Tuesday, 9 December 2014

በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት እናወግዛለን !!!
በአብዛኛው በወጣት ወንዶችና ሴቶች የተገነባው ሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነበት የዘጠኝ ፓርቲዎች ኅበረት፣ “ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” የተሰኘ የአንድ ወር መርሀ ግብር አውጥቶ፤ ችግሮችን ተጋፍጦ አብዛኛውን ተግባራዊ አድርጓል። የመርሀ ግብሩ አቢይ አካል የነበረውና በህዳር 27 እና 28 ሊከናወን ታድቆ የነበረው የ24 ሰዓት የአደባባይ ተቃውሞ ግን በአገዛዙ የኃይል እርምጃ ምክንያት በታቀደው መንገድ ሊከናውን አልቻለም። የህወሓት ቅልብ የሆኑት ሲቪል የለበሱ ሰላዮችና የፌደራል ፓሊስ በተቃውሞው ተሳታፊዎች ላይ ኢሰብዓዊ የሆነ ጥቃት ፈጽመዋል።
ከጅምሩ፣ የፓርቲዎቹ ኅበረት የተቃውሞ ማሳወቂያ ደብዳቤውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለማስገባት የገጠመው ችግር የህወሓት አገዛዝ የመንግሥትን መዋቅር ለፓ...ርቲ ሥራ፤ የመንግሥት ተቀጣሪዎችን ደግሞ እንደ ህወሓት አገልጋዮች የሚጠቀምባቸው መሆኑ አንዱ ማሳያ ሆኗል። ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርጉ ማሳወቅ የፈለጉት ፓርቲዎች ህወሓት የዘረጋውን አፋኝ ሥርዓት የሚታገሉ በመሆናቸው ብቻ ደብዳቤዓቸውን የሚቀበል እንኳን አጥተው ተጉላልተዋል። ለሰልፉ ቅስቀሳ ማድረግም በራሱ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ወጣቶች ተንገላተዋል፣ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል። ያም ሆኖ ውጣ ውረዶች ታልፈው ቅዳሜ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ. ም. ደረሰ።
የኅበረቱ አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና ጥሪውን የሰማ ሕዝብ ወደ መስቀል አደባባይ ማምራት ሲጀምር ሲቪል የለበሱ የአገዛዙ ታጣቂዎች እና ፌደራል ፓሊሶች ከሰንደቅ ዓላማዎችና መፈክሮች ባለፈ አንዳች ነገር ያልያዙትን እድሜያቸው ከሃያዎች ያልዘለሉ ውድ የኢትዮጵያ ልጆችን ደብድበዋል፤ ብዙዎቹም አፍነው በአሰቃቂ ሁኔታ እያንገላቱ ወደ እስር ቤቶች ወስደዋል። ወጣቶች ተወልደው ባደጉበት አገር፤ ስሜታቸውን በነፃነት ለመግለጽ በመድፈራቸው ብቻ በጭካኔ ተረግጠዋል፤ ተፈንክተዋል፤ እጅና እግሮቻቸው ተሰብሯል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህ የህወሓትን ፋሺስታዊ እርምጃ አጥብቆ ይቃወማል። ግንቦት 7፣ ህወሓት ከስልጣን እስካልተወገደ ድረስ እንዲህ ዓይነቱን ፋሺስታዊ ተግባር መፈፀሙን የማይተው እኩይ ኃይል እንደሆነ ያውቃል፤ በዚህም ምክንያት የትግላችን ግብ ህወሓትን ማስወገድና በምትኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ ያገኘ መንግሥት መመሥረት መሆን ይኖርበታል ብሎ ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል።
ግንቦት 7፣ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. “መብቶቻችንን በህወሓት ዘረኛ አምባገነኖች አናስነጥቅም” በማለት አደባባይ የወጡ ወጣቶችን ጽናት ያደንቃል። ህወሓት የሚለውን ሳይሆን የይስሙላ ህጉ የፈቀደላቸውን ለማድረግ በመድፈራቸው በህወሓት የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የሚደረገውን ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት አራምደውታል።
እያንዳንዱ የፓለቲካ ድርጅት ከዚህ ኩነት የሚወስዳቸው ተጨማሪ ትምህርቶች ቢኖሩም የሚከተሉትን ነጥቦች ብዙዎችን ያስማማሉ ብለን እናምናለን።
1. ህወሓት በምንም ዓይነት ቢሆን የያዘውን ስልጣን ለሕዝብ ፈቃድ ማስገዛት አይፈልግም፤
2. ህወሓት አገራችን ወደ ትርምስ እየገፋት እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፤
3. ስልጣኑን የሚያሳጣው ከመሰለው እና አቅሙ እስካለው ድረስ ዘግናኝ እርምጃዎችን ከመውሰድ አይመለስም፤
ከህወሓት አገዛዝ መገላገል የሚቻለው ተገዶ ሲወገድ ብቻ ነው። ህወሓት እንዲወገድ ደግሞ የመጨቆኛ አቅሙ መዳከም ይኖርበታል። ህወሓትን የማስወገጃ አማራጭ መንገዶች ብዙ ሲሆኑ ተቀናጅተው ቢሠሩ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ ብለን እናምናለን፤ “ሁለገብ ትግል” የምንለው የትግል ስልት ጭብጥ ይህ ነው። “እምቢ ለነፃነቴ” ብሎ የተነሳ ሕዝብ ህወሓትን ምን ያህል እንደሚያስደነግጥ በተደጋጋሚ ታይቷል። ህዳር 27ን መንደርደሪያ አድርገን በመውሰድ ከዚህ በተሻለ ለተደራጀ ሕዝባዊ እምቢተኝነትና አመጽ ራሳችን እናዘጋጅ።
በዚህ አጋጣሚ ግንቦት 7፣ ለመከላከያ ሠራዊት እና ፓሊስ አባላት ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ማድረግ ይሻል። የመከላከያ ሠራዊት እና ፓሊስ አባላት እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ በህወሓት ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ የተበደላችሁ መሆኑን እናውቃለን። የህወሓት ሹማምንት ከሆኑ አዛዦቻችሁ መላቀቅና ራሳችሁን ነፃ የማውጣት ኃላፊነት የወደቀው በእናንተው በራሳችሁ ላይ ነው። ሠራዊቱ ራሱን በራሱ ነፃ ማውጣት ይኖርበታል። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ህወሓት መወገዱ የማይቀር በመሆኑ ሠራዊቱ ራሱን ነፃ አውጥቶ ከሕዝብ ጋር ካልወገደ እጣ ፈንታው የተሸነፈ ሠራዊት መሆን ነው። ከዚህ በላይ የሠራዊቱ አባል እየደበደበ ያለው የራሱን ልጅ፣ ወንድሙን ወይም እህቱን እንደሆነ ይወቅ። ይህ ወሳኝ ጊዜ ነው እያንዳንዱ የሠራዊቱ አባል በግል ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ሊሰማው ይገባል።
በሁሉም ዓይነት የትግል ዘርፎች የኢትዮጵያ ወጣቶች በስፋት እየተቀላቀሉ መሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው። ጊዜው የለውጥ ነው። የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተደጋግፈው እንዲሄዱ መደረግ ያለበት ወቅት ላይ ነን። በህዳር 27 ቀን በህወሓት ቅልብ ሰላዮችና የፌደራል ፓሊሶች አማካይነት የደረሰው ጉዳትና የፈሰሰው ደም ለፍትህና ለነፃነት የተከፈለ ዋጋ ነው። ህመማችሁ ህመማችን፤ ትግላችሁ ትግላችን ነው። የተለያዩ መንገዶች ወደ ነፃነት አደባባይ እያመሩ ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

Monday, 8 December 2014

መሪዎች ቢታሰሩም ትግሉ እንደማይቆም የ 9 ፓርቲዎች ትብብር አመራሮች አስታወቁ

-የምርጫ ስርዓት ለውጥ እንዲደረግ ለመጠየቅ ህዳር 27 ቀን የአዳር ተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ወደ አደባባይ በወጡት 9 የተቃዋሚ ድርጅት አመራሮች ላይ የፌደራል ፖሊስ አባላት ድብደባ በመፈጸም ወደ እስር ቤት ቢወስዱዋቸውም፣ የትብብሩ አመራሮች ግን ትግሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ኢትዮጵያውያን ለትግሉ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ሶስተኛ እየተባለ በሚጠራው እስር ቤት ውስጥ ታስረው የሚገኙት የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣  አቶ ኤርጫፎ ኤርዳሎ፣ አለሳ መንገሻና ሌሎችም አመራሮች አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፣ በጨርቆስ ታስረው የሚገኙት እነ አቶ ግርማ በቀለ ደግሞ የ7 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።
አመራሮቹ ሀግመንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድና የተከለከለ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ወንጀል መከሰሳቸውን ታውቋል።
በፍርድ ቤት አካባቢ ሆነው ጉዳዩን ከተከታተሉት መካከል ናትናኤል ያለምዘውድ ለኢሳት ሲናገር፣ አብዛኞቹ አመራሮች ሲሄዱ ያነክሱ እንደነበር ገልጾ፣ ኢ/ር ይልቃል እጁ አካባቢ መመታቱን፣ ብርሃኑ ተክለያሬድ ደግሞ እጅና እግሩ አካባቢ በጨርቅ ተጠቅሎ ማየቱን ገልጿል። ሴት እስረኞችም ሲጓዙ ያነክሱ እንደነበር በተለይ አንደኛዋ ኩላሊቷ አካባቢ መመታቱዋን እንደገለጸችለት ተናግሯል ሴት እስረኞችን ለመጠየቅ በሄደበት ወቅት ለአጭር ደቂቃዎች ራቅ ብሎ ለማናገር መቻሉን የገለጸው ዮሴፍ ተሻገር በበኩሉ፣ ሴቶች በጠንካራ መንፈስ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
ኮተቤ አካባቢ ታስረው ስለሚገኙት የድርጅት መሪዎችና አባላት ጉዳይ በስፍራው በመገኘት ለመታዘብ የቻለው አቶ እምላሉ ፍሰሃ እንደገለጸው ደግሞ ምንም እንኳ እስረኞቹ መጸዳጃ ቤት አካባቢ በመታሰራቸው እንዲሰቃዩ ቢደርግም አሁንም በጠንካራ መንፈስ ላይ መሆናቸውን ገልጿል።
መንግስት የወሰደው እርምጃ በትብብሩ የወደፊት የትግል አካሄድ ላይ ተጽአኖ ይኖረው እንደሆን የተጠየቁት የመኢዴፓ ሊቀመንበርና የትብብሩ ገንዘብ ያዥ አቶ ኑሪ ሙዲሰር ሲመልሱ ” መንግስት እስረኞች ይፈቱ አይፈቱ ወደ ሚል አታካራ እንድንገባ ቢፈልግም፣ እኛ ግን ትግሉን ወደ ፊት ከመግፋት ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም” ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለትግሉ አስፈላጊውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አቶ ኑሪ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ አንድነት ፓርቲ በ9 ፓርቲዎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ አውግዟል። ፓርቲው ባወጣው መግለጫ  ” የዘጠኙ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን ሰላማዊ ሰልፍ የማድርግ መብት ከመጠቀም ውጪ ያጠፉት ምንም ዓይነት ነገር ስለሌለ በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል።” ብሎአል።  ፓርቲው ” የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ህገወጥና አረመኔያዊ ድርጊት በዝምታ ሊያልፈው አይገባም፤ ኢህአዴግን በቃህ ሊለው ይግባል።” በማለት በመግለጫው አስታውሷል።

እነ ግርማ በቀለና ጌታነህ ባልቻ መስቀል አደባባይ ላይ ንብረት አውድመዋል ተብለው ተከሰሱ

እነ ግርማ በቀለና ጌታነህ ባልቻ መስቀል አደባባይ ላይ ንብረት አውድመዋል ተብለው ተከሰሱ
ለአዳር ሰላማዊ ሰልፉ መስቀል አደባባይ ተይዘው ጨርቆስ ፖፖላሬ ታስረው የሚገኙት የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ፀኃፊ አቶ ግርማ በቀለ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የጥናትና እስትራቴጅ ክፍል ኃላፊ ጌታነህ ባልቻን ጨምሮ 27 ያህል የትብብሩ አመራሮች፣ አባላትና የሰልፉ ተሳታፊዎች ዛሬ ህዳር 29/2007 ዓ.ም ጨርቆስ አካባቢ የሚገኝ ፍርድ ቤት ቀርበው ‹‹መስቀል አደባባይ ላይ ንብረት አውድመዋል፡፡›› በሚል ተከሰዋል፡፡
ፖሊስ ‹‹ታሳሪዎቹ መስቀል አደባባይ ላይ ንብረት አውድመዋል፣ የጠፉ ንብረቶችና ያልተያዙ ግብረአበሮቻቻው ስላሉ ለምርመራ 14 ቀን ይሰጠኝ›› ሲል ጠይቋል፡፡ ታሳሪዎቹ በበኩላቸው ‹‹እኛ መስቀል አደባባይ ላይ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳንጀምር ነው የታሰርነው፣ ምንም ...ያወደምነውም ሆነ የወሰድነው ንብረት የለም፡፡›› ሲሉ የፖሊስን ክስ አጣጥለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በህጋዊ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በሚዘጋጁበት ወቅት መያዛቸውን በመግለጽ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ ሆኖም ዳኛው የ7 ቀን ቀጠሮ አስተላልፈውባቸዋል፡፡
በተመሳሳይ በዛሬው ዕለት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው የ14 ቀን ቀነ ቀጠሮ የተሰጠባቸውና በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙት ታሳሪዎች በደረሰባቸው ድብደባ ምክንያት ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡ ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱት መካከል ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት፣ እየሩስ ተስፋው፣ ጋዜጠናኛ በላይ፣ አቤል ኤፍሬም፣ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ስሟ ያልተጠቀሰች አንዲት ሴትና ሌሎች በርካታ ወንዶች እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ ሶስተኛ ከሚገኙት ታሳሪዎች መካከል ከሴቶቹ ንግስት ወንዲፍራውና ምኞቴ መኮንን ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው እና አብዛኛዎቹ ወንዶች ለየብቻቸው ጨለማና ቀዝቃዛ ቤት ውስጥ እንደታሰሩ ተገልጾአል፡፡

70 ኢትዮጵያውያን ቀይ ባህር ላይ ሰጥመው መሞታቸውን የየመን ባለስልጣናት ገልጸዋል

ስደትን የህይወታቸው የመጨረሻ አማራጭ በማድረግ በጅቡቲ በኩል አድርገው ወደ የመን ለመግባት የሞከሩ 70 ኢትዮጵያውያን ቀይ ባህር ላይ ሰጥመው መሞታቸውን የየመን ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ታይዝ በምትባለዋ ግዛት የሚገኙ ባለስልጣናት ለአሶሴትድ ፕሬስ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያውያኑን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረችው ጀልባ ባጋጠማት ከባድ አውሎ ንፋስና ማእበል አል ማክታ እየተባለ ከሚጠራው ወደብ ራቅ ብሎ ለመስመጥ ተገዳለች። ባለስልጣናቱ እንዳሉት ጀልባዋ 70 ኢትዮጵያውያንን ጭና የነበረ ሲሆን በደጋው ሁሉም ኢትዮጵያውያን አልቀዋል።
የመን የሚገኘው ጋዜጠኛ ግሩም ተክለሃይማኖት በበኩሉ በጀልባዋ ላይ የነበሩት 81 ሰዎች ሲሆኑ፣ 71 ኢትዮጵያውያንና 9 ሶማሊያዎች አልቀዋል። አይ ኦ ኤም የተባለው የስደተኞች ድርጅት አስከሬን ለመሰብሰብ ሙከራ ቢደረግም እስካሁን ምን ያክል አስከሬን እንደተሰበሰበ ለማወቅ አለመቻሉን ገልጿል....

Wednesday, 26 November 2014


የታሰሩ ዜጎች አሸባሪዎች ስለነበሩ አልነበረም፡፡የፖለቲካ ጨዋታው ሌላ በመሆኑ ምክንያት የዚህን ሁሉ ህዝብና ባለሙያ ጩኽት ኢህአዴግ ከምንም ሳይቆጥር የዚህን አዋጅ ወደ ሚሞግቱት ፊቱን በማዞር ሲቃወሙ የነበሩ ግለሰቦችንና ተቋማት ላይ በጠራራ ጸሀይ የወሰደው እርምጃ በእርግጥም ትክክል እንደነበሩ አረጋግጧል፡፡የፀረሽብር አዋጁ በፀደቀ ማግስት የያኔው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የመንግስታቸውን ሪፖርት ለማቅረብ ፓርላማ ተገኝተው ስለአዋጁ ካብራሩ በኋላ ከምክር ቤቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስን ሰጥተው እብዳጠናቀቁ ለአንድነት ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ‹‹ዋ ዋጋ ትከፍላላችሁ በማለት በፓርቲው አመራርና አባላት ላይ ሽብር አወጁ ››ያኔ ይህንን ማስፈራሪያቸውን በቃላት ብቻ ገድበውት አላለፉም፡፡አንዴ ሰይፋቸውን መዘዋልና ፓርተአቸው አስቀድሞ ጣት የቀሰረባቸውን እስር ቂምና ቁርሾ የተያዘባቸው በርካታ ትንታግ ፖለቲከኞችን፤ጋዜጠኞችን ለሀገራቸው ተስፋን የሰነቁ ኮኮብ ልጆችን በአዋጁ ጎራዴ ሰየፉት ፡፡ከእነዚህ ሰለባዎች ውስጥ በትህትናው ፡በፀባዩና በምግባሩ እንዲሁም በአካዳሚክ እውቀቱ የሚታወቀው ወጣቱ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አንዷለም አራጌ ፤የአንድነት ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል ወጣቱ ፖለቲከኛ ናትናኤል መኮንን፤መምህር አሳምነው ብርሀኑ፤አንጋፋው የፕሬስ ተሟጋችና አለማቀፍ የፖለቲካ ተንታኝ ጎልማሳው እስክንድር ነጋ ፤የኦፌዴን ምክትል ለቀመንበርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር በቀለ ገርና የኦህኮ አመራር አባል የነበሩት አቶ ኦልባና ሌሊሳን እነደምሳሌ መጥቀስ የሚቻሉ የፀረሽብር አዋጁ ሰለባዎች ናቸው፡፡

Tuesday, 18 November 2014

ታሪካችን የደብተራ ነው አላችሁኝ?
በፋሲል የኔያለም (የኢሳት ጋዜጠኛ)
ከዋልን ካደርን ገና ብዙ ጉድ እንሰማለን። የኢትዮጵያን ታሪክ ማጠልሸት ሰሞኑን እንደ ወረርሽኝ ሆኗል። የኢትጵያን ታሪክ የደብተራ ተረት ነው ብሎ ማጣጣል፣ ደብተራን ከአማራ ጋር ብቻ ማያያዝ ያለማወቅ በሽታ ካልሆነ ምን ይባላል? አለማወቅን ማወቅ ጤና፣ አለማወቅን አለማወቅ ደግሞ በሽታ ነው።
...
ደብተራ ያየውን የሰማውን በከተበ ለምን ይንቋሸሻል? የደብተራ ጥፋቱ አስቀድሞ መሰለጠኑ ነው፤ ፊደል የስልጣኔ በር ነው፤ ደብተራ ደግሞ ፊደል የቆጠረ የመጀመሪያ ሰው ነው፤ የኢትዮጵያ ደብተሮች በጊዜያቸው ከነበሩት ሰዎች አስቀድመው የሰለጠኑ ናቸው፤ ስልጣኔውን ያገኙትም በፊደል በኩል ነው። አስቀድመው በመሰልጠናቸውም፣ ለሁላችንም የሚሆን ነገር ጽፈው አለፉ። ባይሰለጥኑ ኖሮ ታሪክን ለመጪው ትውልድ ስለማስተላለፍ አይጨነቁም ነበር። ከደብተራ ውጭ ታሪክን ለመጪው ትውልድ ጽፎ ስለማስቀረት ያሰበ ማን ነው? ተራው ገበሬ ዝናብ መጣ ሄደ፣ ተራው ነጋዴ አሞሌ ተወደደ ረከሰ፣ ተራው ወታደር ድንበር ሰፋ ጠበበ፣ ንጉስ ግብር ጨመረ ቀነሰ ከማለት ውጭ ታሪክ ጽፎ ስለማስተላለፍ ተጨንቆ ያውቃል? ስለጥበብ ስለውበት ተጨንቆ የጻፈውም ደብተራው ነው።
ደብተራ ባየው በሰማው፣ የጆግራፊ እውቀቱ፣ የእግሩ ጥንካሬ፣ የቀለም አቀባበሉና እድሜው በፈቀደለት መጠን ጻፈ። ሲጽፍ ይጨምራል፣ ይቀንሳል። የጨመረውን የቀነሰውን ማስተካከል ከደብተራ የተሻለ እውቀት ያገኘው የሁዋለኛው ትውልድ ሃላፊነት ነው። ታዲያ እንዲህ ሲባል ደብተራን በማድነቅ እንጅ በማንቋሸሽ አይጀመርም። ኒውተን ጋሊሊዮን አንቋሾ ጥናት አልጀመረም፣ አንስታይን ኒውተንን አንቋሾ አልተነሳም። የኛ ዘመንኛ ጻፊዎች ደግሞ የሁዋላውን አንቋሾ መጀመር እውቀት ይመስላቸዋል። ጽሁፋቸውም በውሃ ላይ እንደበቀለ ተክል የሚሆነው ለዚህ ነው፣ ስር አልባ ነው፤ እፍ ቢሉት እንደ ላባ በኖ ይጠፋል።
አሁን ደብተራ ባይጽፍ ኖሮ ታሪካችን የሰሃራ በታች ካሉት አገራት ይለይ ነበር?። ከሰራሃ በታች ካሉ አገራት በራሱ ቋንቋ ታሪኩን ጽፎ ያስቀረ ከእኛዋ ኢትዮጵያ ውጭ ሌላ አለ? አብዛኛው የጥቁሩ የአፍሪካ ታሪክ የተጻፈው በቅኝ ግዛት ጊዜ አይደለምን? ፈረንጆቹ ለእነሱ በሚጥማቸው መንገድ አይደለም የከተቡት? ምንጫቸውስ ምንድነው? ህንጻዎች እና ቁሳቁሶች አይደሉም? ታዲያ ደብተራ ታሪክ ጽፎ ባስቀረ፣ ድንጋይና ቁሳቁስ ከመፈለግ ባዳነ ለምን ይሰደብ?
ደብተራ ታሪክ የሚጽፈውስ በእኛ አገር ብቻ ነው? የአውሮፓ የጥንት ታሪክ በማን ተጻፈና ነው? የአውሮፓ የታሪክ ወመዘክር ካቶሊክ ቤ/ክ አይደለችም? ስኮላስቲስዝም የሚባለው ታላላቅ ምሁራን የወጡበት የትምህርት ስርዓት የሚመራው በደብተሮች አልነበረምን? የአውሮፓን ታሪክ ከደብተራ ታሪክ መነጠል ይቻላል? የፈረንጅን ደብተራ አቆለጳጵሰን የሃበሻን ደብተራ የምናዋርድበት ምክንያቱ ምን ይሆን? አውሮፓ ውስጥ በኢራስመስ ስም ስኮላርሽፕ የምትመጣው ኢራስመስ ማን ሆነና ነው? የፈረንጅ ደብተራ አይደለም?
ከአገራችን ደብተራ ብንማር ኖሮ ዛሬ እንደ አውሮፓውያን 6 ቢሊዮን ኪሜትር የሚጓዝ መንኮራኩር እናመጥቅ ነበር። ኮፐርኪነከስና ጋሊሊዮ ማን ናቸው? ደብተሮች አይደሉም? የሰማይን ምስጢር ለማወቅ ሰማይ ሲያንጋጥጡ በመኖራቸው የኸው ለዛሬው አስደማሚ የህዋ ምርምር በር ከፈቱ። የእኛዎቹ ደብተሮች ስለአስትሮሎጂ ምርጥ የሆነ እውቀት ቢያከማቹም አጣጥለነው በዘመናዊ መንገድ ሳንማረው ቀረን፤ የማጣጣላችን ውጤትም ፈረንጅ ወደ ላይ ሲመጥቅ እኛ መሬት መሬት እያየን ተቀብረን ቀረን። ዛሬ በየጋዜጣው ጀርባ የምታነበው ሆሮስኮፕ፣ የእኛ ደብተሮች ከዘመናት በፊት ኮከብ ቆጠራ እያሉ ሲያሰሉት የነበረ ነው። ፈርንጅ የተለየ ስም ስለሰጠው እንጅ ስራውና ይዘቱ ያው ነው። ልጅ እያለሁ አንድ ደብተራ ስለ ኮከብ ቆጠራ እና ስለጨረቃ አወጣጥ ቀመር አስተምረውኝ ነበር፤ የደብተራ ትምህርት ዳቦ አያበላም ብየ ሳልገፋበት ቀረሁ። የአገራችን ደብተሮች እምቅ እውቀት ቢኖራቸውም እያጣጣልነው ሳንጠቀምበት ቀረን።
ደብተራ ማለት ፊደል የገደለ ከሆነ ታሪኩን ጽፎ ያስቀረ ስንት የእስላም ደብተራስ አለ? በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ወደ አማርኛ የተተረጎሙ የሃይማኖት መጽሃፍት በአረብ ደብተራ የተጻፉ ናቸው። ደብተራንስ ማነው አማራ ብቻ ያደረገው? የትግሬ ደብተራም ሞልቷል።
ለታሪካችን የምንሰጠው ዝቅተኛ ቦታ ገና ዋጋ ያስከፍለናል፤ ታሪክ አልባነት የሚፈጥረውን ስሜት ለማወቅ ወደ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ሂዱና እዩት። በ20ኛ ክፍለዘመን መግቢያ ፈረንሳይ ውስጥ እነ ሴዳር ሴንጎር ያቋቋሙት ኔግሪቲውድ የሚባል እንቅስቃሴ ነበር። ኔግሪቲውድ የተመሰረተው ፈረንሳይ ጥቁር አፍሪካውያንን ፓሪዛውያን አደርጋለሁ ብላ ወደ ፈረንሳይ ሰብስባ ካመጣቻቸው በሁዋላ ነው። ጥቁር አፍሪካዊያኑ ፈረንሳይ ከመጡ በሁዋላ ሲያዩት ባዶነት ተሰማቸው፣ የሚወራው ታሪክ ታሪካቸው አልመስል አላቸው፤ ታሪካቸውንና ባህላቸውን ፈልጎ ለማግኘት ተነሳሱ፤ ኔግሪቲውድን ፈጠሩ። ያን ጊዜ የነበሩ ጻሃፎች ሁኔታውን ታቡላ ራሳ (tabular rasa) ብለው ይገልጹት ነበር። በግርድፍ ትርጉሙ፣ ባዶ ሰሌዳ ማለት ነው፤ አዎ የመጡበትን ታሪክ አለማወቅ ጭንቅላትን ጥቁር ሰሌዳ ያደርጋል፤ ጭንቅላትህ ጥቁር ሰሌዳ ከሆነ ደግሞ ነጭ ጠመኔ ( ቾክ) እንደፈለገ ይጽፍብሃል። ያን ጊዜ የምታነበንበው ነጩ ቾክ የጻፈልህን ይሆናል። ራስን ለባርነት አሳልፎ መስጠት ይሉሃል ( ይሉሻል) ይህ ነው።

Thursday, 30 October 2014



ሃብታሙ አያሌው ቶርቸር እየተደረገ ነው !
ክስ ሳይመሰረትበት ለአራት ወራት በማእከላዊ እስር ቤት የሚገኘው የአንድነት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ወጣት ሃብታሙ አያሌው፣ ከፍተኛ ኢሰብአዊ ግፍ እየተፈጸመበት እንደሆነ ታወቀ። “ወደ ፖለቲካው የማትመለስ ...ከሆነ ትወጣለህ። አለበለዚያ እዚሁ ነው የምትሞተው” በማለት አማራጭ ቢያቀርቡለትም፣ ሃብታሙ መሞትን እመርጣለሁ የሚል መልስ የሰጣቸው ሲሆን፣ እየደረሰበት ባለው ስቃይ በጣም እየታመመ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
“እስኪ ትግሉን እናስቀጥላለን የሚሉ ሰዎች ያድኑህ ? “ ሲሉ አሳሪዎቹ በስቃዩ የሚደሰቱ ሲሆን፣ ከባለቤቱ በስትቀር ጠበቃዉም ሁሉ ሳይቀር እንዳያየው ተደርጓል። በተመሳሳይ ሁኔታ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአንድነት የድርጅት ጉዳይ ም/ሃላፊ ፣ በታፈነና አየር በማያስወጣ ክፍል ዉስጥ እንዲታሰር በመደረጉ በተደጋጋሚ ለተቅማጥና ተያያዥ በሽታ መጋለጡን፣ እንዲሁም የመተንፈስ ችግር እንዳለበት ለማወቅ ችለናል።
“የፓርቲያችሁ የገንዘብ ምንጭ ምንድን ነው ? አንድነት ዉስጥ ያሉ ጠንካራ አባላት እነማን ናቸው ? “ በሚል ጥያቄ የቀረበለት ዳንኤል ሺበሺ፣ ክብሩን በሚነካ መልኩ እንደሚሰደብም የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ሃብታሙ አያሌው ፣ በእርሱ ላይ እይደረሰ ያለው ግፍ በማንም ዜጋ ላይ መድረስ እንደሌለበት በመግልጽ “የግፈኛው አገዛዝ እንዲያበቃ የኢትዮጵያ ሕዝብ መነሳት አለበት” ሲልም ለህዝቡ የትግል ጥሪ አስተላልፏል
የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ለ 90 ቀናት በተከታታይ በወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና የመረጃ እና ደህንነት ትምህርቶች ያሰለጠናቸውን ታጋዮች ጥሪ የተደረገላቸው እን...ግዶች እና የተለያዩ የተቃዋሚ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ ባስመረቀበት ወቅት የህዝባዊ ሃይሉ ስልጠና በግንቦት ሰባት ስም ከሚደረጉት ስልጠናዎች የመጨረሻው መሆኑ ተመልክቷል።
ህዝባዊ ሃይሉ ለኢሳት በላከው መግለጫ የህዝባዊ ሃይሉ ዋና አዛዥ ኮማንደር አሰፋ ማሩ ‘’ህዝባዊ ሃይላችን በኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋውን ዘረኛና አፋኝ የወያኔ ስርዓት ከህዝብ እና ከሃገራችን ጫንቃ ላይ አስወግዶ በምትኩ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ከተመሰረተ ጀምሮ ባለፉት ጊዚያት በርካታ ስራዎችን በመስራት አስተማማኝ ድርጅታዊ አቋም ላይ ይገኛል’’ ማለታቸውን ጠቅሷል።
የኢትዮጲያ ህዝብ አርበኞች ግንባር፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ እና የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ተዋህደው ባንድ ድርጅት ጥላ ስር ትግላቸውን አስተባብረው ለመታገል የሚያደርጉትን የውህደት ሂደት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ባደረሱበት ወቅት ላይ መርቃቱ መደረጉን ያወደሱት ኮማንደሩ፣ የህዝባዊ ሃይሉ ስልጠና በግንቦት ሰባት ስም ከሚደረጉት ስልጠናዎች የመጨረሻው እንደሚሆንም ተናግረዋል።
ኮማንደሩ ‘’ስልጠና ለአንድ ታጋይ የትግሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲሆን በስልጠና ላይ ያገኛችሁትን ትምህርት በተግባር ለቆምንለት ዓላማ እና ተልዕኮ በቁርጠኝነት እንደምታውሉት ሙሉ እምነቴን እገልጻለሁ‘’ በማለት ለስልጠናው መሳካት የተለያዩ ድጋፎችን ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል ከዚህ ቀደም 4 ተከታታይ ምርቃቶችን ማካሄዱ ይታወሳል።