝቶ የመኖሪያ ፈቃድ ካገኙ በኋላ አገር ቤት በመመላለስ፣ ህግ በመተላለፍ ለአገዛዙ የሚሰሩ በሙሉ “ብልጥና አዋቂ ነን፣ ባለጊዜዎች ነን” በሚል አስተሳሰብ የሚንቀሰቀሱ አንደማያዋጣቸው ሲያሳስቡ “ለእንደዚህ አይነቶች ሁሉም ዓይነት መንገድ አይሰራላቸውም። ግለሰቦችንና ባለስልጣናትን ሳይሆን አሰራርን በማጭበርበር ይጠየቃሉ። አገራቱ እንደ ኢትዮጵያ ሳይሆን ስራ ላይ የሚውል ህግ አላቸውና ይተገብሩባቸዋል። አሰራራቸው ሲጭበረበር ዝም የማይሉት ለማንም ሲሉ ሳይሆን ለራሳቸው ሲሉ ነው። አሰራር / ሲስተም/ ሲበረዝ የሚያስከትለውን አደጋ ስለሚረዱ የሚታገሱ ካልሆነ በቀር በዝምታ አያልፉም። በኖርዌይም ሊሆን የታሰበው ይህ ነው። አሁንም ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እቸገራለሁ” በማለት ነው። አቶ መለስ ህይወታቸው ባለፈ ወቅት በስደት ካምፕ የሚኖሩ ጭምር ለቅሶ መቀመጣቸው በኖርዌይ ሚዲያዎች አስገራሚ ተብሎ መዘገቡ፣ በህዝቡና በፖለቲከኞች ዘንድ መነጋገሪያ አጀንዳ እንደነበር አይዘነጋም።
በርካታ አሳዛኝና ህሊናን የሚፈታተኑ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ያወሱት ኦባንግ ሜቶ፣ ህጻናትን በጉዲፈቻ ስም በመቸብቸብ፣ ሴት እህቶቻችንን አረብ አገራት ያለ ዋስትና በመላክ ከፍተኛ ገበያ እየሰሩ ያሉት የህወሃት ሰዎች እንደሆኑ በበርካታ ማስረጃዎች መረጋገጡን ያስታውሳሉ። አያይዘውም አገራቸውን ለቀው ለስደት የሚወጡትን ወደ ኬኒያ፣ ታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካ ብሎም በጅቡቲና በሶማሌ በኩል ገንዘብ እያስከፈሉ የሚያሻግሩት አሁንም እነሱ ናቸው ሲሉ አስቀድመው ስለ ጠየቁት ትብብር ማሳሰቢያቸውን ያጠናክራሉ።
“በማስተዋል እንስራ” የሚሉት ኦባንግ በየአቅጣጫው መረጃ ላይ የተኙና፣ በምን አገባኝ ስሜት ዝምታን የመረጡ ወገኖች ያላቸውን መረጃ በመስጠት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራ ያለውን ስራ እንዲያግዙ አሳስበዋል። ይህንን ማድረግ አቶ ኦባንግንና እርሳቸው የሚመሩትን ድርጅት መርዳት ሳይሆን ራስንና አገርን መርዳት እንደሆነም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ከተቋቋመ 135ዓመታትን ያስቆጠረው የአሜሪካ ሕግ ባለሙያዎች ማኅበር (ABA) እየተባለ በሚጠራውና 400 ሺህ በላይ አባላት ባሉት የህግ ባለሙያዎች ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት ንግግር እንዲያደርጉ በተጋበዙበት ወቅት አቶ ኦባንግ ሜቶ በርካታ ጉዳዮችን በማንሳት ድጋፍ ጠይቀው አዎንታዊ ምላሽ እንዳገኙ ጠቅሰዋል፡፡ በርካታ የህግ ባለሙያዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ ኢህአዴግ ህግን ከለላ በማድረግ በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ወንጀል፣ ለእንደዚህ ዓይነት ተግባሩ ማስፈጸሚያም የጸረ ሽብርተኝነትን፣ የመያዶችን፣ ወዘተ ህጎች በማውጣት ዜጎችን ለእስር፣ ለስደት፣ ለስቃይ መዳረጉን፣ የፍትህ አካላቱን ህግን በሚያከብሩና ፍትህ በሚያስፈጽሙ ሳይሆን ራሱ በመሠረተው ተቋም እያመረተ ለፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረገ መሆኑን፣ ከዚህ አልፎ ደግሞ በስደተኛነት ስም ደጋፊዎቹን ወደ ውጪ በመላክ በሃሰት የኢህአዴግ ሰለባ በማስመሰል በየምዕራቡ ዓለም የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ በማስደረግ መልሶ ስደተኛውን እዲሰልሉና ለሥርዓቱ እንዲሰሩ እያደረገ መሆኑን፣ ወዘተ በስፋት አብራርተዋል፡፡ የባለሙያዎቹ ማኅበር ጉዳዩን በጥልቀት እንደሚያየውና ያለውን ከፍተኛ የሰው ኃይል በመጠቀም ከአኢጋን ጋር እንደሚሰራ ከሌሎች ማኀበራት ጋር በመሆንም በተለይ በምዕራቡ ዓለም የተሰገሰጉትን አስመሳይ ስደተኞች ወደ ፍትህ የማምጣቱ ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ለአቶ ኦባንግና ለድርጅታቸው አረጋግጠዋል፡፡

Tuesday, 19 January 2016

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ተቋርጠው የነበሩት ከ80 በላይ የሚሆኑ ክሶች እንደገና እንዲታዩ ተወሰነባቸው

ኢሳት (ጥር 09 ፥ 2008)
ከመንግስት ጋር ያደረጉት ስምምነት ተከትሎ በቅርቡ ወደሃገር የተመለሱትና ከቀናት በፊት ለእስር የተዳረጉት የአክሰስ ሪል ስቴት መስራች የተቋረጡባቸው ከ 80 በላይ ክሶች እንደገና እንዲታዩ ተወሰነ።
የኩባንያው መስራችና አመራር አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ወደሃገር ከተመለሱ በኋላ ሊተገብሩ ቃል የገቡትን ስራ ባለማከናወናቸው ምክንያት ክሳቸው እንዲቀጥል መደረጉን የፍትህ ሚኒስቴር ገልጿል።
ከመንግስት ጋር ድርድር አድርገው ባለፈው አመት ወደሃገር ቤት የተመለሱት የአክሰስ ሪል ስቴት መስራች፣ ወደሃገር ሲመጡም ያለመታሰር ዋስትና አልተሰጣቸውም ነበር ሲሉ የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ መግለጻቸው ከሃገር ቤት የተገነው መረጃ አመልክቷል።
የገቡትን ቃል መፈጸም አልቻሉም የተባሉ አቶ ኤርሚያስ ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር መዋላቸው የሚስታወስ ሲሆን፣ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ እና የተቋረጡ ከ80 በላይ ክሶችም እንደገና የሚታዩ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
አክሰስ ሪል ስቴስ ከስድስት አመት በፊት ከሁለት ሺ በላይ ከሚሆኑ ደንበኞች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ወደስራ ቢገባም ለደንበኞቹ መኖሪያ ቤትን አላስረከበም በሚል ብውዝግብ ውስጥ መቆየቱ ይታወቃል። አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በበኩላቸው ቤቶቹን ሰርቶ ለማስረከብ የገጠማቸው መሰናክልም መግለጻቸው ይታወሳል።


በሆሳዕና ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት ማመላለሻ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ


ኢሳት (ጥር 09 ፥ 2008)
በሆሳዕና ከተማ ከመንጃ ፈቃድ ቅጣት እና አስተዳደር ብልሹነት ጋር በተያያዘ የህዝብ የትራስፖርት ማመላለሻ አገልግሎት ለሁለት ቀን ተቋርጦ መዋሉት ዛሬ ሰኞ ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመለከተ።
አንድ ሆሳዕና ወደሌላ ወረዳ ወይም ከወደ ዋና ዋና ከተሞች የሚያጓጉዙ የትራንስፖት መገናኛ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ህዝቡ ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ውስጥ ላይ እንደሆነ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ በሆሳዕና የሚኖሩ ሰው ለኢሳት በስልክ ተናግረዋል።
“መንግስት ያወጣው አዲሱ ህግ አንድ ሹፌር 3 ጊዜ አንድ አንድ ሺ ብር ከተቀጣ መንጃ ፈቃዱን ይነጠቃል የሚለው ነው አድማውን ያስነሳው” ያሉት አንድ አስተያየት ሰጪ፣ አድማውን ተላልፎ ከቡታጅራ ሆሳዕና ይጓዝ የነበረ አንድ ሃይሩፍ የትራስፖርት ተሽከርካሪም ወራቤ ላይ በትራንስፖርት አገልግሎት ሰራተኞች እና በህዝቡ እንደወደመ ተነግሯል።
አዲሱን የመንግስት መመሪያ በመቃወም የሆሳዕና፣ ጉራጌ  እና ወላይታ ዞኖች ባሉት ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎች በአድማው መሳተፋቸው ታውቋል።
የአካባቢው ህብረተሰብም ታምቀው የቆዩ የመልካም አስተደደር ችግሮችን እየገለጸ ያለበት አጋጣሚ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት አስታውቀዋል።
ትናንት እሁድና ዛሬ ሰኞ ከባጃጅ ጀምሮ ሁሉም የትራስፖርት አገልግሎቶች በመቋረጣቸው፣ ከከተማዋ የሚወጣም ሆነ የሚገባ ምንም አይነት የትራስፖርት አገልግሎት ተሽከርካሪ እንደሌለ ታውቋል።
ከአድማው ጋር በተያያዘ በሃድያ ዞን ማረሚያ ቤት 4 ሰዎች በመንግስት ሃይሎች መታሰራቸው ተነግሯል።
የመንግስት አዲሱን አሰራር በመቃወም ነገ ማክሰኞ በሆሳዕና ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ እንደተጠራ በአካባቢው የሚኖሩ ሰው ለኢሳት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ በህጻናት ላይ ከጦርነት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ጉዳት እያደረሰ ነው ተባለ


ኢሳት (ጥር 09 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የድርቅ አደጋ በህጻናት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ጦርነት በሶሪያ ህጻናት ላይ እያደረሰ ካለው አደጋ ጋር ተመሳሳይ እየሆነ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቁ።
ይኸው በስድስት ክልሎች ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋ ከ 400ሺ በላይ በሚሆኑ ህጻናት ላይ ክፉኛ የአካልና የጤና ችግርን እያስከተለ እንደሚገኝ ድርጅቱ ገልጿል።
ድርቁ በህጻናት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ጦርነት በሶሪያ ህጻናት ላይ እያደረሰ ካለው ጉዳት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናቱን ህይወት ለመታደግ አፋጣኝ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
በኢትዮጵያ ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋና በሶሪያ ቀጥሎ የሚገኘው ጦርነት በአለማችን ግንባር ቀደም የሰብዓዊ እርዳታን የሚፈልጉ አስቸኳይ ችግሮች ሆነው ተገኝተዋል ሲሉ የህጻናት አድን ድርጅት ተወካይ የሆኑት ካሮሊን ማይልስ ገልጸዋል።
ለዚሁ አፋጣኝ የነብስ አድን ስራም የህጻናት አድን ድርጅት ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚፈልግ ተወካዩ ይፋ ማድረጋቸውን ኒውስ 24 የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
ድርቁ ዱዳትን እያደረሰ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ዘገባን ያቀረበው አልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በበኩሉ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ለምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች በቂ እርዳታን እያገኙ እንዳልሆነ መግለጻቸውን አስነብቧል።
በድርቁ ሳቢያ ክፉኛ ጉዳት የደረሰባቸው እና የአስር ልጆች አባት የሆኑት ሞሃመድ ዱባሃላ ከነበራቸው 53 ላሞች መካከል አምስቱ ብቻ መትረፋቸውን ለቴለቪዥን ጣቢያው አስረድተዋል።
በተለይ ህጻናት ላይ እያደረሰ ባለው ጉዳት ሃዘን እንደተሰማቸው የገለጹት አርብቶ አደሩ ከመንግስት እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣዮቹ ሁለት ወራት በድርቁ ሳቢያ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልና የድርቁ ጉዳትም እየከፋ እንደሚሄድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳስቧል።

ኢትዮጵያ አልፋሽጋ የሚባለው ግዛት የሱዳን መሆኑን እንደምትቀበልና ለማስረክብ መቁረጧ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ

“የሱዳን መሬት በኢትዮጵያ መያዙን የኢትዮጵያ መንግስት አምኖአል” ሲሉ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጹ
ጥር ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዱር ለአልጀዚራ እንደተናገሩት “ኢትዮጵያ አልፋሽጋ የሚባለው ግዛት የሱዳን መሆኑን እንደምትቀበልና ለማስረክብ መቁረጧን” ተናገሩ።
ለሱዳን ይሰጣል የተባለው መሬት 250 ካሬ ኪሎሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ ለም የሆነ መሬትና በርካታ የውሃ ተፋሰሶች ያሉት ነው።
...
የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያ አርሶአደሮች መሬቱን ሰጥቷቸው ሲያርሱት ነበር ያሉት ባለስልጣኑ፣በዚህ አመት ውስጥ መሬቱን ኢትዮጵያ ለሱዳን ልታስረክብ መሆኑን ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ንግግር፣ አቶ ሃይልማርያም ደሳለኝ በቅርቡ የሰጡትን መግለጫ የሚያጠናክር ነው። አቶ ሃይለማርያም የኢትዮጵያ ባለሃብቶችና አርሶአደሮች ወደ ሱዳን ገብተው እያረሱ መሆኑንና የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳንን መንግስት ለምኖ እስካሁን በቦታው ላይ እንዲቆዩ ማድረጉን ተናግረው ነበር።
የሱዳን መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰጡት መግለጫ ከኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስትር ጋር መመሳሰሉ የተጠቀሰው መሬት ለሱዳን እንደሚሰጥ ማረጋገጫ ነው። በድንበሩ አካባቢ ያሉ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች ግን መሬቱ የኢትዮጵያ መሆኑን ይናገራሉ።
የኢህአዴግ መንግስት መሬቱ የሱዳን መሆኑን አምኖ ከተቀበለ ቀሪው ነገር አለማቀፋዊ ህጋዊነትን ማላበስ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ ሁለቱም መንግስታት ተስማምተው ስምምነታቸው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከገለጡ፣ መሬቱን መልሶ ለማግኘት ጉዳዩን ውስብስብ ሊያደርገው ይችላል።
የመንግስት ቃለአቀባይ ጌታቸው ረዳ እና ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የድንበር ጉዳይን ለማየት የተቋቋመ ኮሚቴ እንደሌለ፣ መሬት ለመስጠት ምንም ዝግጅት እንደሌለ ሲገልጹ ቆይተዋል። ይሁን እንጅ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሪዎች ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። የኮሚቴው ሰብሳቢ አብደላ አል ሳድቅ ኮሚቴው ስራውን ያለምንም ችግር እያከናወነ መሆኑን ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ላለፉት ሁለት ወራት የደህንነት መስሪያ ቤት (ኢንሳ) መሬቱን የአየር ላይ ፎቶ ሲያነሳ ከርሟል። የአካባቢው ነዋሪዎች ለሚያነሱት ጥያቄ የደህንነት መስሪያ ቤቱ “የመሬቱ ልኬቱ የሚካሄደው ለልማት የሚውለውን መሬት ለመለየት ነው” የሚል መልስ ሲሰጥ ቆይቷል። የደህንነት መስሪያ ቤቱ መሬቱን የማስረከብ ሃላፊነት መውሰዱን ምንጮች ገልጸዋል።

Tuesday, 12 January 2016

የኖርዌይ ኤምባሲ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በማገርሸቱ ዜጎች የጥንቃቄ እርምጃን እንዲወስዱ አሳሰበ

ኢሳት (ጥር 3 ፥ 2008) መቀመጫውን በኢትዮጵያ ያደረገ የኖርዌይ ኤምባሲ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ዳግም በማገርሸቱ ምክንያት ዜጎች በክልሉ በሚያድርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ እርምጃን እንዲወስዱ አሳስቧል። የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በቅርበት የምትከታተለው ኖርዌይ እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ የጸጥታ ስጋት ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት በቅርቡ ለኤምባሲ ተወካዮች በሰጡት ማብራሪያ ተቃውሞው በቁጥጥር ስር ዉሏል ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል። ይሁንና በሁለቱ ወገኖች መካከል የተካሄደው ውይይት ተከትሎ ኖርዌይ ተቃውሞው አለመብረዱንና የጸጥታ ስጋት እየሆነ መምጣቱን በይፋ ስትገልጽ የመጀመሪያ ሃገር ሆናለች። መቀመጫቸውን በሃገሪቱ ያደረጉ የተለያዩ ሃገራት ተወካዮችና አለም አቀፍ ድርጅቶች በወቅታዊው የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ የተናጥል ምክክርን እያካሄዱ እንደሚገኝም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የአክሰስ ሪል ስቴትና የዘመን ባንክ መስራች አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ታሰሩ

ኢሳት (ጥር 3 ፥ 2008) የአክሰስ ሪል ስቴት እንዲሁም የዘመን ባንክ መስራች አቶ ኤርሚያስ አመልጋ መታሰራቸውን ከአዲስ አበባ የደረስን ዜና አመለከተ። በመንግስት ዋስትና ወደሃገር ቤት ከተመለሱ ወራት ብቻ ያስቆጠሩት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ ተመልሰው የታሰሩበት ዝርዝር ምክንያት ባይገለጽም፣ ከአክሰስ ሪል ስቴት ጋር የተያያዘ መሆኑን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ሃይላንድ ውሃን በማምረት ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ በመግባት በንግዱ አለም ታዋቂ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በየካቲት ወር 2005 ዓ ም ከመንግስት ጋር ባለመግባባት ከሃገር የወጡ ሲሆን፣ በመንግስት ተሰጣቸው በተባለ ዋስትና በየካቲት ወር 2007 ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። ለሁለት ዓመታት ያክል በዱባይ ቆይተው ወደኢትዮጵያ የተመለሱት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በነሃሴ ወር 2007 ከአክሰስ ቦርድ ሊቀመንበርነታቸው እንዲነሱ የተደረጉ ሲሆን፣ በርሳቸው ምትክ ወ/ሮ መብራት ወልደትንሳዔ የተባሉ ባለአክሲዮን መሾማቸው ታውቋል። በዋስትና ወደሃገር ቤት የተመለሱት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የተገባላቸውን በአደባባይ የተነገረው ቃል ታጥፎ ወደእስር ቤት የገቡበት ሁኔታ ግልጽ አልሆነም።
Ermias-Amelga

Tuesday, 5 January 2016

የአዳማ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች በአጋዚ ወታደሮች ግድያ፣ ድብደባና ወከባ ደረሰባቸው

ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2008)

በኦሮሚያ እየተካሄደ ያለውን የመሬት ዘረፋና የጅምላ ጭፍጨፋን  በመቃወም ላይ በነበሩ በአዳማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ተቃውሞውን ለማስቆም በተሰማሩ የጸጥታ ሃይላት መካከል ግጭት እንደተፈጠረ የአይን እማኞች ከስፍራው አስታወቁ።ሰኞ ጠዋት የተጀመረው ይህ ተቃውሞ፣ ተማሪዎቹ በአዳማ ዩንቨርስቲ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ በኦሮሚያ ክልልና በሌላው የኢትዮጵያ ክልሎች ላይ እየደረሰ ያለው ጭፍጨፋና፣ ወከባና፣  እንግልትን እንዲቆም ሲጠይቁ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።አመጹን ለማስቆም ቀደም ብሎ በአካባቢው የሰፈረው ብዛት ያለው የአጋዚ ክፍለጦር እንደተሰማራ የተገለጸ ሲሆን፣ ተማሪዎችም ከመሬት ወረራና ከሰብዓዊ መብት ጥሰት በተጨማሪ የአጋዚን በትምህርት ማዕከል መስፈር በጽኑ ተቃውመዋል።ተቃውሞ እየተደረገ በነበረበት ወቅት የአጋዚ ክፍለጦር አባላት ተማሪዎች ላይ ጥይት እንደተኮሱና፣ ተማሪዎች ደግሞ ራሳቸውን ለመከላከል ይሯሯጡ እንደነበር የአይን እማኞች ገልጸዋል። የአጋዚ ወታደሮች አስለቃሽ ጋዝ በዩንቨርስቲ ግቢ እንደተጠቀሙ እነዚሁ የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
በግጭቱም ወቅት አንድ ተማሪ እንደተገደለ ሲታወቅ፣ በጥይት የቆሰሉ ተማሪዎች ደግሞ በአምቡላን ወደሆስፒታል ተወስደዋል።  የአጋዚ ወታደሮች ብዛት ያላቸው ተማሪዎችን እየደበደቡ ጉድጓድ ውስጥ እንደወረወሯቸው የአይን እማኞች ለኢሳት አስረድተዋል።የፖሊስን ጥይት፣ አስለቃሽ ጋዝና፣ ዱላ ለማምለጥ ብዛት ያላቸው ተማሪዎች ከአዳማ ዩንቨርስቲ ጀርባ በሚገኘው ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ተጠልለው የነበረ ቢሆንም፣ የአጋዚ ሃይሎች ወደዚያ በመሄድ ተማሪዎችን እየደበደቡ እንዳስወጧቸው ታውቋል። በኋላም አብዛኞቹን ተማሪዎች ከቤተክርስቲያን አስወጥቶ በማሰለፍ ወደ ግቢ ይዘዋቸው ሄደዋል ተብሏል። የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎችም የፖሊስን ድርጊት ዝም ብሎ ከማየት ውጭ ምንም ነገር ማድረግ አለመቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪ የአጋዚ ክፍለጦር ወታደሮች የአውቶቡስ መነሐርያን በመዝጋት ተማሪዎች ወደቤተሰቦቻቸው እንዳይሄዱ እንዳደረጉ ታውቋል። አውቶቡስ ተራ የሚገባ ሰው መታወቂያ እያሳየ እንደነበርና፣ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ግን ወደግቢው እንዳይገቡ እንዳልተፈቀዳላቸው የአይን እማኞች ለኢሳት ተናግረዋል።ተማሪዎቹ ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ የገለጹ ቢሆንም፣ የአጋዚ ወታደሮች ግን ያለርህራሄ ተማሪዎች እየደበደቡ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።የኦሮሚያ ፖሊስ በአካባቢው ቢኖርም፣ ተማሪዎችን ይደበድቡና ያዋክቡ የነበሩት ግን የታጠቁ እና ለውጊያ ዝግጁ የሆኑ የመደበኛ ሰራዊት አባላት እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።
የማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ግጭት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የዩንቨርስቲ ግቢ በከባድ መሳሪያ ጭምር እየተጠበቀ እንደሆነ የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።ከማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በሃረማያ፣ አምቦ፣ ዲላ፣ እና በሁሉም በአገሪቱ ባሉት ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሁለት ወራት በተካሄደ ተቃውሞ፣  ከ125 በላይ የሚሆን የሰው የህይወትና ከፍተኛ ንብረት መውደሙ ይታወቃል። አሁንም በአብዛኛው የኦሮሚያ ክፍሎች ከፍተኛ ግጭቶት እየተከሰቱ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ ያለው ርሃብ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አሳወቀ

ታኀሳስ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የዓለም የምግብ ድርጅት በኢትዮጵያ ያለው የድርቅ ሁኔታ እየከፋ መምጣቱንና ዜጎች አፋጣኝ እርዳታ ካልተደረገላቸው በአገሪቱ የሚደርሰው ሰብዓዊ ቀውስ እጅግ አደገኛ መሆኑን በሪፖርቱ ገልጿል።

በኢትዮጵያ በተከሰተው የአየር መዛባት ኤሊኖ ምክንያት ወቅቱን ጠብቆ ዝናብ ባለመዝነቡ በቂ ምርት መሰብሰብ ያልተቻለ ሲሆን እንስሳትም በድርቁ ሰበብ ሞተዋል።
ቁጥራቸው ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን የዓለም የምግብ ድርጅት 7.6 ሚሊዮን የሚሆኑትን በ2016 ዓ.ም ለመርዳት መዘጋጀቱንና ባለፉት ስድስት ወራቶች ውስጥ ከ5% ያነሰ የምግብ አቅርቦት ግብዓቶችን ማድረሱን የድርጅቱ ቃል አቀባይ እስቴፋን ጁሪክ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ተከስተው ከነበሩት ሁሉ የከፋውን ቀውስ ያስከተለ መሆኑን የተባባሩት መንግስታት ድርጅት በሪፖርቱ ማሳሰቡን ዩኤን ኒውስ ዘግቧል።
በተጨማሪም በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይና አማራ ክልል፣ በምስራቅ ኦሮሚያና ሶማሊያ ድርቁ ባስከተለው ችግር ሕጻናት በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት ለሞት መጋለጣቸውንና በአገሪቱ ያለው የርሃብ ተጠቂዎች ቁጥር 20 ሚሊዮን እንደሚጠጋ የካቶሊክ የእርዳታ ድርጅትን ጠቅሶ አልጀዚራ ዘግቧል። ከየአካባቢው በተሰባሰቡ መረጃዎች መሰረት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እንዲሁም በትግራይ የዕርዳታ አሰጣጡ ስራ መቀነሱ፣ ተረጂዎች ባሉባቸው ወረዳዎችና ቀበሌዎች በቂ የዕርዳታ እህል እየቀረበ አለመሆኑ፣ የሚመጣውም ዕርዳታ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ለተረጂዎች እየተሰራጨ አለመሆኑ አሳሳቢ ሆኖአል፡፡

በኦሮምያ ዜጎች በህወሃት ንብረቶች ላይ የኢኮኖሚ ማእቀብ እየጣሉ ነው

ታኀሳስ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-

በኦሮምያ ህዘባዊ ተቃውሞው እንደቀጠለ ሲሆን፣ ዜጎች በህወሃት ኩባንያዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ነው። ትንናት በምስራቅ ሀረርጌ ቆቦ ከተማ የተጀመረው ተቃውሞ ወደ መሰላ ከተማም ተዛምቷል። የኢህአዴግ ወታደሮች በሚወስዱት ጭካኔ የተሞባለት እርምጃ እስካሁን 3 ሰዎች መገደላቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያመለክታል። የስርዓቱ ወታደሮች የሚወስዱት ጭካኔ የተሞላበት የሃይል እርምጃ ያሳሰባቸው የክልሉ ነዋሪዎች፣ የህወሃት ንብረት በሆነው ሰላም አውቶብስ ላለመሳፈር እንቅስቃሴ ጀምረዋል:፡ የክልሉ ወኪላችን እንዳለው ዜጎች በሰላም አውቶቡስ አንሳፈርም ማለታቸው ብቻ ሳይሆን፣ አውቶቡሱ በአካባቢው እንዳይንቀሳቀስ እየወሰዱት ያሉት እርምጃ ስጋት ላይ የጣለው ፣ ገዢው ፓርቲ፣ በእያንዳንዱ የሰላም ባስ ተሽከርካሪ ላይ ጠባቂ ወታደሮችን ለመመደብ ተገዷል።

ባለፉት 3 ቀናት በክልሉ የነበረው የሰላም አውቶቡስ እንቅስቃሴ የቀነሰ ሲሆን፣ ትናንት በአንዳንድ የኦሮምያ አካባቢዎች የተንቀሳቀሱ አውቶቡሶች በወታደሮች ታጅበው ታይተዋል። በኦሮምያ ክልል ውስጥ በሚሰሩ በሁሉም የሰላም አውቶቡሶች ውስጥ ጠባቂ ወታደሮች መመደባቸውን ዘጋቢያችን ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአጋዚ ወታደሮች በክልሉ ህዝብ ላይ የወሰዱት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ መከፋፈል መፍጠሩን፣ አንዳንድ የኦሮሞ ተወላጅ የሰራዊቱ አባላት እየገለጹ ነው። ከፍተኛ መፈራራትና ቅሬታ አለ የሚሉት ምንጮች፣ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች “የተወሰደው እርምጃ ተገቢ ነው” ብለው ሌላውን ሰራዊት ለማረጋጋት እየተሯሯጡ ነው። ቅሬታው የእሰፋ በመምጣቱ በመሃል አገር ውስጥ የሚገኙ ወታደሮችና አዛዥ መኮንኖች እርስ በርስ እንዲጠባበቁ እንዳደረጋቸው አክለው ገልጸዋል።
ገዢው ፓርቲ በሚወስደው እርምጃ የተጎዱ በርካታ ዜጎች ፎቶግራፎች በማህበራዊ የመገናኛ ብዙሃን እየተሰራጩ ነው። እስካሁን ደድረስ ባለው መረጃ ከ100 በላይ ሰዎች በወታደሮች ተገድለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ታስረዋል።

በኦሮሚያ ክልል ግድያው እና እስራቱ ቀጥሏል፥ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች እንዲተባበሩም ጥሪ ቀርቧል

ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2008)

የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት በአዲስ አበባ ዙሪያ ሊተገበር የተዘጋጀውን ማስተር ፕላን በመቃወም ሰላማዊ ተቃውሞ ያሰሙ ዜጎችን መግደሉን፣ መደብደቡንና፣ ማዋከቡን አጠናክሮ መቀጠሉ ታወቀ።በኦሮሚያ ስላለው ስለወቅታዊ ሁኔታ አጠቃላይ ሁኔታ ዝርዝር እንዲሰጡን የተጠየቁት ዶ/ር መረራ፣ በመንግስት ሃይሎች ዜጎችን የማሰሩ ሄደት አሁንም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ተናግረዋል። ባለፈው እሁድ በሃገረማሪያም ይኖር የነበረ አንድ የኦፌኮ አመራርና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመንግስት ሃይሎች ተይዘው እንደታሰሩ ዶ/ር መረራ ለኢሳት ገልጸዋል።
የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የተቃውሞው አስተባባሪዎች ናቸው ያላቸውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አመራር አባላት አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጀኔ ቱፋ እና የወጣቶች ጉዳይ ሃላፊ የነበሩት አቶ ጉርሜሳ አየነውን ማሰሩን መዘገባችን ይታወሳል። በቅርቡም የአቶ በቀለ ነጋአ በቁም እስር እንዲሆኑ እንደተደረገ ታውቋል። አቶ በቀለ ነጋአ በቁም እስር ላይ እያሉ ለሚዲያ ምንም አይነት መረጃ እንዳይሰጡና ወደ ቢሮ ወይም ወደ ፈለጉበት አካባቢ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ እገዳ እንደተጣለባቸው ለማወቅ ተችሏል።
እስካሁን ድረስ ከ4ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በማስተር ፕላን ሰበብ እንደታሰሩ ሲታወቅ፣ አሁንም በመላው ኦሮሚያ ተቃዋሚ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩትን ሁሉ እየታደኑ መታሰራቸው ተገልጿል። የታሰሩት የአመራር አባላትም አብዛኞቹ እስካሁን ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ በጸጥታ ሃይሎች ተከልክለዋል።
የኦሮሞ ኮንግሬስ አባላት ከመታሰራቸው ውጪ ምንም አይነት መረጃ ከመንግስትም ሆነ ከሌሎች አካላት ማግኘት እንዳልቻሉ ዶ/ር መረራ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
ዶ/ር መረራ “የኢትዮጵያ መንግስት የፖሊስ ወይም የህግ አካላት ያልሆኑ ከህግ ውጭ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች አሰማርቶ ባለበት ሁኔታ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ አቶ በቀለ ነጋአን ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ደህንነት ሲል መጫን አይፈልግም” ብለዋል።
የደህንነት አካላት በአቶ በቀለ ነጋአ ቤተሰብ ላይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ማስፈራርያ እንደሰጧቸው መዘገባችን ይታወሳል። አቶ በቀለ ነገአ በራሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ ወስነው መንቀሳቀስ ከፈለጉ መብታቸው እንደሆነም የደህንነት ሰዎች እንደነገሯቸው ለመገናኛ ብዙሃን ባሰራጩት ጹሁፍ አስታውቀው ነበር።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አባላት ቢታሰሩም ፓርቲው ስራውን አጠናክሮ መስራቱን እንደቀጠለ ለኢሳት የገለጹት ዶር መረራ፣ “መንግስት የተወሰኑ አባሎቻችንን ቢያስርብንም፣ አሁን በዋናነት መልሶ የማደራጀት ስራ እየሰራን ነው”  ብለዋል።
በአዲስ አበባ እስካሁን ድረስ ለምን ሰላማዊ ሰልፍ እንዳላደረጉ ለተጠየቁት ጥያቄ ዶር መረራ ሲመለሱ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ሲፈልግ ህግን፣ ካልፈለገ የራሱን ህግ የሚጠቀም  በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፍ ከልክሎናል ብለዋል። በመሆኑም ኢህአዴግ “አታደርጉም የሚል ውሳኔ ሲሰጥ ህገመንግስትን እየጣሰ፣ እኛ ግን ህግ ያልሆነውን የራሱን ህግ እንድናከብር የሚፈልግ ፓርቲ ነው” ብለዋል።
ሆኖም ዶ/ር መረራ ኢህአዴግ ፈቀደ አልፈቀደ ህዝቡ በየክፍለሃገሩ ለሰላማዊ ሰልፍ እየወጣ እንደሆነ አብራርተዋል።  ትግሉ አዲስ አበባ ሲደርስ ሰላማዊ ህዝቡ ሰልፍ መውጣቱ አይቀሬ መሆኑን ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
ዶር መረራ የኢትዮጵያ መንግስት የገባበት መንገድና ግትር አቋሙ እጅግ አደገኛ፣ ማንንም እንደማይጠቅም መሆኑን አስረድተው ወደ እርቅና ሰላም የሚያመጣ መንገድ መከተል እንደሚያስፈልግ መክረዋል። በመቀጠልም የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱ በጋራ እንዲታገል ዶ/ር መረራ ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ተሰባስበው ህዝቡን በመምራት ለሁላችን የምትሆን ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመመስረት የሚያስችል አቅጣጫ መቀየስ እንዳለባቸው ጥሪ አስተላልፈዋል።
በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተባብሶ መቀጠሉን መረጃዎች ያመለክታሉ። በትናንትናው ዕለት በአዳማ ላይ አንድ ሰው ተገሎ መገኘቱንና፣ ሰሜን ሸዋ አቦቴ አካባቢ ሌላ ሰው ተሰቅሎ እንደተገኘ ለኢሳት የደረሱ መረጃዎች ያለመክታሉ። በማስተር ፕላን ሰበብ የተነሳው ተቃውሞ በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች እንደገና አገርሽቷል። በምዕራብ ሸዋ በሃረር መስመር ጨለንቆ እና ቆቦ ላይ በትናንትናው ዕለት  የታሰሩት ይፈቱ የሚል ተቃውሞ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።

Friday, 1 January 2016

የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት ከማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ እየወሰደ ያለው የእስር እርምጃ አሳስቦኛል አለ

በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ያለው የእስር ዘመቻ ስጋት እንዳሳደረበት የአሜሪካ መንግስት በድጋሚ ገለጠ።

ተቃውሞውን ተከትሎም ለእስር የተዳረጉት ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱና በሃገሪቱም ሃሳብን በነጻነት የመግለጥ መብቱ እንዲከበር አሜሪካ አሳስባለች።
የአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል-አቀባይ የሆኑት ኔድ ፕራይስ ሃገራቸው ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞችንና ሌሎች ሰዎችም በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥያቄ ማቅረቧን ሃላፊው ዋቢ በማድረግ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
መንግስት ተግባራዊ አድርጎ የሚገኘውን የጸረ-ሽብር አዋጅንም የሰብዓዊ መብቶችን ለማፈን ማዋል እንደሌለበት ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
ከቀናት በፊት ተመሳሳይ ስጋቷን የገለጸችው አሜሪካ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ሁኔታ አሳስቧት እንደሚገኝም በድጋሚ አስታውቃለች።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት ሃገሪቱ በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ የሆነ አቋም እንድትከተልና እርምጃዎችን እንድትወስድ በማሳሰብ ላይ ናቸው።
በኢትዮጵያ እየታየ ነው የሚባለው ልማት ኢኮኖሚያዊ እድገት ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ፣ በሃገሪቱ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርና የሰብዓዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸው የአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ሚስተር ኔድ ፕራይስ አክለው አስታውቀዋል።
ለአንድ ወር ያህል ጊዜ በቀጠለው በዚሁ በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ፣ እስከአሁን ድረስ ከ100 በላይ የሚገመቱ ሰዎች እንደሞቱ የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡና መንግስት ጥያቄን በሚያነሱ ሰዎች ላይ የሚወስደውን የሃይል እርምጃ እንዲያቆም ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ተቃውሞውን ተከትሎ ከ4ሺ በላይ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሁለት ጋዜጠኞችም የዚሁ ሰለባ መሆናቸው ታውቋል።

በአፋርና ሶማሌ ክልል የምግብ እጥረት አሳሳቢ ነው ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ



ኢሳት (ታህሳስ 23 ፣ 2008) በደቡብ የአፋር አካባቢና በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን በድርቅ ምክንያት የተከሰተው የምግብ እጥረት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አርብ አስታወቀ። በነዚህ አካባቢዎች የአደጋው አሳሳቢነት በደረጃ ሁለትና ሶስት ውስጥ ተመድቦ ቢቆይም፣ ይኸው አሃዝ ወደ ደረጃ አራት ከፍ ማለቱን የምግብ እጥረቱ የከፋ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል። በእነዚሁ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ-አደሮች አፋጣኝ የምግብ አቅርቦት ካልተደረገላቸው ችግሩ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳስቧል። ለአስቸኳን የምግብ እጥረት የተጋለጡ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎችም በቂ እርዳታን እያገኙ እንዳልሆነ ተገልጿል። በቀጣዮቹ ሶስት ወራቶች ውስጥም ለተረጂዎች የሚያስፈልገው እርዳታ ወደሃገሪቱ መግባት ካልጀመረ የድርቁ አደጋ በስድስት ክልሎች ውስጥ ከፍተኛ ጉዳትን ሊያስከትል እንደሚችል ድርጅቱ አክሎ አስታውቋል። በአማራ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊያን ደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወደ 184 ወረዳዎች በደረጃ ሶስት ወስጥ ተመድበው የቅርብ ክትትል እየተደረገባቸው የሚገኝ ሲሆን፣ የበጋ ወቅቱ እየተጠናከረ በመሃሉም የድርቁ አደጋ እየተባባሰ ይሄዳል ተብሎ ተሰግቷል። ከ 10 ሚሊዮን በላይ ደርሶ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ፈላጊዎች ቁጥርም በቀጣዮቹ ጥቂት ወራቶች ውስጥ 15 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ተተንብዮአል። ለእነዚሁ ተረጂዎች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን የእርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውና የድርቁ አደጋ እስከቀጣዩ አመት መጋቢት ወር ድረስ የሚዘልቅ እንደሆነም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክቷል። በድርቁ አደጋ ከቀያቸው የሚሰደዱና ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ህጻናት ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።

ኢትዮጵያ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር በየአመቱ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እያጣች እንደሆነ አንድ አለም አቀፍ የፋይናንስ ደህንነት ተቋም ይፋ አደረገ



ኢሳት (ታህሳስ 23 ፣ 2008) በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር በየአመቱ ከፍተኛ ገንዘብ የምታወጣው ኢትዮጵያ ከህገ-ወጥ ንግድ ተቋማት ጋር በተያያዘ በየአመቱ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እያጣች እንደሆነ አንድ አለም አቀፍ የፋይናንስ ደህንነት ተቋም ይፋ አደረገ። እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2004-2013 26 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ያጣችው ኢትዮጵያ ከዚሁ ገንዘብ መካከል 19.7 ቢሊዮን ዶላር ከህገወጥ ንግድ ጋር የተያያዘ መሆኑን ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተለጀንስ አስታውቋል። ሃገሪቷ ከህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ጋር በተገናኘ እያጣች ያለችው ገንዘብ ከሃገሪቱ አመታዊ አጠቃላይ ምርት ውስጥ ከ5-10 በመቶ የሚሆነውን እንደሚሸፍንና መጠኑም ከአህጉሪቱ ሰፊ መሆኑን ተቋሙ ገልጿል። ኢትዮጵያ በተጨማሪ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ሜክሲኮ፣ ህንድ እና ማሌዥያ ከፍተና ገንዘብን በህገወጥ ዝውውር ከሚያጡ ሃገራት መካከል ዋንኞቹ መሆናቸውን የፋይናንስ ተቋሙ አመልክቷል። ኢትዮጵያ ካላት አነስተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የውጭ ንግድ ገቢ አኳያም በየአመቱ እያጣች ያለው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የድርጅቱን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ ዘ-ሲቲዝን የተሰኘ ጋዜጣ አርብ እለት ዘግቧል። የአለም ባንክን ጨምሮ የብሪታኒያ መንግስትና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ የምታጣውን ገንዘብ እንዲቀንስ ለማድረግ የስልጠናና የምክር ድጋፍን እየሰጡ ኣንደሚገኝም ታዉቋል። በህገወጥ መንገድ ከሃገር የሚወጣው ገንዘብ በላኪና በአስመጪዎች እንዲሁም በሌሎች የገንዘብ ዝውውሮች መሆኑን የፋይናንስ የደህንነት ተቋሙ መረጃ አመልክቷል። ሀገሪቱ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2004 እስከ 2013 ድረስ ከሃገሯ የወጣው ወደ 26 ቢሊዮን ዶላርም በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛው ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ትግሉ ከ10 ዓመት በኋላም እልባት አለማግኘቱ ተገልጿል። የመንግስት ባለስልጣናትም በበኩላቸው የህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ሲሉ ምላሽ መስጠት ዘሲቲዝን ጋዜጣ በዘገባው አስነብቧል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ሊቀመንበር ኦቦ በቀለ ነጋ ዛሬ በመንግስት ደህንነቶች የደረሰባቸውን ድብደባና ዛቻውን በፁሁፍ ለኢትዮዽያ ህዝብ ይፋ አደረጉ

 "ኦቦ በቀለ ነጋ ዛሬ በህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ በሚመራው ጉጀሌ የመንግስት ደህንነቶች የደረሰባቸውን ድብደባና ዛቻውን በፁሁፍ ለኢትዮዽያ ህዝብ ይፋ አደረጉ
ወዳጆቼ ዛሬ ማለዳ ወደ ስራ እያመራሁ ሲቪል የለበሱ 4 ሰዎች ስሜን ጠርተው ሰላምታ ካቀረቡልኝ በኋላ ፖሊሶች መሆናቸውን ነግረውኝ እኔን ካስቆሙበት ቦታ አጠገብ ወደሚገኘው መኪናቸው እንድገባ ጠየቁኝ።ፈቃደኛ አለመሆኔን ስነግራቸውም እጆቼን ይዘው እየጎተቱኝ በመኪናቸው የኋላ መቀመጫ ላይ እንድቀመጥ አድርገውኝ መንዳት ጀመሩ ። መኪናው መንቀሳቀስ እንደጀመረም መማታት ጀመሩ ፣በቀኝና በግራዬ የተቀመጡት ሁለት ሰዎች ሲደበድቡኝ ጋቢና የተቀመጠው ወደኋላ ዞሮ በመሳሪያው ፊቴን ይነካ ነበር ።
እየደበደቡኝ ይህንን የሚያደርጉት ማስጠንቀቂያቸውን ችላ ብዬ ለሚዲያ መረጃ በመስጠቴ እንደ...ሆነ ይነግሩኝ ነበር ።ድብደባቸውን እንዳቆሙም መሳሪቸውን እንደደገኑ ስልኬን ወሰዱብኝ ።የሚሉኝን ካላደረግኩም ለእኔና ለቤተሰቦቼ እንደሚመጡ አስፈራርተውኛል።
“ከዛሬ ጀምሮ ከቤትህ ብትወጣ ወይ ሚዲያ ብታናግር በአንተም ሆነ በቤተሰቦችህ ላይ ለሚሆነው ነገር ሃላፊነቱ ያንተ ነው” ብለውኛል ።
የእኔ ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦቼ ህይወት አደጋ ውስጥ እንደሆነ በመንገርም ከመልቀቃቸው በፊት የሚሉኝን ካላደረኩ እንደሚገሉኝ ዝተውብኛል። ከእንግዲህ ወዲህ እናንተን የምናስርበት ቦታ የለንም:: ወይ እንገድልሃለን ወይ በመኪና ገጭተን ፓራላይዝ እናደርግሃለን ብለውኛል። የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ ክልል ብዙዎች እያቀረቡለት ለሚገኘው አቤቱታ ጆሮውን ደፍኖ ሰላማዊውን ጥያቄ በኃይል ለማፈን እየሰራ በመሆኑ ያለምንም ኃላፊነት ዜጎችን እያሰረ፣እያዋረደና እየገደለ ይገኛል።
በቀለ ገርባ፣ ደጀን ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላና ደስታ ዲንቃን ጨምሮ 4.000 የሚደርሱ የፓርቲያችን አባላት በግፍ ታስረዋል ። መንግስትና ሁኔታውን በፀጥታ እየተመለከቱ የሚገኙ አካላት ንፁሃንን ማሰርና መግደል የሚልዮኖችን ህጋዊ ጥያቄ ለማፈን መፍትሔ እንደማይሆንና ኦሮሞውንም ይህ ድርጊት እንደማያስቆመው ይገነባሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ። እስከዛው ግን እንደግለሰብና እንደ ኦፌኮ አባልነቴ በሰላማዊ አግባብ የኦሮሞ ህዝብ አንደበት መሆኔን እቀጥላለሁ ።ምክንያቱም ለነፃነትና ለህዝባችን ክብር ስንል በምንከተለው ሰላማዊ ትግል እኔና ሚልዮን ኦሮሞዎች ህይወታችንን ጭምር ለመክፈል ተዘጋጅተናል።"

ከአክብሮት ጋር
በቀለ ነጋ
የኦሮሞ ፌደራሊስት ሊቀመንበር