Tuesday, 23 February 2016

በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር ህወሃት/ኢህአዴግ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር ህወሃት/ኢህአዴግ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ
ኢሳት (የካቲት 15 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልል ለሶስተኛ ወር ቀጥሎ ያለውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማክሰኞ አስታወቀ። 
በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ በክልሉ በበርካታ አካባቢዎች እየተካሄደ ካለው ተቃውሞ ጀርባ የጥፋት ሃይሎች ይገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል። 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደራጁ የጥፋት ሃይሎች ያሏቸውን አካላት በስም ባይጠቅሱም መንግስትን የማፈራረስና የመቀየር ተልዕኮ አላቸው ሲሉ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። 
ድርጊቱንም ለመቆጣጠር መንግስት የማያዳግም እርምጃን እንደሚወስድ ገልጸው በምዕራብ አርሲና በሃረር አካባቢዎች ተቃውሞ መቀጠሉን አመልክተዋል።
የአሜሪካ መንግስትና የአውሮፓ ህብረት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያለውን የሃይል እርምጃ በማውገዝ የኢትዮጵያ መንግስት ከድርጊቱ እንዲቆጠብና ለተቃውሞ ሰላማዊ ምላሽን እንዲሰጥ ማሳሰባቸው የታወሳል።
በክልሉ እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ያለፉ የመብት ጥያቄን ያካተተ እንደሆነ የሚገልጹት እነዚሁ አካላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመ ግድያን ማጣራት እንዲካሄድበት ጠይቀዋል።
በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ሰኞ መግለጫን ያወጣው ሂውማን ራይትስ ዎች በበኩሉ ሶስተኛ ወሩን በያዘው ተቃውሞ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና እርምጃው ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክቷል።
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ ያለው ተቃውሞ መፍትሄን እንዲያገኝ በመጠየቅ ላይ ቢሆኑም መንግስት የጥፋት ሃይሎች እጅ አለበት በማለት የሚወስደውን የሃይል እርምጃ እንደሚቀጥል ማክሰኞ ገልጿል።

Sunday, 21 February 2016

የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አዛዦች በአዲስ አበባ ስብሰባ አካሄዱ፡፡ ስብሰባው ያለምንም ውጤት በግጭት ተቋጭቷል


የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አዛዦች በአዲስ አበባ ከየካቲት 9 እስከ 12 2008 ዓ.ም የተሰበሰቡ ሲሆን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የፀጥታ ሁኔታ እና የአባላት መክዳት እያነሱ ከተወያዩባቸው አጀንዳዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በስብሰባው ላይ የአማራና የኦሮሞ ተወላጅ አዛዦች "እኛ ከእናንተ የተሻለ የትምህርት ደረጃና ልምድ እያለን ሁሉንም ቦታ ጠቅልላችሁ ይዛችሁት ተገቢው ቦታ አልተሰጠንም..." በማለት ህወሓቶችን ልካቸውን ነግረዋቸዋል፡፡
ህወሓቶች በፌደራል ፖሊስ ተቋም ውስጥ ባሰፈኑት ዘረኝነት ምክንያት ሰራዊቱ በመፍረስ ላይ እንደሚገኝ ስብሰባው ላይ በተደጋጋሚ ...ተወስቷል፡፡ በውይይቱ ላይ ተቃውሟቸውን ያሰሙ የኦሮሞና አማራ ተወላጅ አመራሮች ከህወሓቶች "የእናስራችኋል" ማስፈራሪያ ደርሷቸዋል፡፡
በመጨረሻም ስብሰባው ወደ ለየለት ንትርክና አምባጓሮ በማምራቱ አብዛኞቹ አዛዦች እንዲበተኑ ተደርገው ውይይቱ በጥቂት ዋና፣ ዋና አመራሮች ለተጨማሪ ጊዜ ተካሂዷል፡፡ የፌደራል ፖሊስ አደረጃጀት ሊፈርስ እንደሚችልም ጭምር ጭምጭምታ ተሰምቷል፡፡
በተያያዘ ዜና የሚከዱ የፌደራል ፖሊስ አባላት ቁጥር አሁንም ከቀን ወደ ቀን እየናረ መምጣቱ እየተነገረ ነው፡፡ በጎንደር ብቻ ቢያንስ በቀን 3 የፌደራል ፖሊስ አባላት እንደሚከዱ የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ ዜና ምንጮች ገልፀዋል፡፡
 #የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ#

የ24ኛ ክፍለ ጦር አባላት በገፍ እየገዱ መሆናቸው ታወቀ

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ)
የ24ኛ ክፍለ ጦር አባላት በገፍ እየገዱ መሆናቸው ታወቀ፡፡
በሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ የነፃነት ድርጅቶች ለረጅም ዓመታት የዘለቀ የሽምቅ ውጊያ ጥቃት ሲደርስበት፣ እስከ ሬጅመንት ድረስ እየተደመሰሰ ሲፈርስና እንደገና በሰው ኃይልና በጦር መሳሪያ በተደጋጋሚ ሲገነባ የኖረው 24ኛ ክፍለ ጦር አባላት በውጊያ በእጅጉ ተሰላችተውና በስርዓቱ ተስፋ ቆርጠው በከፍተኛ ሁኔታ በመክዳት ላይ ናቸው፡፡
በተለይም ደግሞ የሽምቅ ውጊያ ጥቃቶች የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የሆኑ በሁመራና አካባቢው ሰፍረው የቆዩ ሬጅመንቶች ውልቃቸውን በመቅረታቸው ከአዘዞ እና ጭልጋ ሌሎች ሬጅመንቶችን አንስቶ የመተካት እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡
የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ የነፃነት ድርጅቶች ክንድ እየፈረጠመ መምጣት እና ዕለት ከዕለት በሚያደርጓቸው የሽምቅ ውጊያ ጥቃቶች የሚያሳርፉት ዱላ እየበረታ መሄድ በዋነኝነት አርበኝነት በሚፋፋምበት አካባቢ የሚገኘውን 24ኛ ክፍለ ጦር አፍረክርኮታል፡፡

Friday, 19 February 2016

እነ በቀለ ገርባና ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ለመጋቢት 9 ተቀጠሩ

እነ በቀለ ገርባና ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ለመጋቢት 9 ተቀጠሩ
*ጋዜጠኛ ጌታቸው ጨለማ ቤት ታስሯል
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በሽብር ተጠርጥረው በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል በእስር ላይ የሚገኙት የኦፌኮ አመራሮች እነ በቀለ ገርባ እና ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው የ28 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ዛሬ የካቲት 11/2008 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት የቀረቡት የኦፌኮ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በቀለ ገርባ እና በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሌሎች የፓርቲው አባላት፣ እንዲሁም ታህሳስ 15/2008 ዓ.ም ለእስር የተዳረገው የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው እና የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው አቶ ዳንኤል ተስፋየ ፖሊስ ምርመራየን አልጨረስኩም በሚል የጠየቀባቸው የ28 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተፈቅዶለታል፡፡...
የጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን ከችሎቱ በኋላ እንደገለጹት ፖሊስ ‹‹ግብረ አበር መያዝ ይቀረኛል፣ ምስክር አላደራጀሁም…›› የሚል ካለፈው ጋር ተመሳሳይ ምክንያት በመስጠት ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡ ደንበኛቸው ከታሰረ ጀምሮ አንድም ቀን አግኝተው ለማነጋገር እንዳልተፈቀደላቸው ለችሎት የገለጹት ጠበቃ አምሃ፣ ጌታቸው ጠበቃውን ሳያነጋግር ቃሉን ለፖሊስ ለመስጠት ፍቃደኛ እንዳልሆነ ፍርድ ቤቱ እንዲገነዘብላቸው በድጋሜ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው በበኩሉ ያለፉትን 28 የምርመራ ቀናት የተጠየቀው ነገር እንደሌለ፣ ነገር ግን በጨለማ ቤት እንዳሰሩት ለችሎት ገልጹዋል፡፡
በተመሳሳይ የምርመራ መዝገብ የሚገኙት አቶ ዳንኤል ተስፋየ እና አቶ ሸዋታጠቅ ኃ/መስቀል በበኩላቸው ቤተሰቦቻቸው እንዲጠይቋቸው እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ችሎት የቀረቡት እነ በቀለ ገርባም እንዲሁ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸው 28 ቀናት ተፈቅዶለታል፡፡ የዛሬውን የችሎት ውሎ ለመከታተል የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦችና ወዳጆቻቸው ፍርድ ቤት ግቢ ቢገኙም ችሎቱ ዝግ በመደረጉ አንድም ሰው መከታተል እንዳልቻለ ታውቋል፡፡


Sunday, 14 February 2016

በጎንደር ከተማ የሚገኙ የፌደራል ፖሊስ አባላት በገፍ እየከዱ ነው

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ)
‪#‎በጎንደር‬ ከተማ የሚገኙ የፌደራል ፖሊስ አባላት በገፍ እየከዱ ነው፡፡
በጎንደር ከተማና አካባቢው የጦር ካምፕ መስርተውም ሆነ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ አገዛዙን ሲያገለግሉ የቆዩ የፌደራል ፖሊስ አባላት በከፍተኛ ሁኔታ ከነትጥቃቸው በመሰወር ላይ ናቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ብቻ ከ30 በላይ ፌደራል ፖሊሶች ከነትጥቃቸው ስርዓቱን በመቃወም ከየካምፓቸውና በውሎ ጠፍተዋል፡፡
የህወሓት አገዛዝ ይህን የፌደራል ፖሊስ አባላት መክዳት ለማስቆም ተደርጎ የማይታወቀውን ጥቅማጥቅምና የማዕረግ እድገት ለመስጠት ቢወስንም ሰራዊቱ እንደበፊቱ በቀላሉ ተሸውዶ ሰጥ ለጥ ብሎ ወደ ሎሌነት ተግባሩ ሊመለስ አልቻለም፡፡ እንዴውም በተቃራኒው የሚጠፉ የፌ...ደራል ፖሊስ አባላት ቁጥር ከቀደመው ጊዜ ጋር ሲነፃፀር አየናረ መጥቷል፡፡
በመሆኑም ለዛሬ ሰፊ ስብሰባ ሊደረግ ፕሮግራም ተይዟል፡፡


Saturday, 13 February 2016

በጎንደር ከተማ ጎሃ ሆቴል ውስጥ ከጥር 28 እስከ የካቲት 1 2008 ዓ.ም በድብቅ በተካሄደው ስብሰባ

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ)
የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የአማራ ክልል ሹሞች በጎንደር ጎሃ ሄቴል ለሦስት ተከታታይ ቀናት ያደረጉት ድብቅ ስብሰባ ያለምንም ውጤት በፀብ ብቻ ተቋጨ፡፡ በህወሓቶችና በብአዴኖች መካከል የተካረረ ፍጥጫና ንትርክ ተከስቶ የነበረ መሆኑም ተደርሶበታል፡፡
===================================================
በጎንደር ከተማ ጎሃ ሆቴል ውስጥ ከጥር 28 እስከ የካቲት 1 2008 ዓ.ም በድብቅ በተካሄደው ስብሰባ ላይ የተገኙት የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት አባይ ፀሐዬ፣ ስብሃት ነጋ፣ ደብረ ፂዮን ገ/ሚካኤል፣ አባይ ወልዱ እና የትግራይ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ሹም ናቸው፡፡
ገዱ አንዳርጋቸው፣ አለምነው መኮንን እና መኳንንት /የአማራ ክልል ፀጥታ ሹም/ ደግሞ ከብአዴን ወገን የተገኙ የአማራ ክልል ሹማምንቶች ነበሩ፡፡
የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የህወሓት ዲቃላ የሆነው ብአዴን ባለስልጣናት በጎንደር ጎሃ ሆቴል ተሰብስበው የተነታረኩባቸው አጀንዳዎች ሁለት ሲሆኑ የወልቃይትን የአማራ ማንነት ጥያቄ እና ብረት ያነሱ የነፃነት ድርጅቶችን /በተለይም አርበኞች ግንቦት 7ን/ በሚመለከት ነው፡፡
የትጥቅ ትግል እያደረጉ የሚገኙ የነፃነት ድርጅቶችን በሚመለከት ህወሓቶች "ሰተት ብለው ከበረሃ ወደ ህዝቡ እንዲገቡ እያደረጋችኋቸው ነው..." በማለት ብአዴኖችን ወቅሰዋቸዋል፡፡
ከወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ደግሞ የትግራይ ክልል አስተዳዳሪና የህወሓት ሊቀ መንበር የሆነው አባይ ወልዱ እንዲህ ብሏል፡፡
"ወልቃይት የትግራይ ነው! የአማራነት ጥያቄው በዚህ የማያቆምና ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን...!"
ቀጥሎም አባይ ወልዱ የአማራ ክልልን አስተዳዳሪ ገዱ አንዳርጋቸውን
"አንተ የአማራን ህዝብ የጦር መሳሪያ ያስታጠከው ሆነ ብለህ በትግራይ ላይ ጦርነት ለማወጅ ነው..." በማለት ተናግሮታል፡፡
ገዱ አንዳርጋቸውም በበኩሉ
"እኔ ህዝቡ በሀብቱ ገዝቶ ከጥንት ጀምሮ ታጥቆት የቆየውን ጦር መሳሪያ ህጋዊ ፈቃድ በመስጠት አፀናሁለት እንጂ ልክ እንዳንተ ከመንግስት ግምጃ ቤት አውጥቼ በገፍ አላስታጠቁትም፡፡ በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት አወጅክ ላልከኝም የትግራይን ህዝብ ሰብስበህ በወልቃይት ህዝብ ላይ እርምጃ እንወስዳለን ብለህ በይፋ ጦርነት ያወጅከው አንተ ነህ፡፡" በማለት ለአባይ ወልዱ መልስ ሰጥቶታል፡፡
የጦር መሳሪያን በሚመለከት ደብረ ፂዮን ገ/ሚካኤል ገዱ አንዳርጋቸው የአማራን ህዝብ እንዳስታጠቀ ወቀሳ ሰንዝሯል፡፡ ደብረ ፂዮን ስለ ወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ የሚከተለውን በማለት ቁልጭ ያለ አቋሙን አስቀምጧል፡፡
"የወልቃይት ጉዳይ ክልል አንድን እንጂ ማንንም አይመለከተውም፤ ውሳኔውም ሊሆን የሚችለው የክልል አንድ ብቻና ብቻ ነው፡፡"
ለዚህ የደብረ ፂዮን ንግግር ገዱ አንዳርጋቸው ሲመልስ
"እኛ ሄደን ኑ አንላቸውም፤ ከመጡ ግን የማንቀበልበት ምንም ምክንያት የለም፤ ደግሞም ውሳኔ ማስቀመጥ ያለበት ራሱ የወልቃይት ህዝብ ነው፡፡"
በመሆኑም በሁለቱ ክልሎች /በትግራይና አማራ/ አስተዳዳሪዎች ማለትም በአባይ ወልዱና ገዱ አንዳርጋቸው መካከል ስብሰባው ውስጥ የተካረረ ፍጥጫ ተከስቶ ነበር፡፡
ህወሓቶች ለገዱ አንዳርጋቸው ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥተውታል፡፡
በአጠቃላይ በጎንደር ጎሃ ሆቴል ከጥር 28 እስከ የካቲት 1 2008 ዓ.ም በድብቅ የተካሄደው የህወሓቶችና የብአዴኖች ውይይት ያለምንም መግባባት በፀብ ብቻ ተጠናቋል፡፡

Thursday, 11 February 2016

ኦሮሚያ የመላው ኢትዮጵያዊ መላው ኢትዮጵያም የሁሉም ኦሮሞ ናት!

ኦሮሚያ የመላው ኢትዮጵያዊ መላው ኢትዮጵያም የሁሉም ኦሮሞ ናት!
ከጃዋር ሃሳብ የማልስማማበት እና የምስማማበትን ስለመለየት፤
የኛ ሀገር ፖለቲካ የቡዳ ፖለቲካ ነው እንዳሉት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና አሁንም ድጋሚ ፖለቲካችንን ቡዳ ሊበላው ነው መሰል ጣት መቀሳሰር እና እነ እንትና እነ እንትና መባባል ልንጀምር ይመስላል… ምናባቱ እንግዲህ ካልደፈረሰ አይጠራም…
ጃዋር ሰሞኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዋሽንግተን ዲሲ ካደረጉት ንግግር በኋላ በአራት ጉድዮች ላይ አስተያየት ሰጥቷል። ካነሳቸው ሃሳቦች ውስጥ በተወሰነ ደረጃ የምስማማባቸው ሃሳቦች ቢኖሩኝም በርካታ የማልስማማባቸው ሃሳቦችም አሉ። ከሁሉ ከሁሉ ግን በትልቁ የማልስማማበት፤ ኦሮሞ በሙሉ ተመሳሳይ ነው ብሎ ሁሉንም ኦሮሞዎች በአንድ ቅርጫት ውስጥ ለማስቀመጥ የሚሞክረው ነገር ሁልጊዜም በጣም የሚያበሳጨኝ ነው። (እነደሱ አባባል እርሱ በሚለው የማይስማማ ኦሮሞ ኦሮሞ አይደለም (ሲያናድድ!))
እኛ ኦሮሞዎች ሰዎች ነን። ምንም እንኳ የሰው ልጆች በሙሉ በፍጥረታቸው አንድ ናቸው ቢባልም፤ በአስተሳሰብ እና በአመለካከት ግን አንድ አይነት መሆን አይችሉም። ሁሉም ሰው የየራሱ አመለካከት እንዳለው ሁሉ፤ ኦሮሞዎችም የየራሳችን አመለካከት አለን። እኛ በፋብሪካ የተመረትን ሮቦቶች አይደለንም። የተለያየ አመለካከት የተለያየ አስተሳሰብ፣ የተለያየ የምፍትሄ አቅጣጫ፣ የተለያየ ምኞት እና ፍላጎት ያለን ሰዎች ነን። ይሄ ሰው በመሆናችን የተሰጠንም ጸጋ ነው። ጃዋር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ ‘’ከለዘብተኛ ኦሮሞዎች ጋር አብረን እየሰራን ነው’’ ማለቱን ተከትሎ በኦሮሞ ውስጥ ለዘብተኛ አክራሪ የለም ብሎ ይሞግተናል። ሞልቶ! በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ በአንድ ጉዳይ ላይ አክራሪ እና ለዘብተኛ እንዳለው ሁሉ በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥም ይሄ አለ። ወደፊትም ይኖራል።
ለምሳሌ ያክልም፤ ራሱ ከጃዋር እና የመሳሰሉት ኦሮሚያ የኦሮሞ ናት ሲሉን እየሰማን ነው። በነገራችን ላይ የ ‘የ’ እና የ ’ለ’ ነገር በትርጉሙ ላይ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም። ኦሮሚያ ለኦሮሞ ናት ተባለም ኦሮሚያ የኦሮሞ ናት ተባለም ምንም የፍቺ ልዩነት የላቸውም። (ወዳጃችን ጃዋር ኦሮሚያ ለኦሮሞ ናት አላልኩም ኦሮሚያ የኦሮሞ ናት ነው ያልኩት ሲል አይቼ ባውጠነጥን ባውጠነጥን ምንም ልዩነት አላየሁበትም።) የሆነው ሆኖ ጃዋር እንደሚያስበው ይሄ አስተሳሰብ የሁሉም ኦሮሞዎች አስተሳሰብ ነው። በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞም ዋና ሃሳብ ይሄ ነው ይለናል።
እኛ ጃዋር ኦሮሞ አይደለም ብለን አንከራከርም። ነገር ግን እርሱ ብቻ ሳይሆን እኛም ኦሮሞዎች ነን። እንደኛ አስተሳሰብ ኦሮሚያ የመላው ኢትዮጵያዊ መላው ኢትዮጵያም የኦሮሞ ናት። እንኳንስ ኦሮሚያ እና ብሪታኒያ እና አሜሪካንን የመሳሰሉት ሀገሮች እንኳን የብርትሾች እና የአሜሪካኖች አይደሉም፤ የሁላችንም ናቸው እንጂ! (ምንም እንኳ እንደ ዶናልድ ትራምፕ አይነት ቀውሶች ይሄ አሳብ ቅዠት ቢመስላቸውም አሁን አለም ባለችበት ደረጃ ግን ማንም ሰው የሀገሪቱን ህግ እና ደንብ አክብሮ እስከኖረ ድረስ ሁሉም ሀገር የሁሉም ነው። በዛ መሰረት ነው ጃዋርም ሆነ እኔ በአሜሪካ እና እንግሊዝ የምንኖረው!)
በኦሮሚያ ክልል የተነሳው ተቃውሞ ዋና ማጠንጠኛ ኦሮሞ ዘመዶቻችን አንድም በገዛ ወገኖቻቸው፤ (በኦህዴድ አባላት) አንድም ከፌደራል በሚሄዱት እነ አባይ ጸሃዬ የሚደርስባቸው ስር የሰደደ በደል ሞልቶ ስለፈሰሰ ነው፤ እንጂ ኦሮሚያ ለኦሮሞ ትሁን በሚል አይደለም። እንደዚ የሚሉ ቢኖሩም እንኳ በኔ አስተሳሰብ ስህተት ውስጥ እየገቡ ነው። ማንም ሰው በአግባቡ እና በደንቡ መሰረት እስከተንቀሳቀሰ ድረስ (በእግር ኳስ ቋንቋ ፌር ፕሌይ እስከተጫወተ) ሁሉም ሃገር የርሱ ነው። ኦሮሚያን ጨምሮ። ብቻ ገበሬዎችን ያለአግባብ አያፈናቅል። ብቻ ገበሬውን በገዛ መሬቱ ላይ ከአምራችነት ወደ ዘበኛነት አይቀይር እንጂ!
አሁን ኢህአዴግ እየፈጸመ ያለው ዘረፋ በኦሮሚያ ላይ ነውር ነው! በትግራይም ላይ ሲፈጸም ብልግና ነው! በአማራ ክልልም ሲደረግ ጸያፍ ነው።
ይልቅስ ጃዋር በብሄር ስለመደራጀት ያነሳው ነገር ላይ እስማማለሁ። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ይሄ የኔ አመለካከት ነው ብለው በነገሩን መሰረት የብሄር ወይም ዘውጌ ፖለቲካዊ ስብስብ አይመስጣቸውም ብቻ ሳይሆን አፍራሽ ነው ሲሉም ኮንነውታል። በርግጥ ‘’እባብን ያየ በልጥ ይደነግጣል’’ እንዲሉ አሁን አሁን እየሆነ እንዳለው ነገር የብሄር አደረጃጀቶች የሚያስፈራ ነገር አላቸው። ቢሆንም ግን አፍራሽ ናቸው ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ ከባድ ነው። ሰዎች በመሰላቸው መልኩ የመደራቸት እና የመታገል መብታቸው በጽኑ ሊከበር ይገባል። በሰለጠኑት ሃገራት በብሄር የተደራጁ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ግንባታ አፍራሽ ሚና ሲጫወቱ አላየንም። እንደ ምሳሌም ስኮቲሽ ናሽናል ፓርቲ በ ዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ማየት ይቻላል። እኛም ሃገር ቢሆን ፖለቲካችን አፍራሽ ሚና የሚኖረው ከአያያዛችን እንጂ ከአደረጃጀታችን አይመስለኝም። (እንደውም ከቤተሰብ ጉባኤ አንስቶ ብብሄር መደራጀት ተፈጥሯዊ ነው ብዬ አስባለሁ.... አፍራሽ የሚሆነው ክኔ ብሄር በላይ ላሳር ማለት ሲጀመር ነው! እሱን የሚገራ ሀገር አቀፍ ህግ መኖር ይኖርበታል!)
በኢሳት ቴሌቪዥን የኦሮምኛ ቋንቋ ዝግጅቶች መጀመራቸውን አስመልክቶ የኦሮሞን ህዝብ ትግል ለማዳከም ነው የሚለን ጃዋር ከላይ እንዳነሳሁት በኢሳት ቴሌቪዥን ላይ በአዘጋጅነት የሚሰሩትን ኦሮሞዎች ስለ ኦሮሞ ጉዳይ የማያስቡ ራሱን ደግሞ ከማንም በላይ ለኦሮሞ አሳቢ የማድረግ አዝማሚያ ነው ያየሁበት... ይሄኔ ይቺ ሰውዬ ቀስ ብላ እኔንም ለኦሮሞ አታስብም ትለኝ ይሆናል እኮ ብዬ ስቄ ትቼዋለሁ!
እያልኩ ልጻፍ ልተወው… በማለት እያሰብኩ ነው….
(ጋዜጠኛ አበበ ቶላ ፈይሳ አቤ ቶኪቻው)