Wednesday, 9 December 2015

ወያኔ በራሱ ወጥመድ -ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም

ኅዳር 2008
ራስን ሳያታልሉ ሌላውን ማታለል አይቻልም፤ ለራስ ካልዋሹ ለሌላ ሰው መዋሸት አይቻልም፤ ዞሮ ዞሮ ወደቤት እንደሚባለው ዞሮ ዞሮ ማታለልም ሆነ ውሸት ማደሪያ ሲያጡ ወደቤታቸው ይመለሳሉ፤ ያኔ ፈጣሪና ፍጡር ይፋጠጣሉ፤ ፍጡር የማታለያ ልብሱን አውልቆ በዓለም ፊት ራቁቱን ይቆማል፤ በከመረው ውሸት መጠን ነቀፌታ ተሸክሞ ያቃስታል፡፡

የታወሩት ዓይኖቹ ይከፈቱና ሕይወት ነጠላ አለመሆኑን፣ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ውጣ-ውረድ መኖሩን፣ ጥላቻና ፍቅር፣ ጤንነትና ሕመም፣ ደስታና ሐዘን መፈራረቃቸውን፣ የግለሰብ ሕይወት በሞት ተሸንፎ መሻሩን፣ ገንዘብ የማይገዛው ነገር መኖሩን፣ ገንዘብ በከበደ መጠን ማቅለሉን አለማወቅ፣ ገንዘብ የማይመክተው ጦርና በገንዘብ ሊታጠቀው የማይችል መሣሪያ መኖሩን አለማወቅ፣ የደከመ እንደሚያይልና ያየለ እንደሚደክም፣ ዓለማችን በጣም የተያያዘና የተቆራኘ በመሆኑ አንዱን ሲያስነጥሰው ሌላውን እንደሚነዝረው የወያኔ ጎረምሶች አልተረዱም፡፡
ዛሬ ፈጣሪና ፍጡር ተፋጠጡ፤ ፍጡር የማታለያ ልብሱን አውልቆ በዓለም ፊት ራቁቱን ቆሟል፤ በከመረው ውሸት መጠን ውርደትን ተሸክሞ ያቃስታል፤ እያታለሉ ውሸትን መጠምጠም እያታለሉ ውሸትን እንደመተርተር ቀላል አይደለም፤ ውሸት ያከሳል፤ ውሸት ያዋርዳል፤ ውሸት መደገፊያ ያሳጣል፤ ውሸት ወዳጆችን ያሳፍራል፤ ጠላቶችን ያፈነድቃል፡፡
በውሸት ለሌሎች የተገነባው ወጥመድ ሲከፈት ማንም፣ ምንም የለበትም፤ ባዶ ግን አይደለም፤ ባለቤቱ አለበት! ባለቤቱ በገዛ ወጥመዱ ውስጥ! ታለለ የተባለው ሁሉ ዳር ቆሞ አታላዩ መታለሉን እያየ ይስቃል፤ አታላዩ የውሸት ምሰሶው መውደቁን ገና አልተረዳም፤ ውሸቱን አይቶ ወዳጁ እንደከዳው አታላዩ አልገባውም፡፡
ማታለልና መዋሸት በሃያ አምስት ዓመታት ጉዞ ዙሪያውን ገደል አደረገው፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአስታራቂነት ጥረት ከብዙ ዓመታት ጦርነት ወጥቶ በሰላም የነበረው ሱዳን አሁን ለሁለት ተገመሰ፤ ለሁለት መገመሱ አልበቃ ብሎ እንደገና ሊገማመስ እየተደባደበ ነው፤ የሶማልያ ትርምስ እየባሰበት ሄደ እንጂ አልተሻለውም፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደተኳረፉ ናቸው፤ ከዚያም በላይ በውክልና እየተቆራቆዙ ነው፤ የኢትዮጵያና የኬንያ ወታደሮች መጋጨታቸውና ጥቂቶች መሞታቸው አዲስ የሰላም ጠንቅ ነው፤ ጂቡቲ በፈረንሳይና በአሜሪካ ጦር የምትጠበቅ ስለሆነ አይበገሬ ትሆናለች፤ ሆኖም የአዲስ አበባ-ጂቡቲ ባቡር መቆም በጂቡቲ ሕዝብ ላይ የሚያስነሣው ግም ስሜት የለም ለማለት ያስቸግራል፡፡
የምዕራባውን ኃይሎች ፍላጎት ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነባት፣ ከነሱ ምጽዋት የማትወጣ ፍጹም ደሀ፣ ያለምንም ስጋት አካባቢውን በሞላ ለመቆጣጠር የሚያስችላቸው ሁኔታ የተመቻቸበት እንድትሆንላቸው ነበር፤ አሁን ግን ሰላም የሰፈነባት አገር እንደማትሆን ምልክቶችን እያዩ ነው፤ እንዲያውም በመሀከለኛው ምሥራቅ በግልጽም ይሁን በስውር እየበረታ የሚሄደው ጸረ-አሜሪካን ስሜት በአፍሪካ ቀንድ ላይ የተተከለ እንደሆነ ምዕራባውያን በመሀከለኛው ምሥራቅ ዘይት አምራች አገሮች ላይ ያላቸውን ጥቅም ሁሉ ክፉ ስጋት ላይ የሚጥልባቸው ሊሆን እንደሚችል የተገነዘቡ ይመስላል፤ በተጨማሪም ከኤርትራ ጋር በጠላትነት የተፋጠጠች ኢትዮጵያ ለምዕራባውያን የምትመች አለመሆንዋንም እየተገነዘቡ ነው፤ ስለዚህም ከኢትዮጵያ አገዛዝ ጋር በመሆን አሻክረውት የነበረውን ግንኙነት ለማለስለስ እየሞከሩ ነው፤ ይህ ሁሉም እየሆነ የኢትዮጵያ አገዛዝ ገና አልነቃም፤ በአፍሪካ ኅብረት በኩል ቀስቃሽ ተልኮለታል፡፡
በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት ለወግም እንኳን መጥፋቱን የአፍሪካ ኅብረት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የተገነዘበው ይመስላል፤ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ለዓመታት የማይቋጭ ሆኖ የቆየውን የእስላሞች ጉዳይ ለማየት ውሳኔ ላይ ደርሷል፤ በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት አለመኖሩን የአፍሪካ ኅብረት ውሳኔ ዋና ማረጋገጫ ነው፤ ዙሪያው ገደል መሆኑ የምዕራባውያን (አሜሪካና አውሮፓ) ኃይሎች ተማምነውበት የነበረውን የኢትዮጵያ አገዛዝ ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል፤ ዙሪያው ገደል መሆኑ የኢትዮጵያ አገዛዝ የሰላም አራማጅ መስሎ እንዳይታይ አድርጎታል፤ እንዲያውም የኢትዮጵያ አገዛዝ በአካባቢው ካሉት አገዛዞች ጋር የሻከረ ዓይነት ግንኙነት ስለሚያሳይ አሜሪካና አውሮፓ የሚወድዱት አይመስልም፤ ይህ ውጪውን ሲታይ ነው፡፡
ከውስጥ ሲመለከቱት ደግሞ ሌሎች የግጭት መድረኮችና ሌሎች ጉዳዮች ይታያሉ፤ ዋናውና መሠረታዊው ግጭት አገዛዙ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን ነጻነቶችና መብቶች ሰርዞ ምንም ዓይነት ልዩነት በቃልም ይሁን በጽሑፍ መግለጽ እንደሽብርተኛነት የሚያስቆጥርና የሚያስወነጅል መሆኑ ነው፤ ፕሮፌሰር ስርግው ሐብለ ሥላሴ ዓጼ ምኒልክ፣ የአዲሱ ሥልጣኔ መሥራች በሚለው መጽሐፉ ኢትዮጵያውያን አእምሮ የሚባለውን ጋዜጣ መግዛት እንዲለምዱ በማለት አጼ ምኒልክ ጋዜጣውን ይዘው በአደባባይ እንደሚወጡ ይነግረናል፤ ዛሬ በአዳፍኔ አገዛዝ፣ መቶ ዓመታት ወደኋላ ሄደን ታዋቂ ጋዜጠኞች ሁሉ በእስር እየማቀቁ ጋዜጦች ሁሉ ጠፍተዋል፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተከልክለውና ታፍነው ባሉበት የወያኔ አገዛዝ፣ የፖሊቲካ ቡድኖች ተኮላሽተው አልጋ ላይ በዋሉበት ሁኔታ፣ ፖሊሶች፣ ዓቃቤ ሕጎች፣ ዳኞችና የወህኒ ቤት አዛዦች እንደፈለጉ በሚሠሩበት አገር ግጭቶች ያለማቋረጥ እንደሚፈጠሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፤ የፖሊቲካ ውይይት፣ ክርክርና ንግግር በተከለከለበትና አንድ ድምጽ ብቻ ለማዳመጥ በተፈቀደበት ሥርዓት ብዙ እምቢ-ባዮች ይኖራሉ፤ አዳፍኔ ጎራዴውን እየሳለ በሄደ ቁጥር ሰላማዊ የፖሊቲካ ውይይትም በተስፋ-ቢስነት አላስፈላጊ አማራጭ ውስጥ ይገባል፤መለስ ዜናዊ ‹‹መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ›› ብሎ ተቀናቃኝ ቡድኖችን ከመረቀ ሃያ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ፤ አሁን ምርቃቱ የደረሰ ይመስላል፤ ዛሬ ላይ ሆኖ ሲታሰብ መለስ ዜናዊ ራሱን የረገመ ይመስላል፡፡
ወሬው ሁሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ አለመረጋጋት የሚያመለክት ነው፤ ከጎንደር አስከቦረና ከኦጋዴን አስከጋምቤላ ወሬው ሁሉ የግጭት ነው፤ አንድም ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ፣ በውይይትና በስምምነት መደምደሚያ ሲያገኝ አይታይም፤ አይሰማም፤ ሁሉንም ነገር በጡንቻ በማስገደድ ለማስፈጸም የሚደረገው ሙከራ ያረጀና ያፈጀ መሆኑን ለማስታወቅ ተቀዋሚውም የጡንቻውን መንገድ እየተላመደው ነው፤ ጡንቻ ለጡንቻ መቆራቆዙ ደም እያፋሰሰ ጡንቻን ያነግሣል እንጂ ሕዝብን አይገነባም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የጡንቻ ግጭት መስፋፋት በሰሜን በኤርትራና በትግራይ፣በትግራይና በጎንደር፣ በትግራይና በወሎ፣ በምሥራቅ በሱማሌና በኦሮሞ፣ በሱማሌና በሐረሬ፣ በኦሮሞና በሐረሬ ፣ በደቡብና በምዕራብ በተለያዩ ጎሣዎች መሀከል የተጫረው እሳት ሲቀጣጠል ማብረዱ እንደማቀጣጠሉ ቀላል አይሆንም፤ ተንጋሎ የተፋ ለራሱ ከፋ እንደሚባለው ይሆናል፤ በምዕራብና በምሥራቅ፣ በሰሜንና በደቡብ የሚቀጣጠለው እሳት ድንበር ጥሶ የሚወጣና ጦሱ የማይበርድ ይሆናል፤ወያኔም ሆነ ለወያኔ ወንበር ያሰፈሰፉ ሁሉ፣ በጎሠኛነት ስሜት እየነደዱ የማመዛዘን ችሎታቸውን ያጡ ሁሉ የሰነዘሩት የጥላቻ ስለት በነሱው ላይም ሲያርፍ የተመኙትን ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ እንደሚያጋጥማቸው ከመሸ በኋላ ይረዱታል፤ ለሌሎቹ አዲስ ይሆናል እንጂ ለወያኔ ከመሸ በኋላ መረዳት የባሕርይ ነው!
ከሶርያ በሶማልያና በኬንያ በኩል እያደፈጠ የሚገሰግሰው የሽብር ቡድን ወደኢትዮጵያ አይደርስም ማለቱ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ እንደተለመደው ለከመሸ በኋላ ማሰብ ማስተላለፉ የመጨረሻው ስሕተት ሊሆን ይችላል፤ የመጨረሻው ስሕተት የተሠራውን አሰፋልት መንገድ አፍርሶ የባቡር ሀዲድ እንደመሥራት አይቀልም፤ የውጮቹን አካባቢ ኃይሎች እንደውስጡ አመራር በጡንቻ (የአሜሪካን ድጋፍ ቢኖርበትም) ለማስተናገድ ማሰብ ማሰብ አይደለም፤ ማሰብ የጎደለው መሆኑም በገሃድ እየታየ ነው፤ በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉ አገሮች በሚከተለው ሰንጠረጅ ተዘርዝረዋል፡፡
ወደአሥራ አንድ የሚጠጉ ጎረቤቶች እንኳን ለአላዋቂዎች አምባገነኖችና ለአዋቂ መሪዎችም ቢሆን በጣም ፈታኝ ነው፤ የኢትዮጵያ አገዛዝ አሜሪካንን ከመጠን በላይ በመተማመን የውጩን አመራር ልክ እንደውስጡ በጉልበትና በማታለል ላይ የተመሠረተ አድርጎታል፤ ይህ ሁኔታ ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል አድርጎታል፤ በዚህም ምክንያት እንዳይደርስ ከተባለበት ከጂቡቲ በቀር ከኢትዮጵያ ጋር በግጭት ያልተላከፈ አገር የለም፤ የኃያል አሽከር መሆን ኃያል የሆኑ የሚያስመስል ሕመም አለ፤ ጃንሆይ አማኑኤል ሆስፒታልን ሲጎበኙ አንዱን ያገኙትና ስሙን ይጠይቁትና ይነግራቸዋል፤ ቀጥሎም በተራው ያንተስ ስም ይላቸዋል፤ የኛማ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ነው ብለው ሲመልሱለት ከት ብሎ ይስቅና እኔንም ሲጀምረኝ እንዲህ ነበር ያደረገኝ ይላቸዋል! መማር የፈለገ አምባገነን እብድ ከተባለ ሰውም መማር ይችላል! አሜሪካኖች የኢትዮጵያን አገዛዝ የአካባቢው ሰላም ጠባቂነት በጥርጣሬ እንዲመለከቱት ያደረጋቸው ይኸው ሳይሆን አይቀርም፤ አንዱና ዋናው የማሰብ ችግር ነው፡፡
ኢትዮጵያና ጎረቤቶችዋ
2008 ዓ.ም.
ተ፣ቁ. አገሮች የኢትዮጵያ ጦር ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት የውስጥ ሰላም
1 ኢትዮጵያ የለም
2 ሱዳን1 አለ አለ የለም
3 ሱዳን2 አለ የለም
4 ሱዳን3? ?
5 ኬንያ ? አለ አለ
6 ሰማልያ አለ የለም
7 • ስባሪ1 የለም
8 • ስባሪ2 የለም
9 • ስባሪ3 የለም
10 ጂቡቲ አለ
11 ኤርትራ አለ አለ
ምናልባት ከባሕር ማዶ ያለው ጎረቤታችን፣ የመን በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ላይ የተለየ መዘዝ ይዞላቸው ይመጣ ይሆናል፡፡
አሁን ደግሞ ከሁሉም የባሰው መጋለጥ መጣ፤ ማንም በማይደርስበት ፍጥነት እያደገ ነው የተባለው ኢኮኖሚ አከርካሪቱን ተመታ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በችጋር ጥቃት ስር ወደቀ፤ የወያኔ የኢኮኖሚ እድገትም ሆነ የአገሩን ሕዝብ ያቀጨጨው የወያኔ ጡንቻ ውሀ ሆኑ፤ ኢኮኖሚ በጡንቻ አያድግም፤ ችጋር በጡንቻ አይገፋም፤ ሕጸናትንና አሮጊትና ሽማግሌዎችን የገጠር ነዋሪዎች እያመነመነ በመጣል የሚጀምረው ችጋር አይደበቅም፤ ከወራት በኋላ ማምለጥ ያልቻሉትን ሁሉ ችጋር እየበላ በያለበት ሲጥላቸው በዓለም ጋዜጦች ይወጣል፤ ያኔ መዋሸትና ማታለል ዋጋ ያጣሉ! ያኔ ጡንቻ ዋጋ ያጣል! ያኔ ስለእድገት ማቅራራት ዋጋ ያጣል!
ዓላማው ሁሉ ታወቀ፤ ዘዴው ሁሉ ታወቀ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓላማውም ዘዴውም ሰለቸው፤ ምዕራባውያን ኃይሎች ውሸትን መጠገን ሰለቻቸው፤ የአፍሪካ ሕዝቦች የጎሠኛነት በሽታ እንዳይተላለፍባቸው ፈሩ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ
=============================
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በስፋት ተቃዉሟቸውን እያሰሙ ነው። በወያኔ ግፈኛ ታጣቂዎች በጎንደር እና በኦሮሚያ በግፍ ለተገደሉ ወገኖቻችን ሃዘናቸውን በመግለጽ፣ እህቶቻችንም ጥቅር በመልበስ፣ በካፌቴሪያ ምሳ አንበላም ብለው ብይኮት አደርገዋል።
እንቅስቃሴ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ወደ አዲስ አበባ እየገባ ። እንቅስቃሴው በኦሮሞ ተማሪዎች በማስተር ፕላኑ ዙሪያ ቢጀመርም፣ መልኩን በስፋት ቀይሮ፣ አሁን የሁሉም ዜጎች እንቅቃሴና ሆኗል። 
ለመሰረታዊ የመብት፣ የነጻነት የእኩልነትና የዲሞክራስ ጥያቄ ሆኗል።
በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች እየተደረጉ ያሉ እጅግ በጣም ብዙ እንቅስቃሴዎች እንደተጠበቁ፣
በተመሳሳይ ሁኔታ በሃረር ከተማ (ሃረሬ ክልል)፣ በዲላ ( ደቡብ ክልል፣ ጌዶ ዞን ዋና ከተማ) እንዲሁም በአዋሳ (የደቡብ ክልል ዋና ከተማ) ተቃዉሞዎች ተደረገዋል።
በተለይም በአዲስ አበባ ህይ ስኩሎችን በቅርብ ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Tuesday, 8 December 2015

ማር በሜንጫ ( ሄኖክ የሺጥላ )

ማር በሜንጫ ( ሄኖክ የሺጥላ )
እኛ ኢትዮጵያውያኖች ነን ፣ ስለዚህ እነ ሜንጫ ( <Ethiopia out of Oromoa> ) ሲሉን ፣ እንዴት ተደርጎ ? እንዴት ልጅ እናቷን ትወልዳለች ብለን ነበር ። እኛ የወያኔ በደልን የምንጠየፈው ወያኔ በዘር ተደራጅቶ አንድን ወይም ሁለትን ዘር ኢላማ አድርጎ የዘር ማጥፋት በየዕለቱ በመፈጸሙ ነው ፣ ይህንንም ስንል ወያኔን ( የኛን ቁስል የጠገበውን ዝንብ አራግፈን ሌላ ወያኔ መሳይ ፣ ቁስል የናፈቀው ዝምብ ይምጣ ማለታችን አይደልም ።) ይህንን ስንል በአሩሲ ፣ በባሌ ፣ በጉጂ ፣ በበደኖ ፣ በአርባባ ጉጉ እና ወዘተ የፈሰሰው የንጹሃን ኢትዮጵያውያን ደም ፍትሃዊ እና ሚዛናዊ የሕግ ፍርድ ስላገኘ አይደለም ዛሬ የኦሮሞ ልጆች ደም መፍሰስ የሚቆጨን ፣ ይህንን ስንል እስከሚገባኝ ያኛውም ይሁን ይሄኛው የዘር ማጥፋት ሴራ በበላይነት የተመራው በወያኔ መሆኑን ስለምንረዳ ፣ አትኩሮታችን ወያኔን ማስወገድ ላይ ይሁን ማለታችን ነው እንጂ ፣ የጠላታችን ጠላት ወዳጃችን ነው ማለታችን አይደለም ። የጠላታችን ጠላት ወድጃችን የሚሆነው የጋራ የሚያደርግ ነገር ሲኖረን ብቻ ነው ። የጋራ የሚያድረግ ስል ፣ የጠላታችን ጠላት ፣ አንቦ ላይ የተገደሉት የኦሮሞ ልጆች ጎንደር ላይ ከፈሰሰው የአማራ ልጆች ደም በምንም አይነት አይበልጥምም አያንስምም ብሎ ማመን ከቻለ ብቻ ፣ የሱ የእንተባበር ጥሪ ሰሚ ያገኛል ። ይህም ማለት አንቦ ላይ ለሚፈሰው ደም እሱ ሕጋዊ ወኪል ወይም ተጠሪ ነው ማለት አይደለም ፣ ወይም ደም ጎንደር ላይ ለፈሰሰው ደም አማራው ብቻ የሚባዝንበት እና በበላይነት የሚመራው የብቻ ኃላፊነት ነው ማለት አይደለም ። ግን ደሞ ፣ ያንተ ቁስል የነፍጠኛ ቁስል ነው ፣ የኔ ግን ዘላለም ሲብደል የኖረ ሕዝብ ቁስል ነው የሚለኝ ከሆነ < ብቻውን ቁስሉን ሲያክ ሊኖር ነው ማለት ነው !> ፣ < በዚህም ጎን እንደዚያው !>
ለዚህም ነው ሰሞኑን ጃዋር መሐመድ በ (ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ( OMN )) ቀርቦ ያደረገውን የእንተባበር ጥሪ ፣ ከጉንጫ አልፋ ፖለቲካና ፣ የመለዜናው ቃናን ከያዘ ብልጣ-ብልጥ የአፍ ፖለቲካ ባሻገር ፣ < ወይም ማር የተለወሰ መርዝ > እንደሆነም አድርጌ ያየሁት ።
በመሰርቱ ውይይቱ ራሱ ብዙ ግድፈት የበዛበት ነው ። ለምሳሌ ጃዋር < ኢትዮጵያ ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት እናዳለ ይናገራል ፣ በኦሮሚያ አካባቢ ያሉ ገበሬዎች የተራቡት መሬታቸው በመንግስት ስለተነጠቀ ነው ይላል ፣ በአማራ ክልል አንድ ሄክታር መሬት አልተወረሰም ፣ ወይም ለባለሃብት በኢንቨስትመን ስም/ምክንያት አልተሰጠም ይላል ? ይህንን ያለው ስለ ወልቃይት ጠገዴ ስለማያውቅ አይደለም ፣ ጎንደር ላይ ዛሬ ድንበር ተካሎ ለሱዳን ተቆርሶ ሊሰጥ እንደሆነ ስለማያውቅ አይደለም ፣ በሁመራ ሰሊጥ ፣ ጥጥ ፣ እጣን እና ኑግ እየዘራ የምያጭደው ወያኔ እንደሆነ ስለማይረዳ አይደለም ፣ ባጭሩ ለጃዋር አማራው ላይ የሚደርሰው በደል በደል ሆኖ ስለማይታየው ነው ፣ ስለዚህ
አባት ዓለም ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ያለውን ለጃዋር ላስታውሰው
የት ሊደረስ
ዛሬ ሀቅ ቢቀለበስ
በጀርባችን ይከተላል ነገ የዳኝነት ፈረስ
መቻቻልን ማወቅ ነው እንጂ
ጠንቅቀን እንደ አባ መቻል
መሸቀል አይሰራም በቃል !
ዛሬ ጮሌ ሆኗል ሁሉም
ብልህነት እንጂ ብልጠት
አክትሞለታል ዘመኑም !
ስለዚህ ይገባናል ፣ ይህ የእንተባበር ጥር ከልብ የመነጨ እንዳልሆነ ። እንደ ጃዋር አባባል < እኛ በኦሮሞ ምድር ሌላ ሰው አይኑር አላልንም ! እንደውም ሰው እንፈልጋለን !> ይላል ። ይህ ልክ ከሆነ ( <Ethiopia out of Oromoa> ) ያለውን ጃዋር እንመን ወይስ ይሄ ሰው እንፈልጋለን ያለውን ። ወይስ ሰው የሚፈልገው ከደማስኮ ይሆን ? በመጀመሪያ ጃዋር የኢትዮጵያን ሕዝብ ለትብብር ለመጠየቅ የሚያስችል የሞራል ብቃት አለው ብዬ አላምንም።
እንድንተባበረው ከፈለገ ፣ እንደ ሕዝብ ይቅርታ ሊጠይቀን ይገባዋል ፣ ዝቶብናል ፣ ፈርጆናል ፣ እንደውም በሜንጫ ( እንደሱ አባባል መንጫ ማለት እንደ ቦክስ ነው ፣ በቦክስ ሊለን ዝቷል !) ። ያለበለዚያ ጃዋር ሆይ ያንተ ይቺ እንተባበር ጥሪ ማር በ -ሜንጫ ላሱ ነገር ትመስላለች ፣ ሙድ የላትም!!!
የግርጌ ማስታወሻ
ጃዋርን ያላማከረ እና ያላማከለ ለኢትዮጵያውያኖች ( ኦሮሞዎች ፣ አማራዎች ፣ ጉራጌዎች እና ወዘተ ) የሚደረግ የተቃውሞ ና የትግል ጥሪ ያስፈልጋል እያልኩ አይደለም ። እያልኩ ያለሁት የትግሉ ብሌን መሆን የሚፈልገው ጃዋር እና መሰሎቹ ከራሳቸው ባህሪ ስንነሳ ሕዝብ ሊከተላቸው ወይም ሊሰማቸው የሚችሉ ሰዎች አይደሉም ( ሕዝብ ስል የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለቴ ነው )። ይልቁንም ሌላ ህውሃት ፣ ሌላ ገዳይ ቡድን ፣ የተፈጠረውን እሳት ተጠቅሞ ፣ ከቻለ ይህ " አማርኛ ሲሰማ የተወደደ የሚመስለው የዋህ አማራ ካለ ፣ እሱን አበድኖ ፣ ወንድምህ ነኝ ብሎ ፣ ትግል መንግሎ ለመቆም የሚያደርጉት ብልጣ ብልጥነት ነው !" የጃዋር የለበጣ አማርኛ ሆድ የሚያስብሰው ካለ የራሱ ጉዳይ ነው ፣ እኔ ግን ስለ ጃዋር ሳስብ ጭንቅላቴ ውስጥ የሚመጣው ሜንጫው ነው !

Friday, 4 December 2015

እነ ዘላለም ወርቃገኘሁ ተጨማሪ መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰሙ

እነ ዘላለም ወርቃገኘሁ ተጨማሪ መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰሙ
‹‹ጉራጌ ሲሰርቅና ሲያጭበረብር እንጂ ሲታገል አያምርበትም እየተባልኩ እደበደብ ነበር›› 9ኛ ተከሳሽ
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብርተኝነት ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙት እነ ዘላለም ወርቃገኘሁ ተጨማሪ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ዛሬ ህዳር 24/2008 ዓ.ም አስደምጠዋል፡፡
በዚህ መዝገብ 9ኛ ተከሳሽ የሆነው አቶ ባህሩ ደጉ 3 መከላከያ ምስክሮቹን ያስደመጠ ሲሆን፣ የተከሳሽነት ቃሉንም ለፍርድ ቤቱ ሰጥቷል፡፡ አቶ ባህሩ በተከሳሽነት ቃሉ ላይ እንደጠቀሰው ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞበታል፤ ቃሉንም በግዳጅ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡...
አቶ ባህሩ ደጉ ለፍርድ ቤቱ እነዳስረዳው ማዕከላዊ እያለ ራቁቱን ተደብድቧል፤ ከድብደባ ብዛት ሽንቱን መቆጣጠር ተስኖት እንደነበር በማውሳት የገዛ ሽንቱን እንዲጠጣ ተገድዷል፡፡ በተጨማሪም አቶ ባህሩ ‹‹የግንቦት ሰባት መሪ ብርሃኑ ነጋ ምንህ ነው? ከአንዳርጋቸው ጽጌስ ምን አለህ? ብርሃኑ ዘመድህ ነው?›› የሚሉ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እየቀረቡለት በማያውቀው ነገር ሲሰቃይ እንደነበር ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
አቶ ባህሩ ደጉ በማንነቱ ምክንያትም ስቃይ እንዳሳለፈ በማውሳት፣ ‹‹ከጉራጌ መወለድ ወንጀል ነው እንዴ?›› ሲል በችሎት ፊት ጠይቋል፡፡ ‹‹ጉራጌ ሲሰርቅና ሲያጭበረብር እንጂ ሲታገል አያምርበትም እየተባልኩ እደበደብ ነበር›› ያለው አቶ ባህሩ፣ ‹‹የደም ስርህን በጥሰን እንገልሃለን፤ ፖሊሱ፣ አቃቤ ህጉ፣ ፍርድ ቤቱ፣ ደህንነቱ…ሁሉም የኛ ነው፤ አንተን 20 አመት እናስርሃለን›› እየተባለ ስቃይ እንደተፈጸመበት በማስረዳት በምርመራ ወቀት የሰጠው ቃል ተገድዶ የሰጠው መሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዲረዳለት አሳስቧል፡፡
9ኛ ተከሳሽ ባህሩ ደጉ የተከሳሽነት ቃሉን ከሰጠ በኋላ ሦስት መከላከያ ምስክሮችን አሰምቷል፡፡ ከምስክሮቹ መካከል በዚሁ መዝገብ 1ኛ ተከሳሽ ዛላለም ወርቃገኘሁ እና ሌላኛው ምስክር ጦማሪ ዘላለም ክብረት ተከሳሹ ‹‹ለሽብር ወንጀል ስልጠና ሊወስድ ነበር›› በሚል ስለቀረበበት ክስ የስልጠናውን አይነትና የአሰልጣኞችን ማንነት በማብራራት ስልጠናው ለሽብርተኝነት ድርጊት ሳይሆን በታወቁ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የሚሰጥ ግልጽ ስልጠና እንደነበር አስረድተዋል፡፡ 3ኛ ምስክር በበኩላቸው ተከሳሹ ማዕከላዊ ወንጀል ምረመራ በነበረበት ወቅት አብረው ታስረው እንደነበር በመግለጽ ይፈጸምበት የነበረውን አሰቃቂ ምርመራ በተመለከተ የሚያወቁትን መስክረዋል፡፡ እኒህ ምስክር ተከሳሹ ሌሊት ለምርመራ በሚል እየተጠራ ድብደባ ይፈጸምበት እንደነበር አስረድተዋል፡፡
በዚሁ መዝገብ 1ኛ ተከሳሽ በምስክርነት የጠሯቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲቀርቡ በተደጋጋሚ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤቱ ቢሰጥም እስካሁን አለመቅረባቸው ታውቋል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ ዛሬም ሌላ ትዕዛዝ በመስጠት ማረሚያ ቤቱ እስካሁን ያላቀረበበትን ምክንያት ገልጾ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርባቸው ታዝዟል፡፡


ልዮነታችን ከፍልሰፍናችን እንደሚመነጭ ተረድቻለሁ

ግርማ ሰይፉ ማሩ
"ኦሮሞ ያልሆነ የኦሮሞ ችግር አይገባውም፣ ድሮም ከአበሻ ምን ይጠበቃል፣ የእኔ እና የሌሎች ሃሳብ የሚል ፖለቲከኛ፣ አንተን ብሎ ፖለቲከኛ የሚሉና የሚመሳስሉ ብዙ ምላሾች አንብቢያለሁ፡፡ ለማነኛውም ልዮነታችን ከፍልሰፍናችን እንደሚመነጭ ተረድቻለሁ፡፡ እኔ በቡድን አስተሳሰብ ውስጥ የለሁበትም፡፡ ብዙ ሰው /ህዝብ የሚባልም ቢሆን/ ስለደገፍ ያለመደገፍ መብት አለኝ፡፡ ማስረጃ ላቅርብ በምክር ቤት 546 ሰው ሲደግፍ ብቻዬን ተቃውሚያለሁ፡፡ ብዙ በደገፈ መደገፍ ከሆነ ይህንንም መደገፍ ሊኖርብኝ ነው፡፡ ይህ ግን አይሰራም፡፡ ለማነኛውም ጉዳዮን ከረር ለማረግ እኔ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ይህ የእኔ ብሔር መሬት፣ ሀብት፣ ወዘተ የምለው የለኝም፡፡ ለእኔ የሌለኝ ሌሎች መብት ሌሎች ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ሌሎች እንዲኖራቸው መፈለግ መብታቸው... ቢሆንም ህጋዊ ግን አይደለም፡፡ ለምሳሌ መሬት በግለሰብ ደረጃ በሚሰጥ ካርታ እንጂ በዘር በጎሳ በሐይማኖት የሚያዝ አይደለም፡፡ ህገ መንግሰቱ ካሉበት ሸፋፋ ነገሮች አንዱ መሬት የህዝብና የመንግሰት ነው የሚለው ክፍል ነው፡፡ እንበል “የኦሮሞ መሬት” የሚባል አለ ከተባለ፣ ይህ መሬት ለወላይታ እንዴት ሊሰጥ ይችላል? በአዋሳ ከተማ ያለ መሬት የሲዳማ ከሆነ ካርታ የያዙ ሌሎች ሰዎች ባለመብት አይደሉም ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ “ብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች” በሰማቸው ካርታ ያላቸው አይመሰለኝም፡፡ ካላቸው እንደመረጃ ፖሰት አድርጉልኝ፡፡ ማንም ደስ ቢለው ቢከፋው እኔ የተመቸኝ ሃሳብ “ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ አማርኛ፣ ወዘተ የሚባሉ ቋንቋ እንጂ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግሬ፣ ወዘተ የሚባል መሬት የለም” የሚለው ነው፡፡ በህገ መንግሰት ማንም ሰው በፈለገበት የመኖርና የመስራት፣ ንብረት የማፍራት መብት እንዳለው ሲገልፅ በዘር የሚገኝ ንብረት፣ ሀብት የሌለ መሆኑን ለማስቀመጥ ይመስለኛል፡፡ ለማነኛውም አንተ ብሎ ፖለቲከኛ ላላችሁኝ መቼ አልኩ እኔ እናንተ አላችሁኝ እንጂ ማለት ነው፡፡ የአኔን ፖለቲካም ሆነ ማህብራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አስተያየት መውደድም ሆነ መጥላት መብት ነው፡፡ ለማንኛው እወዳችኋለሁ … ገለቶማ!"

‎በእሳት‬ በጋየው የጎንደሩ ግዙፍ ወህኒ ቤት ውስጥ በህወሓት ጦር የተጨፈጨፉት እስረኞች ማንነት በመታወቅ ላይ ነው

የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ

ህዳር 21 2008 ዓ.ም በጎንደር ከተማ በሚገኘው ግዙፍ ወህኒ ከባድ የእሳት ቃጠሎ መነሳቱን ተከትሎ የህወሓት ሰራዊት በርካታ እስረኞችን በግፍ መጨፍጨፉና ዙሪያውን በእሩምታ ተኩስ አጥሮ ማህሉንም ዳሩንም እሳት በእሳት በማድረግ መሽሎኪያ ቀዳዳ በማሳጣት ብዙዎቹን ማጋየቱ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም በግፈኛውና ፋሽስቱ የህወሓት አገዛዝ ሰራዊት ከተጨፈጨፉት እስረኞች መካከል የተወሰኑት ማንነታቸው ተለይቶ በየትውልድ ቀዬዎቻቸው በመቀበር ላይ ናቸው፡፡...
አቶ አለቤ ኃይሌ የተባሉትና ከመታሰራቸው በፊት በጥበቃ ስራ ይተዳደሩት የነበሩት ሰው ትናንት በወገራ ወረዳ ጉንትር ቀበሌ አቦ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስርዓተ ቀብራቸው ተፈፅሟ፡፡ በተጨማሪም የዚሁ ወገራ ወረዳ ጉንትር ቀበሌ ነዋሪ የሆነው የ17 ዓመቱ ታዳጊ መላክ ችሎት በወህኒ ቤቱ ውስጥ በጥይት ተደብድቦ ከባድ ጉዳት ደርሶበት በህክምና ላይ ይገኛል፡፡
ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለው በቅርቡ በህወሓት ደህንነቶችና የታጠቁ ቡድኖች ታፍነው ከደልጊ ወደ ጎንደር ከተወሰዱት ከ10 በላይ ሰዎች መካከል እስካሁን አቶ አሰፋ ገዳሙ የተባሉት አዛውንት መገደላቸው ተረጋግጧል፡፡ በአርማጭሆ የሽመለ ጋራ ቀበሌ አስተዳዳሪ የነበረው ነውጥ ብቃለ የተባለው ግለሰብም መገደሉ ጭምር ታውቋል፡፡
አድራሻቸውና የአባታቸው ስም ገና በመጣራት ላይ ከሚገኙት እጅግ በርካታ የተጨፈጨፉ እስረኞች መካከል ደግሞ ቀናው፣ እሸቴ፣ ጤናው፣ ማስረሻ፣ አዱኛ... የተባሉት ይገኙበታል፡፡
ሽመልስ አቡሃይ የተባለው እስረኛ ያልነበረ ሰላማዊ ወጣት ደግሞ ትናንትና በተነሳው ግርግር በግፍ ተገድሎ ዛሬ በጎንደር ደብረ ብርሃን ስላሴ ቤተክርስቲያን ተቀብሯል፡፡


Thursday, 3 December 2015

በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የቀረበውን ይግባኝ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አደረገው

በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የቀረበውን ይግባኝ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አደረገው

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በእነ ዘመነ ካሴ መዝገብ ከ2 ኛ እስከ 5 ኛ ድረስ ለተጠቀሱት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ተጠይቆ እስር ቤቱ በተደጋጋሚ ጊዜያት ሳያቀርባቸው ቢቆይም፣ ተከሳሾቹ ለጠ/ፍርድ ቤት ባመለከቱት መሰረት፣ የፌደራል አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ምስክር ሆነው እንዳይቀርቡ ያቀረበውን ይግባኝ ህዳር 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኙን ውድቅ አድርጎታል፡፡ የፌደራል አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው በእነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ እና በእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መዝገብ ላይ ክስ ቀርቦባቸው በእድሜ ልክና በሞት እንዲቀጡ ተወስኖባቸው የህዝባዊ መብታቸው የተሻረ ...በመሆኑ በምስክርነት ሊቀርቡ እንደማይችሉ መቃወሚያ አቅርቧል። የልደታ ፍርድ ቤት በበኩሉ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ምስክርነት እንዲሰጡ ከወሰነ በኋላ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ‹‹ትዕዛዝ አልደረሰኝም የተፃፈው ለቃሊቲ ሳይሆን ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት የሚል ነው›› እና ሌሎችም ምክንያቶች በመደርደር በተደጋጋሚ አቶ አንዳርጋቸውን ሳያቀርብ ቢቆይም፣ ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው እንዲቀርቡላቸው የጠየቁት ለዋስ አሊያም ልዩ አዋቂ ምስክር ሆነው ሳይሆን ነበሩበት የተባለውን ጉዳይ ለመናገር በመሆኑ ለምስክርነት ሊቀርቡ ይገባል በሚል የፌደራል አቃቤ ህግ ያቀረበውን ተቃውሞ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል። በተጨማሪ በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል 1ኛ ተከሳሽ አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁም አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት ጠርቷቸዋል፡፡ በሌሎች የክስ መዝገቦች ከአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ተገናኝታችኋል የተባሉ ተከሳሾችም የመከላከያ ምስክር አድርገው ሊጠሯቸው እንደሚችሉ የነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።