Sunday, 31 January 2016

በሰሜን ጎንደር የወያኔ አፈና ቀጥሏል

ዛሬም በሰሜን ጎንደር የወያኔ አፈና ቀጥሏል ‪#‎AmharaProtests‬
‪#‎ETHIOPIA‬ | ህወሃት መራሹ የወያኔ ቡድን በሰሜን ጎንደር ሽንፋ እና አካባቢው ላይ የሚገኙ በህብረተሰቡ ተሰሚነት ያላቸውን የአማራና ቅማንት ማህበረሰብ አካል የሆኑ ሰዎችን እያፈነ ወደ ማጎሪያ ቤቶቹ ማጋዝ ቀጥሏል፡፡
ታሳሪዎቹ ለዕስራት የተጋለጡበት ምክንያት የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ከለላውን አንቀበልም ልንዋጋው ይገባል በማለታቸው እና በተጨማሪ አማራና ቅማንት ማህበረሰቦች ላይ እየሰራ የሚገኘውን የወያኔ ሴራ ለህብረተሰቡ እያጋለጡ በመሆኑ እንደሆነ ከቦታው የመረጃው ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡
ከታፈኑት ሰዎች መካከል
-መ/አለቃ ደጀኔ ወርቁ
-አቶ አታላይ ደምሴ
-አቶ ጋሹ ጌጡ
-አቶ ነጋ አቤ፥አቶ አስቻለው እና ሌሎች በርካቶች ይገኙበታል፡፡
©

Wednesday, 20 January 2016

አቶ ኦባንግ የኢህአዴግ ደጋፊ ስደተኞችን አስጠነቀቁ

 ኦባንግ የኢህአዴግ ደጋፊ ስደተኞችን አስጠነቀቁ “በአስመሳይ ስደተኞች ላይ በቂ መረጃ አለ” “ክፉን በክፉ መመከት ባያስደስትም ወቅቱ ያስገድደናል” ሲሉ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ በተለይ ለጎልጉል ተናገሩ። አገዛዙን ሸሽተው በተለያዩ አገራት ከለላ አግኝተው በስደት የሚኖሩም ሆኑ ጉዳያቸው እየታየ ያሉ ወገኖች አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ህግ አውጪዎች፣ የጀርመን የኢሚግሬሽን ሃላፊዎችና ከፍተኛ የፖለቲካ ሰዎች፣ ከኖርዌይ የኢሚግሬሽን ጉዳይ ሃላፊዎችና ተዛማጅ ሃላፊነት ካላቸው የህግ ክፍሎች፣ በካናዳ በተለያዩ ደረጃ ካሉ ባለስልጣናትና ወትዋቾች (አክቲቪስቶች)፣ በስዊድን አንዲሁም በእንግሊዝ በተመሳሳይ ግንኙነት ፈጥረው እየሰሩ መሆኑንን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “አገራቱ የስደት ፈቃድ ካገኙ በኋላ ለስደት ዳረገን ከሚሉት መንግሥት ጋር በቅርብ እየሰሩ ስላሉ አስመሳይ ስደተኞች አስገራሚ መረጃዎች መሰብሰባቸውን አውቃለሁ” ብለዋል።
አቶ መለስ በሞቱ በወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በካናዳ ቫንኮቨር 27 አንድ አይነት ቋንቋ ብቻ የሚናገሩ ወጣቶች ጥገኛነት መጠየቃቸውን ጉዳዩን በጥብቅ እየመረመሩት ካሉ ክፍሎች ማረጋገጣቸውንና የምርመራውን ውጤት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ ኦባንግ፣ “ወጣቶቹ ካናዳ የገቡት ለእያንዳንዳቸው 75 ሺህ ዶላር በማውጣት ነው። ይህን ገንዘብ ማን ሰጣቸው? እንዴት አገኙት? እንዴት ከአንድ አካባቢ (ክልል) ብቻ ሊሆኑ ቻሉ? የሚሉት ጉዳዮች ምርመራውን በያዙት ወገኖች ላይ ግራሞት የፈጠረ ትልቅ ጉዳይ ነው” በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት ከገንዘብ ማሸሽ ጋር በማያያዝ አመላክተዋል። ለምሳሌ አንድ ጉዳይ አነሱ እንጂ በመላው ካናዳ በተመሳሳይ የምርመራ ስራ እየተሰራ መሆኑንን ተናግረዋል።
የካናዳው አንድ ማሳያ ሲሆን በአሜሪካ ግዙፍ ቪላዎችን እየገዙ ያሉት ክፍሎች ጉዳይ ከገንዘብ ማሸሽ ጋር ተያይዞ እየተመረመረ እንደሆነ አቶ ኦባንግ አስረድተዋል። ጥገኝነት ካገኙ በኋላ “ሊገለን ሲል አመለጥነው” ያሉትን ኢህአዴግን የሚደግፉ ክፍሎች ላይም ለሚመለከታቸው ባለስልጣናትና ተቋማት ከሚቀርበው መረጃ በተጨማሪ ከፍትህ ወዳድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር ድርጅታቸው በጥምረት እየሰራ መሆኑን አቶ ኦባንግ አልሸሸጉም፡፡
በጀርመን ኑረንበርግ በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰሩ ባለስልጣናት በተመሳሳይ የምርመራ ስራ እያከናወኑ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ኦባንግ፣ በግል በጉዳዩ ዙሪያ መነጋገራቸውን አስታውቀዋል። የጥገኝነት ፈቃድ ካገኙ በኋላ ዲያስፖራውን በመከታተልና አገር ቤት የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ለችግር እንዲዳረጉ የሚያደርጉትን ክፍሎች ማንነት ነቅሰው እንደሚያውቋቸው ባለሥልጣናቱ በግንኙነታቸው ወቅት እንዳረጋገጡላቸው አመልክተዋል።
“ኢህአዴግ ለጊዜው የጠመንጃ ሃይል አለው። የገንዘብ አቅም አለው። ወዳጆችም አሉት። እኛ ደግሞ በየአቅጣጫው ፍትህ ወዳድ አጋሮች አሉን። ከነሱ ጋር እየሰራን ነው” በማለት አስረግጠው የተናገሩት ኦባንግ በማንኛውም መስፈርት ስደት ላይ ያሉ ወገኖችን መከታተልና መሰለል ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
“አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ስዊድንና ጀርመን አገር ባለስልጣናቱ ከበቂ በላይ መረጃ አግኝተዋል። እኛም እየሰራንበት ያለ ተከታታይ ስራ አለ። በየአቅጣጫው የሚደረገው ትግል በቅርቡ ፍሬው መታየት ይጀምራል” የሚሉት ኦባንግ ርምጃው መወሰድ ሲጀምር ከስድስት እስከ አስራ ሁለት ዓመት እስር እንደሚያስከትል፣ ከዚያም የከፋ አደጋ እንዳለው ጠቁመዋል።
በትምህርትና በተለያዩ ስልጠናዎች ወደ ተለያዩ ዓለማት የሚሰማሩ የአገዛዙ አገልጋዮችም ቢሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው የሚያሳስቡት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር “አገዛዙ መድቧቸው በየኤምባሲው ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች፣ የስለላ ሰዎች፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት ምስላቸውንና ማንነታቸውን ባደባባይ አይገልጹም። በኤምባሲዎች ድረ ገጽ ላይ እንኳ ስለማንነታቸው በቂ መረጃ ለመስጠት ድፍረት የላቸውም። የስርዓቱ ባህሪና የወንጀለኛነቱ መጠን ራሳቸውን እንዲገልጹ አይፈቅድላቸውም” በማለት በተራ መደለያና ጥቅማ ጥቅም ደረታቸውን እየሰጡ ያሉ ወገኖች አካሄዳቸውን በመመርመርና የሚያስከብራቸውን ተግባር እንዲፈጽሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
“ምክር በመለገስ ሰፊ ጊዜ የወሰድነው ክፉን በክፉ የመመለስ እምነት፣ ክፉ እንድናደርግ የሚገፋን ድርጅታዊ አቋም ስለሌለንና የሚጠሉንን ጭምር ነጻ የሚያወጣ ግዙፍ ራዕይ ስላለን ነው” የሚል ጥልቅ አስተያየት የሰነዘሩት አቶ ኦባንግ፣ በአገራቸው መኖር ያልቻሉ ወገኖች ተሰደውም ሰላም ሲያጡ መመልከት ግን የማይቻልበት ደረጃ መድረሱን አመልክተዋል። ከዚህም በተጨማሪ እሳቸው በግል፣ ድርጅታቸው በመርህ የሚታገሉለት የሰዎች መብት መከበር ብሩህ አጀንዳ በዝምታ እንዲቀመጡ እንደማይፈቅድላቸው ተናግረዋል።
ከኖርዌይ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ጋር በተገናኙባቸው ወቅቶች ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ በግልጽ እንደነገሯቸው ያመለከቱት ኦባንግ ሜቶ፣ አሁን ስሙንና ዝርዝር ጉዳዩን ለመናገር ፈቃደኛ ካልሆኑት ክፍል ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑንን ጠቁመዋል። አኢጋን ያቋቋመው የግልጽነትና የተጠያቂነት ግብረ ሃይል አንዱና ትልቁ ስራው እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን መርምሮና አጣርቶ ለሚመለከታቸው በማቅረብ ፍትህን መጠየቅ መሆኑንን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “ዝርዝሩን መናገር ቢከብድም ብዙ ስራ እየሰራንበት ያለው የስደተኞች ጉዳይ የሌሎችንም ተሳትፎና ትብብር ይጠይቃል” ብለዋል።
“በስሜት መታገል አያዋጣም” የሚል የትግል ማስተካከያ ሃሳብ ፈንጠቅ ያደረጉት አቶ ኦባንግ የስደት ማመልከቻቸው ተቀባይነት አግኝቶ የመኖሪያ ፈቃድ ካገኙ በኋላ አገር ቤት በመመላለስ፣ ህግ በመተላለፍ ለአገዛዙ የሚሰሩ በሙሉ “ብልጥና አዋቂ ነን፣ ባለጊዜዎች ነን” በሚል አስተሳሰብ የሚንቀሰቀሱ አንደማያዋጣቸው ሲያሳስቡ “ለእንደዚህ አይነቶች ሁሉም ዓይነት መንገድ አይሰራላቸውም። ግለሰቦችንና ባለስልጣናትን ሳይሆን አሰራርን በማጭበርበር ይጠየቃሉ። አገራቱ እንደ ኢትዮጵያ ሳይሆን ስራ ላይ የሚውል ህግ አላቸውና ይተገብሩባቸዋል። አሰራራቸው ሲጭበረበር ዝም የማይሉት ለማንም ሲሉ ሳይሆን ለራሳቸው ሲሉ ነው። አሰራር / ሲስተም/ ሲበረዝ የሚያስከትለውን አደጋ ስለሚረዱ የሚታገሱ ካልሆነ በቀር በዝምታ አያልፉም። በኖርዌይም ሊሆን የታሰበው ይህ ነው። አሁንም ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እቸገራለሁ” በማለት ነው። አቶ መለስ ህይወታቸው ባለፈ ወቅት በስደት ካምፕ የሚኖሩ ጭምር ለቅሶ መቀመጣቸው በኖርዌይ ሚዲያዎች አስገራሚ ተብሎ መዘገቡ፣ በህዝቡና በፖለቲከኞች ዘንድ መነጋገሪያ አጀንዳ እንደነበር አይዘነጋም።
በርካታ አሳዛኝና ህሊናን የሚፈታተኑ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ያወሱት ኦባንግ ሜቶ፣ ህጻናትን በጉዲፈቻ ስም በመቸብቸብ፣ ሴት እህቶቻችንን አረብ አገራት ያለ ዋስትና በመላክ ከፍተኛ ገበያ እየሰሩ ያሉት የህወሃት ሰዎች እንደሆኑ በበርካታ ማስረጃዎች መረጋገጡን ያስታውሳሉ። አያይዘውም አገራቸውን ለቀው ለስደት የሚወጡትን ወደ ኬኒያ፣ ታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካ ብሎም በጅቡቲና በሶማሌ በኩል ገንዘብ እያስከፈሉ የሚያሻግሩት አሁንም እነሱ ናቸው ሲሉ አስቀድመው ስለ ጠየቁት ትብብር ማሳሰቢያቸውን ያጠናክራሉ።
“በማስተዋል እንስራ” የሚሉት ኦባንግ በየአቅጣጫው መረጃ ላይ የተኙና፣ በምን አገባኝ ስሜት ዝምታን የመረጡ ወገኖች ያላቸውን መረጃ በመስጠት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራ ያለውን ስራ እንዲያግዙ አሳስበዋል። ይህንን ማድረግ አቶ ኦባንግንና እርሳቸው የሚመሩትን ድርጅት መርዳት ሳይሆን ራስንና አገርን መርዳት እንደሆነም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ከተቋቋመ 135ዓመታትን ያስቆጠረው የአሜሪካ ሕግ ባለሙያዎች ማኅበር (ABA) እየተባለ በሚጠራውና 400 ሺህ በላይ አባላት ባሉት የህግ ባለሙያዎች ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት ንግግር እንዲያደርጉ በተጋበዙበት ወቅት አቶ ኦባንግ ሜቶ በርካታ ጉዳዮችን በማንሳት ድጋፍ ጠይቀው አዎንታዊ ምላሽ እንዳገኙ ጠቅሰዋል፡፡ በርካታ የህግ ባለሙያዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ ኢህአዴግ ህግን ከለላ በማድረግ በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ወንጀል፣ ለእንደዚህ ዓይነት ተግባሩ ማስፈጸሚያም የጸረ ሽብርተኝነትን፣ የመያዶችን፣ ወዘተ ህጎች በማውጣት ዜጎችን ለእስር፣ ለስደት፣ ለስቃይ መዳረጉን፣ የፍትህ አካላቱን ህግን በሚያከብሩና ፍትህ በሚያስፈጽሙ ሳይሆን ራሱ በመሠረተው ተቋም እያመረተ ለፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረገ መሆኑን፣ ከዚህ አልፎ ደግሞ በስደተኛነት ስም ደጋፊዎቹን ወደ ውጪ በመላክ በሃሰት የኢህአዴግ ሰለባ በማስመሰል በየምዕራቡ ዓለም የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ በማስደረግ መልሶ ስደተኛውን እዲሰልሉና ለሥርዓቱ እንዲሰሩ እያደረገ መሆኑን፣ ወዘተ በስፋት አብራርተዋል፡፡ የባለሙያዎቹ ማኅበር ጉዳዩን በጥልቀት እንደሚያየውና ያለውን ከፍተኛ የሰው ኃይል በመጠቀም ከአኢጋን ጋር እንደሚሰራ ከሌሎች ማኀበራት ጋር በመሆንም በተለይ በምዕራቡ ዓለም የተሰገሰጉትን አስመሳይ ስደተኞች ወደ ፍትህ የማምጣቱ ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ለአቶ ኦባንግና ለድርጅታቸው አረጋግጠዋል፡፡

Tuesday, 19 January 2016

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ተቋርጠው የነበሩት ከ80 በላይ የሚሆኑ ክሶች እንደገና እንዲታዩ ተወሰነባቸው

ኢሳት (ጥር 09 ፥ 2008)
ከመንግስት ጋር ያደረጉት ስምምነት ተከትሎ በቅርቡ ወደሃገር የተመለሱትና ከቀናት በፊት ለእስር የተዳረጉት የአክሰስ ሪል ስቴት መስራች የተቋረጡባቸው ከ 80 በላይ ክሶች እንደገና እንዲታዩ ተወሰነ።
የኩባንያው መስራችና አመራር አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ወደሃገር ከተመለሱ በኋላ ሊተገብሩ ቃል የገቡትን ስራ ባለማከናወናቸው ምክንያት ክሳቸው እንዲቀጥል መደረጉን የፍትህ ሚኒስቴር ገልጿል።
ከመንግስት ጋር ድርድር አድርገው ባለፈው አመት ወደሃገር ቤት የተመለሱት የአክሰስ ሪል ስቴት መስራች፣ ወደሃገር ሲመጡም ያለመታሰር ዋስትና አልተሰጣቸውም ነበር ሲሉ የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ መግለጻቸው ከሃገር ቤት የተገነው መረጃ አመልክቷል።
የገቡትን ቃል መፈጸም አልቻሉም የተባሉ አቶ ኤርሚያስ ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር መዋላቸው የሚስታወስ ሲሆን፣ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ እና የተቋረጡ ከ80 በላይ ክሶችም እንደገና የሚታዩ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
አክሰስ ሪል ስቴስ ከስድስት አመት በፊት ከሁለት ሺ በላይ ከሚሆኑ ደንበኞች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ወደስራ ቢገባም ለደንበኞቹ መኖሪያ ቤትን አላስረከበም በሚል ብውዝግብ ውስጥ መቆየቱ ይታወቃል። አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በበኩላቸው ቤቶቹን ሰርቶ ለማስረከብ የገጠማቸው መሰናክልም መግለጻቸው ይታወሳል።


በሆሳዕና ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት ማመላለሻ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ


ኢሳት (ጥር 09 ፥ 2008)
በሆሳዕና ከተማ ከመንጃ ፈቃድ ቅጣት እና አስተዳደር ብልሹነት ጋር በተያያዘ የህዝብ የትራስፖርት ማመላለሻ አገልግሎት ለሁለት ቀን ተቋርጦ መዋሉት ዛሬ ሰኞ ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመለከተ።
አንድ ሆሳዕና ወደሌላ ወረዳ ወይም ከወደ ዋና ዋና ከተሞች የሚያጓጉዙ የትራንስፖት መገናኛ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ህዝቡ ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ውስጥ ላይ እንደሆነ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ በሆሳዕና የሚኖሩ ሰው ለኢሳት በስልክ ተናግረዋል።
“መንግስት ያወጣው አዲሱ ህግ አንድ ሹፌር 3 ጊዜ አንድ አንድ ሺ ብር ከተቀጣ መንጃ ፈቃዱን ይነጠቃል የሚለው ነው አድማውን ያስነሳው” ያሉት አንድ አስተያየት ሰጪ፣ አድማውን ተላልፎ ከቡታጅራ ሆሳዕና ይጓዝ የነበረ አንድ ሃይሩፍ የትራስፖርት ተሽከርካሪም ወራቤ ላይ በትራንስፖርት አገልግሎት ሰራተኞች እና በህዝቡ እንደወደመ ተነግሯል።
አዲሱን የመንግስት መመሪያ በመቃወም የሆሳዕና፣ ጉራጌ  እና ወላይታ ዞኖች ባሉት ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎች በአድማው መሳተፋቸው ታውቋል።
የአካባቢው ህብረተሰብም ታምቀው የቆዩ የመልካም አስተደደር ችግሮችን እየገለጸ ያለበት አጋጣሚ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት አስታውቀዋል።
ትናንት እሁድና ዛሬ ሰኞ ከባጃጅ ጀምሮ ሁሉም የትራስፖርት አገልግሎቶች በመቋረጣቸው፣ ከከተማዋ የሚወጣም ሆነ የሚገባ ምንም አይነት የትራስፖርት አገልግሎት ተሽከርካሪ እንደሌለ ታውቋል።
ከአድማው ጋር በተያያዘ በሃድያ ዞን ማረሚያ ቤት 4 ሰዎች በመንግስት ሃይሎች መታሰራቸው ተነግሯል።
የመንግስት አዲሱን አሰራር በመቃወም ነገ ማክሰኞ በሆሳዕና ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ እንደተጠራ በአካባቢው የሚኖሩ ሰው ለኢሳት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ በህጻናት ላይ ከጦርነት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ጉዳት እያደረሰ ነው ተባለ


ኢሳት (ጥር 09 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የድርቅ አደጋ በህጻናት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ጦርነት በሶሪያ ህጻናት ላይ እያደረሰ ካለው አደጋ ጋር ተመሳሳይ እየሆነ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቁ።
ይኸው በስድስት ክልሎች ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋ ከ 400ሺ በላይ በሚሆኑ ህጻናት ላይ ክፉኛ የአካልና የጤና ችግርን እያስከተለ እንደሚገኝ ድርጅቱ ገልጿል።
ድርቁ በህጻናት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ጦርነት በሶሪያ ህጻናት ላይ እያደረሰ ካለው ጉዳት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናቱን ህይወት ለመታደግ አፋጣኝ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
በኢትዮጵያ ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋና በሶሪያ ቀጥሎ የሚገኘው ጦርነት በአለማችን ግንባር ቀደም የሰብዓዊ እርዳታን የሚፈልጉ አስቸኳይ ችግሮች ሆነው ተገኝተዋል ሲሉ የህጻናት አድን ድርጅት ተወካይ የሆኑት ካሮሊን ማይልስ ገልጸዋል።
ለዚሁ አፋጣኝ የነብስ አድን ስራም የህጻናት አድን ድርጅት ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚፈልግ ተወካዩ ይፋ ማድረጋቸውን ኒውስ 24 የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
ድርቁ ዱዳትን እያደረሰ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ዘገባን ያቀረበው አልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በበኩሉ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ለምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች በቂ እርዳታን እያገኙ እንዳልሆነ መግለጻቸውን አስነብቧል።
በድርቁ ሳቢያ ክፉኛ ጉዳት የደረሰባቸው እና የአስር ልጆች አባት የሆኑት ሞሃመድ ዱባሃላ ከነበራቸው 53 ላሞች መካከል አምስቱ ብቻ መትረፋቸውን ለቴለቪዥን ጣቢያው አስረድተዋል።
በተለይ ህጻናት ላይ እያደረሰ ባለው ጉዳት ሃዘን እንደተሰማቸው የገለጹት አርብቶ አደሩ ከመንግስት እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣዮቹ ሁለት ወራት በድርቁ ሳቢያ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልና የድርቁ ጉዳትም እየከፋ እንደሚሄድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳስቧል።

ኢትዮጵያ አልፋሽጋ የሚባለው ግዛት የሱዳን መሆኑን እንደምትቀበልና ለማስረክብ መቁረጧ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ

“የሱዳን መሬት በኢትዮጵያ መያዙን የኢትዮጵያ መንግስት አምኖአል” ሲሉ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጹ
ጥር ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዱር ለአልጀዚራ እንደተናገሩት “ኢትዮጵያ አልፋሽጋ የሚባለው ግዛት የሱዳን መሆኑን እንደምትቀበልና ለማስረክብ መቁረጧን” ተናገሩ።
ለሱዳን ይሰጣል የተባለው መሬት 250 ካሬ ኪሎሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ ለም የሆነ መሬትና በርካታ የውሃ ተፋሰሶች ያሉት ነው።
...
የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያ አርሶአደሮች መሬቱን ሰጥቷቸው ሲያርሱት ነበር ያሉት ባለስልጣኑ፣በዚህ አመት ውስጥ መሬቱን ኢትዮጵያ ለሱዳን ልታስረክብ መሆኑን ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ንግግር፣ አቶ ሃይልማርያም ደሳለኝ በቅርቡ የሰጡትን መግለጫ የሚያጠናክር ነው። አቶ ሃይለማርያም የኢትዮጵያ ባለሃብቶችና አርሶአደሮች ወደ ሱዳን ገብተው እያረሱ መሆኑንና የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳንን መንግስት ለምኖ እስካሁን በቦታው ላይ እንዲቆዩ ማድረጉን ተናግረው ነበር።
የሱዳን መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰጡት መግለጫ ከኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስትር ጋር መመሳሰሉ የተጠቀሰው መሬት ለሱዳን እንደሚሰጥ ማረጋገጫ ነው። በድንበሩ አካባቢ ያሉ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች ግን መሬቱ የኢትዮጵያ መሆኑን ይናገራሉ።
የኢህአዴግ መንግስት መሬቱ የሱዳን መሆኑን አምኖ ከተቀበለ ቀሪው ነገር አለማቀፋዊ ህጋዊነትን ማላበስ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ ሁለቱም መንግስታት ተስማምተው ስምምነታቸው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከገለጡ፣ መሬቱን መልሶ ለማግኘት ጉዳዩን ውስብስብ ሊያደርገው ይችላል።
የመንግስት ቃለአቀባይ ጌታቸው ረዳ እና ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የድንበር ጉዳይን ለማየት የተቋቋመ ኮሚቴ እንደሌለ፣ መሬት ለመስጠት ምንም ዝግጅት እንደሌለ ሲገልጹ ቆይተዋል። ይሁን እንጅ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሪዎች ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። የኮሚቴው ሰብሳቢ አብደላ አል ሳድቅ ኮሚቴው ስራውን ያለምንም ችግር እያከናወነ መሆኑን ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ላለፉት ሁለት ወራት የደህንነት መስሪያ ቤት (ኢንሳ) መሬቱን የአየር ላይ ፎቶ ሲያነሳ ከርሟል። የአካባቢው ነዋሪዎች ለሚያነሱት ጥያቄ የደህንነት መስሪያ ቤቱ “የመሬቱ ልኬቱ የሚካሄደው ለልማት የሚውለውን መሬት ለመለየት ነው” የሚል መልስ ሲሰጥ ቆይቷል። የደህንነት መስሪያ ቤቱ መሬቱን የማስረከብ ሃላፊነት መውሰዱን ምንጮች ገልጸዋል።

Tuesday, 12 January 2016

የኖርዌይ ኤምባሲ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በማገርሸቱ ዜጎች የጥንቃቄ እርምጃን እንዲወስዱ አሳሰበ

ኢሳት (ጥር 3 ፥ 2008) መቀመጫውን በኢትዮጵያ ያደረገ የኖርዌይ ኤምባሲ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ዳግም በማገርሸቱ ምክንያት ዜጎች በክልሉ በሚያድርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ እርምጃን እንዲወስዱ አሳስቧል። የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በቅርበት የምትከታተለው ኖርዌይ እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ የጸጥታ ስጋት ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት በቅርቡ ለኤምባሲ ተወካዮች በሰጡት ማብራሪያ ተቃውሞው በቁጥጥር ስር ዉሏል ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል። ይሁንና በሁለቱ ወገኖች መካከል የተካሄደው ውይይት ተከትሎ ኖርዌይ ተቃውሞው አለመብረዱንና የጸጥታ ስጋት እየሆነ መምጣቱን በይፋ ስትገልጽ የመጀመሪያ ሃገር ሆናለች። መቀመጫቸውን በሃገሪቱ ያደረጉ የተለያዩ ሃገራት ተወካዮችና አለም አቀፍ ድርጅቶች በወቅታዊው የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ የተናጥል ምክክርን እያካሄዱ እንደሚገኝም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።