Saturday, 2 May 2015

አውነቱ ይውጣ! (ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)

ሴቶችን በወንዶች ፊት፣ ወንዶችን በሴቶች ፊት ልብስ እያስወለቁ የአካላቸውን ክፍሎች ሁሉ ለማየት የሚያስችል አንቅስቃሴ አንዲሠሩ ማስገደድ በሽተኞችን ያስደስታል፤ የምርመራ ዘዴ ግን አይደለም፤ ውርደት እንዲሰማቸው ከሆነ በወራዶች ሰዎች ፊት የምን መዋረድ አለ? ወራዶች እነሱ ደረጃ ላይ ከእነሱ ጋር ያስተካክላሉ አንጂ አያዋርዱም፤ በሌላ አነጋገር ወራዶች አያዋርዱም፤ ወራዶቹ ደንቆሮዎችም ሆነው ነው እንጂ ልብስ የሚያስወልቁ እነሱ ብቻ አይደሉም፤ ሀኪሞችም ልብስ አስወልቀው፣ አጋድመው በጣታቸውም ሆነ በመሣሪያ የፈለጉትን የአካል ክፍል አንደፈለጉ ያደርጉታል፤ ወራዶቹና ደንቆሮዎቹ ከሚያደርጉት የሀኪሞቹ የሚለየው ሀኪሞቹ ሰዎችን ለማዳን ሲሉ ነው፤ ወራዶቹና ደንቆሮዎቹ ግን የራሳቸውን ሱስ ለማርካት፣ የራሳቸውን ህመም ለማስታገስ ነው፤ 
ወራዶቹንና ደንቆሮዎቹን ከመለዮአቸው አራቁቻቸዋለሁ! ከነውር በቃላት ወደነውር በተግባር፣ ያውም በመሥሪያ ቤት! ዱሮ ዱሮ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ፊት ለፊት የአንድ ኢጣልያዊ ቡና ቤት ነበር፤ እዚያ ውጭ ተቀምጠን ቡና ስንጠጣ አንዲት ውብ ሴት ወደጸጉር መሥሪያው ቤት ስትመጣ የሁላችንም ዓይኖች እየዘለሉ እስዋ ላይ ዐረፉ፤ ከሦስታችን አንዱ ስለሴትዮዋ የወሲብ ችሎታ በዝርዝር መናገር ሲጀምር ሁለታችን ተያየንና አፈርን፤ ጨዋታው የጣመለት መስሎት ሲቀጥል የሕግ ባለሙያ የሆነ ጓደኛዬ አቋረጠውና ‹‹ስማ! ይህን ጊዜ እናትህ በአንድ ቦታ ስታልፍ አንዱ እንዳንተ ያለ ስለስዋ ችሎታ ያወራ ይሆናል!›› አለው፤ ሊጠጣ ወደአፉ ያስጠጋውን ስኒ ቁጭ አደረገና ተነሥቶ ሄደ፡፡
ሥልጣን ተሰጥቷቸው ሴቶችን ልብስ እያስወለቁ ምርመራ ነው የሚሉ በእናቶቻቸውና በእኅቶቻቸው ላይ ሊደርስ እንደሚችል አይገነዘቡም ይሆናል፤ ደንቆሮ የሚያደርጋቸውም ይኸው ነው፤ የአንዱ እናት አንድ ቦታ ላይ ራቁትዋን ቆማ በሽተኞች ተሰብስበው ሲስቁባት፣ በሌላ ቦታ ደግሞ ጓደኛው የእሱን እናት ወይም እኅት ያንኑ እያደረገ ያስቅባት ይሆናል፤ አንተ በእኔ እናትና በእኔ አኅት አስቅባቸው፤ እኔ ደግሞ በአንተ እናትና በአንተ እኅት አስቅባቸዋለሁ፤ ይህንን እየሠራን ኑሮአችንን እናቃናለን፤ እቤታቸው ሲገቡና ከእናቶቻቸውና ከእኅቶቻቸው ጋር ሲቀመጡና ሲበሉ (?!) ሰው ይመስላሉ፤ እነዚያም ግፉ የተፈጸመባቸው እናቶችና እኅቶች ‹ነውራቸውን› ምሥጢር አድርገው ለሰው ስለማይናገሩ ግፈኞችና የግፍ ሰለባዎች አብረው ይበላሉ!
አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ አንዳንድ ሴቶች የደረሰባቸውን ተናገሩ፤ አሁን ያፍራሉ የተባሉት እውነቱን ራቁቱን አወጡትና ከእፍረት ነጻ ወጡ! እውነቱ ሲወጣ የሚያፍረው ማን ነው? ደካማዎቹና የግፍ ሰለባ የነበሩት በጭራሽ አያፍሩም፤ የሚያፍሩት ግፈኞቹ ናቸው፤ የሚያፍሩት የሕዝብን አደራ በማቆሸሻቸው፣ በሥልጣን በመባለጋቸው፣ የሕዝብንና የአገርን ክብር በማዋረዳቸው ያፍራሉ፤ ኅሊናቸው በየቀኑ ነፍሳቸውን አርባ ሲገርፋት እየሳሳች እንቅልፍ ትነሳቸዋለች፡፡
ለመሆኑ በአገሩ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ መነኮሳት፣ ቀሳውስት — ሼሆች፣ ሽማግሌዎች በአገሩ የለንም?
መስፍን ወልደ ማርያም

ደህንነቶች የወይንሸትን ቤት ሲፈትሹ ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ባንዲራ በማግኘታቸው የብሄር/ብሄረሰቦችን መብት አትቀበይም ብለው ከሰሷት

ደህንነቶች የወይንሸትን ቤት ሲፈትሹ ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ባንዲራ በማግኘታቸው የብሄር/ብሄረሰቦችን መብት አትቀበይም ብለው ከሰሷት

ኢትዮጲያ ባንዲራ ቀለሙ ምን አይነት ነው›› ለሚለው ጥያቂያቸው ‹‹አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ከዚህ ውጪ ሌላ አላውቅም›› ብላ በማለቷ ፈርሚ ብለው አስፈርመዋታል........ እነርሱ ሀፍረተቢስ ናቸው በሚቀጥለው ችሎት ደግሞ ከሁከት እና አመፅ ማነሳሳት ጎን ለጎን ‹‹የኢትዮጵያን ባንዲራ ባለመቀበል›› ብለውም ይከሷት ይሆናል፡፡ ወይ ዘመን፡፡
አሳሳቢው ጉዳይ የጤንነቷ ነገር ነው..... ከጥቂት ቀናት በፊት ጤና ጣቢያ ወስደዋት ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ሪፈር የፃፈላት ቢሆንም ፖሊስ ተብዬዎቹ ሊወስዷት ግን ፍቃደኞች አይደሉም፡፡ እንኳን ወደ ሆስፒታል እንድትሄድ ሊያደርጉ ቀርቶ የጤና ጣቢያው ሀኪም ያዘዘላትን መድሀኒት ራሳቸው ጋር በማስቀመጥ ጠፋብን ብለው ይኸው መድሀኒቱን ከወሰደች ሁለት ቀን አለፋት፡፡ ከውጪም መድሀኒቱን ማስገባት ከልክለዋል፡፡ ወይ ነዶ፡፡
የፌስቡክ ፓስወርዳችሁን ካልሰጣችሁ እያሉ የሚደበድቡት አንሷቸው ህክምና መከልከል አሁን ምን ይባላል?

Thursday, 30 April 2015

ኢትዮጵያ እሥር ላይ የምትገኘውን ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን፤ ቪየትናም ደግሞ የኢንተርኔት ፀሐፊዋን ወይም ብሎገሯን ታ ፎንግ ታንን እንዲለቅቁ ዩናይትድ ስቴትስ ጠየቀች፡፡

ኢትዮጵያ እሥር ላይ የምትገኘውን ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን፤ ቪየትናም ደግሞ የኢንተርኔት ፀሐፊዋን ወይም ብሎገሯን ታ ፎንግ ታንን እንዲለቅቁ ዩናይትድ ስቴትስ ጠየቀች፡፡


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቃል አቀባይ ጄፍ ራትካ ናቸው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ይህንን የመንግሥታቸውን ማሳሰቢያ ያስተላለፉት፡፡የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በዚህ ሣምንት እያወጣቸው ባሉ ተከታታይ የፕሬስ መግለጫዎች በዓለም ዙሪያ በየእሥር ቤቱ ያሉ ጋዜጠኞችን በየቀኑ እያነሣ ይገኛል፡፡
በዚህ “FREE THE PRESS” ወይም “ፕሬስን ነፃ አውጡ” በሚለው ዘመቻው የዛሬው የመሥሪያ ቤቱ መግለጫ ካተኮረባቸው ሁለት ጋዜጠኞች አንዷና ቀዳሚዋ የቀድሞ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ መምህር ኢትዮጵያዊቱ ፍሪላንስ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ነች፡፡በፀረ-ሽብር ሕጉ መሠረት በተመሠረተባት ክሥ ጥር 10/2004 ዓ.ም ተፈርዶባት እስከዛሬ ወኅኒ ቤት እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ጄፍ ራትካ ጠቁመዋል፡፡
ርዕዮት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ በተመሠረቱባቸው ክሦች ምክንያት ከታሠሩ 18 ጋዜጠኞች አንዷ ስትሆን ይህ ሁኔታም ኢትዮጵያ በአህጉሩ ብዙ ጋዜጠኞችን በማሠር ቀዳሚዋ እንድትሆን አድርጓታል ብለዋል፡፡
ርዕዮት የመንግሥቱን ፖሊሲዎች የሚተቹ ፅሁፎችን በጋዜጣ በማውጣቷ ምክንያት በሰኔ 2003 ዓ.ም ተይዛ የሽብር ፈጠራ ክሥ ከተመሠረተባት በኋላ የ14 ዓመት እሥራት ተፈርዶባት እንደነበረ ያስታወሱት ራትካ የእሥራት ዘመኗ ወደ አምስት ዓመት ዝቅ እንዲል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በነሐሴ 2004 ዓ.ም መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ክሡ ሙሉ በሙሉ እንዲሠረዝላት በተከታታይ ያቀረበቻቸው የይግባኝ አቤቱታዎች ውድቅ መደረጋቸውንም ራትኮ አመልክተዋል፡፡
ሃሣብን የመግለፅ ነፃነት መብቷን ተግባራዊ በማድረጓ ብቻ ታሥራ የምትገኘውን ርዕዮትን እንዲፈታ ለመንግሥቱ ጥሪያችንን እናቀርባለን – ያሉት ራትኮ – መንግሥቱ ፀረ-ሽብር አዋጁን ሃሣብን በነፃነት የመለዋወጥን ተግባር ለመጠምዘዝ ጉዳይ ከመጠቀም እንዲቆጠብም እናሳስባለን …” ብለዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ጄፍ ራትኮ በመቀጠልም በአውሮፓ የዘመን አቆጣጠር የ2013 ዓ.ም ጀብዱ ፈፃሚ ሴቶች ዓለምአቀፍ ሽልማት ያሸነፈችውና የቪየትናምን መንግሥትና ኮምዩኒስት ፓርቲውን የሚተቹ ፅሁፎችን ኢንተርኔት ላይ በማውጣቷ የአሥር ዓመት እሥራት ተፈርዶባት ወኅኒ የምትገኘው ታ ፎንግ ታንን የቪየትናም መንግሥት በአፋጣኝ እንዲለቅቅ መንግሥታቸው እንደሚያሳስብ አስታውቀዋል፡፡

Wednesday, 29 April 2015

ካድሬዎች የሰማያዊን ፖስተሮች ባልተፈቀዱ ቦታዎች እየለጠፉ መሆናቸው ተገለፀ

ካድሬዎች የሰማያዊን ፖስተሮች ባልተፈቀዱ ቦታዎች እየለጠፉ መሆናቸው ተገለፀ
የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የሰማያዊን ፖስተሮች ባልተፈቀዱ ቦታዎች በመለጠፍ ላይ መሆናቸውን ሰማያዊ ፓርቲ ለምርጫ ቦርድ በፃፈው ደብዳቤ አሳወቀ፡፡ ፓርቲው ለምርጫ ቦርድ በፃፈው ደብዳቤ አዲስ አበባ ውስጥ በትምህርት ቤቶች፣ በቤተ ክርስቲያናት፣ በወታደራዊ ካምፖች እንዲሁም በሌሎች ፓርቲዎች ዕጩ ፖስተሮች ላይ ያለ ፓርቲው ዕውቅና የሰማያዊ ፓርቲ ፖስተር እየተለጠፈ እንደሚገኝና ይህም የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የሚፈጽሙት ተግባር እንደሆነ ገልጾአል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ በተከለከሉ ቦታዎች ፖስተር እየተለጠፈ ነው›› የሚል ቅሬት በማቅረቡ ምን አልባት አባላት ተሳስተው ለጥፈው ይሆናል ብለው ፖስተሮቹን እንዳነሱ የገለጸው የፓርቲው የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ ወጣት እያስፔድ ተስፋዬ ፖስተሮቹን ካስነሱ በኋላ በድጋሜ እነዚህ ቦታዎች ላይ ያለ ሰማያዊ እውቅና ፖስተሮቹ ተለጥፈዋል ብሏል፡፡ ፖስተሮቹን ለሁለተኛ ጊዜ ለማንሳት የሄዱት የሰማያዊ ፓርቲ አባላትም መታሰራቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
ወጣት እያስፔድ አክሎም ‹‹ከሰማያዊ ፓርቲ እውቅና ውጭ ፖስተሮች እየተለጠፉ ያሉት ገና ሰማያዊ ፖስተር ባልለጠፈባቸው አካባቢዎች ነው፡፡ እኛ ስናነሳ ደግመው ይለጥፋሉ፡፡ ለማንሳት የሚሄዱ አባላትንም ያስራሉ፡፡ ይህን እኩይ ድርጊትም ገዥው ፓርቲ ነው የሚፍጽመው ብለን እናምናለን፡፡ ይህን እያደረገ ያለው ሰማያዊን ሆን ብሎ ለመክሰስ ነው፡፡ ይህንንም ለምርጫ ቦርድ አሳውቀናል፡፡›› ሲል ገልጾአል፡፡ ፓርቲውም ‹‹ይህን ድርጊት ፓርቲያችን እንደፈፀመው ተደርጎ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት በኩል የተሰጠው ማሳሰቢያ ፓርቲያችን አይመለከተውም›› ሲል በደብዳቤው አሳውቋል፡፡

የወያኔ ቡድንን እስከመጨረሻው እናስወግደው

የወያኔ ቡድን ለህዝብ ደንታ እንደሌለው በተለያዩ አጋጣሚዎች እያሳየ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ስደትን በይፋ የጀመረው ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም፤ የሴቶች መብት ይከበር፤ ዲሞክራሲ ያለገደብ፤ እና የተለያዩ የእኩልነት እና የነጻነት ጥያቄ በማንሳታቸው በፖለቲካ አስተሳሰባቸው እና ያለውን መንግስት በመቃወማቸው የደርግ ስርአት ያደርግ የበነበረውን አሰቃቂ ግርፋት ግድያ በአጠቃላይ ስርዓቱ የፈጠረውን አፈናና እና ግፍ ሽሽት እንደሆነ ይታወቃል። ዛሬ ደግሞ በአይነቱም ሆና በብዛቱ ተባብሶ ይገኛል። ህዝባችን ሃገሩ ያለውን ችግር ቢሸሽም ሸሽቶ የሚሄድባቸው ሃገራት ያለውን ሃገር አጥፊ ስርዓት ደጋፊ በመሆናቸው እንደዚሁም የተለያዩ ሃገራት መፈራረስ እና የተለያዩ አሸባሪ ቡድኖች በየቦታው መፈልፈል ከሃገራቸው በስርዓቱ በደል የተሰደደው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚሄደበት መንገድም ሆነ በደረሰበት ሃገር ሁሉ እየተገፋ እና እየተሰቃየ መራራ እና አስከፊ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።
ህዝባችን በተለያዩ ሃገራት ለምሳሌ በየመን የተለያየ ግፍ እና መከራ ሲያሳልፍ መቆየቱ የሚታወስ ነው።በአሁኑ ሰአት ደግሞ የisis ወደ የመን መግባት አስጨንቆት የይድረሱልን ጥሪ እያሰማ ይገኛል።በደቡብ አፍሪካ ያለውም ሁኔታ ሙሉ በሙሉ እንዳልተረጋጋ እዛው ያሉ ወገኖች ይናገራሉ። በሊቢያም ሌሎች ዜጎቻችን በቅርቡ ያሳለፉትን አሰቃቂ ድርጊት እንዳይደግሙ የብዙዎቻችን ስጋት ነው። በአረብ ሃገራትም የሚኖሩ እህቶቻችን እየደረሰባቸው ያለውን መቋቋም እያቃታቸው እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች እየጨመሩ ናቸው።በአውሮፓም ቢሆን የሚደርስብን እንግልት ቀላል የሚባል አይደለም።ባለውለታቸው ነን ብንቸገር ይደርሱልናል ብለን የምናስባቸው ሃገራት ጭራሽ የችግራችን አባባሽ ሆነው ተገኝተዋል ሲሰደዱ የተቀበልናቸው በችግራቸው የደረስንላቸው ውለታችን ከምንም እንደማይቆጥሩት በተግባር አሳይተውናል።
እዚህ ላይ የሚገርመው ከየአቅጣጫው ህዝባችን ለሚደርስበት ችግር የድረሱልኝ ጥሪ የሚያሰማው በተቃዋሚ ሚዲያዎች እንደነ ኢሳት እና ፍኖተ ሬድዮ ላይ መሆኑ ነው። ይህ የሚያሳየው ህዝባችን ባለው ስርአት ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጠ ነው።ህዝባችን መንግስት አልባ ነው የሚለውንም ማረጋገጫ ነው።
በመንግስት ስም የተቀመጠው የወያኔ ቡድን ለህዝብ ደንታ እንደሌለው በተለያዩ አጋጣሚዎች እያሳየ ይገኛል። እንኳንስ ለወገን ሊቆረቆር በሃገር ውስጥ በውጭ ሃገራት የሚደርስብንን በደል ለመቃወም የሚወጡትን የወገን ተቆርቋሪዎች በመደብደብ እና በማሰር ከህዝብ ጎን ከመሰለፍ ይልቅ ህዝብን ከሚያንገላቱት ጎን መቆሙን አሳይቶናል።በሳኡዲ የተቃወሙት ላይ ያደረሰውን ድብደባ ሳንረሳ በሊቢያ isisን ለመቃወም በወጡት ላይ ደግሞታል ይባስ ብሎ ለህዝብ መቆርቆር እና ለወገን ማልቀስን እንደአሸባሪነት ቆጥሮ እየደነፋ ይገኛል።የተለያዩ ሃገራት ከየመን ዜጎቻቸውን በቻሉት ሁሉ እያወጡ ወገንተኛነታቸውን እያሳዩ ባለበት ሰአት ወያኔ የመረጠው በቃላቀባዩ የፌስቡክ ለበጣን ሆኖ ተገኝቷል።ዳሩከዝንብ መቼስ ማር ይጠበቅ እና
ታዲያ የሚያሳዝነው ህዝባችን ይህን ሁሉ መስዋእትነት የሚከፍለው በአምባገነኖች በጠባቦች በባንዳዎች በሆድ አደሮች በንዋይ ናፋቂዎች እና በባእዳኖች መሆኑ ነው። እንደነዚህ አይነት ጥርቅሞች ደግሞ ለወገን ይቆረቆራል ወይም ለሃገር ያስባል ማለት ቀሚሰ ተስፋ ነው።ባእዳኖቹም ቢሆኑ የራሳቸውን ጥቅምትተው ለሃገራችን ያስባሉ ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው።
እንደማንኛውም የህብረተሰብ ጥርቅም እንደነዚህ አይነቶች በሃገራችን ቢኖሩም እራሳቸውን ለሃገራቸው ያሳለፉ እድሜያቸውንም በትግልእየጨረሱ ያሉ እንዳሉ ማወቁ ተገቢ ነው። በአሁኑ ሰአት እንደሚታየውም ከሆዳሞቹ ከባንዳዎቹ ከጠባቦቹ ቁጥር ይልቅ የሃገር ተቆርቋሪው የአንድነት ሃይሉ ሚዛን እየደፋ መጥቷል። ወያኔም እርቃኑን መቅረቱም በቅርቡ ያየነው እውነታ ነው። በመሆኑም የተጀመረው የህዝብ ትግል ከዳር ይደርስ ዘንድ በየቦታውየሚሰቃየው የህዝባችን ሰቆቃ ይቆም ዘንድ የራሳችን የሆነ የሚቆረቆርልን በህዝብ የተመረጠ መንግስት ይኖረን ዘንድ ከእስከዛሬው በበለጠ ተደራጅተን እና አንድ ሆነን ትግላችንን በማጠናከር ይህን ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሳው የወያኔ ቡድንን እስከመጨረሻው እናስወግደው።
ህዝብ ያሸንፋል!!!!!!!!!!!!

የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያቀረቡት አስቸኳይ ጥሪ

የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያቀረቡት አስቸኳይ ጥሪ
የተከበራችሁ ወገኖቼ፤ ከሰላሳ በላይ የሆኑ ወገኖቻችን አይ ሲስ በተሰኘ ህሊና ቢስ፣ ፀረ-ሰው እና ፀረ-ስልጣኔ ቡድን በሊቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ የመገደላቸው መርዶ ከትናንት ወዲያ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓም ደርሶን ኢትዮጵያዊያን በያለንበት በመሪር ሀዘን ውስጥ ነን። ዛሬ “እግዜር ያጥናህ” ወይም “እግዜር ያጥናሽ” የሚባል ሰው የለም። ሁላችንም ሀዘንተኞች ነን። ካጣናቸው ቁጥራቸው በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ወገኖቻችን አሁንም በአራዶች መዳፍ ውስጥ መሆናቸው ሀዘናችን እጅግ የበረታ ያደረገዋል። ቁጥራቸው በትክክል የማይታወቅ ሆኖም በሺህ የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም ሊቢያ ውስጥ ናቸው። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን አሁንም ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ናቸው። ሌሎች በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ደግሞ በየመን ከሰማይም ከምድርም በቦንብና በጥይት እየተማገዱ ነው።
ለምንድነው ኢትዮጵያዊያን እንዲህ እሳት ውስጥ ለመማገድ የምንደፍረው? መልሱ ግልጽ ነው። አገር ውስጥ ተስፋ የለም፤ ወያኔዎች ተስፋችንን አጨለሙት። ከሳዉዲ በመከራ የተመለሱ ወንድሞቻችን ናቸው በሊቢያ በኩል ለመሰደድ ሲሞክሩ በአይ ሲስ ተይዘው የታረዱት። ወያኔዎች አገራችንና ክብራችን ዘረፉን። ወያኔዎች ስብዕናችንን ገፈፉን።
የዘመኑ ጥቂት የህወሓት ቱጃሮች ፎቆችን እየገነቡ በነሱ መጥገብ እኛ እንድናገሳላቸው ይፈልጋሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ መራቡ፣ መታረዙ፣ መደህየቱ እውነት ነው፤ ሆኖም ግን “ተራብኩ”፣ “ታረዝኩ”፣ “ደኸየሁ” ብሎ መናገር አይችልም። እውነት መናገር ያስቀጣል፣ ያስወነጅላል። በፍርደ ገምድል ችሎት እውነት መናገር “ሽብርተኛ” ያስብላል። እስር ቤቶችን የተሞሉት ለእውነት፣ ለፍትህ፣ ለነፃናትና ለእኩልነት በቆሙ ሰዎች አይደለምን?
በአይ ሲስ ያሳረደን ማነው? መልሱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ነው። ያዋረደን፣ በአይ ሲስ ቢላዋ ያሳረደን ህወሓት ነው። እንደ አገርና እንደ ሕዝብ የደረሰብን ውርደት የትም ብንሄድ የምናመልጠው አልሆነም። በአገር ውስጥ የደረሰብንን ውርደት ለማምለጥ ስንሰደድ ውርደት ተከትሎን ይመጣል።
ወገኖቼ፤ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ የተሻለች አገር ሊኖረን አይችልም። ዛሬ የመሸሻ ጊዜ አይደለም። አገራችንን ከወያኔ ነጥቀን፤ በአገራችን ኮርተን በሰላም መኖር እንሻለን። ይህ መብታችን ነው። አገራችን የኛ ነች። አገራችን የጥቂት ወያኔዎች መፈንጫ አይደለችም።
ወገኔ፤ ዛሬ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓም በአርበኖች ግንቦት 7 ስም የማደርግልህ ጥሪ አድምጠኝ። በሀይማኖት፣ በብሔር፣ በጾታ ልዩነት ሳታደርግ ዛሬ በአንድነት እንደተሳህ አንድነትህን እንደጠበቅህ ቀጥል። አንድነትህን ለመሸርሸር ወያኔ የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም፤ ለወያኔ ዱለታ ጆሮህን አትስጥ። የወያኔ አገዛዝ እንዲያበቃ በአንድነት ተነስ። ዛሬ የጀመርከው ትግል እዳር ሳይደርስ እረፍት የለንም።
አርበኞች ግንቦት 7፣ ከትግራይ፣ ከኦሮሚያ፣ ከአፋር፣ ከኦጋዴን፣ ከጋምቤላ፣ ከቤሻንጉል ድርጅቶች ጋር በመጣመር የአገር አድን ኃይል የመገንባት ሥራውን እያጠናቀቀ ነው። እኛ ልጆችህ በብሔርም ሆነ በሀይማኖት ሳንከፋፈል፤ ከትግራይ እስከ ኦጋዴን፤ ከአፋር እስከ ጋምቤላ ሁሉንም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ባካተተ ስብስብ ውስጥ አብረን ህወሓትን እየታገልን ነው። ይህ ትግል ግን የአንተ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ነው። የትግሉም የአገሪቷም ባለቤት አንተ ነህ። ስለሆነም ተነስ! “እንቢኝ” በል። ዘርፈ ብዙ የትግል ስልቶችን በመጠቀም ወያኔን አዳክም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! በትግልህ ፍሬ የአገርህ ባለቤት ሁን።
የመከላከያና የፓሊስ ሠራዊት አባላት ሆይ!እናንተ የሕዝብ አካላት ናችሁ። የደረሰብንን ብሔራዊ ውርደት እያያችሁ፤ እሮሮዓችን እየሰማችሁ በሕዝብ ላይ መተኮስ በራሳችሁ ጭንቅላት ላይ መተኮስ ማለት መሆኑን ለደቂቃ እንኳን አትዘንጉ። ይልቁኑ ዛሬውኑ ነፃነትና ፍትህ ከጠማው ወገናችሁ ጎን ቁሙ።
የኢትዮጵያ ወጣቶች፤ የወጣትነት የፈጠራ ችሎቻችሁ መፈተኛው አሁን ነው። ለእያንዳንዱ ጥቃቅን ጉዳይ መመሪያ እስኪሰጣችሁ አትጠብቁ። እያሰላችሁ፣ እያጠናችሁ፣ እያደባችሁ፣ ወያኔን ታገሉ።
የታፈረች፣ የተከበረችና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን።

ሰው በአሹቅ ብቻ አይኖርም !


ሰው በአሹቅ ብቻ አይኖርም !
(አሌክስ አብርሃም)
‹‹ጥጋብ ፍንቅል አድርጓችሁ ነው የተሰደዳችሁት እንጅ …አገራችሁ ማሩ ወተቱ …›› ማለት ‹‹ጠግባችሁ ሂዳችሁ ነው የታረዳችሁት እንኳን የእጃችሁን አገኛችሁ ›› ከማለት አይተናነስም !!አሁን ከትላንት ወዲያ ታዋቂው የማስታወቂያ ባለሙያ አርቲስት ሰዊት ፍቅሬ ጨርቆስ ሃዘን ቤቱ ንግግር እንዲያደርግ ተፈቅዶለት በሚያስገመግም ድምፁ እንዲህ አለ ‹‹ ከሰው አገር ወርቅና ብር እናታችን እቅፍ ውስጥ አሹቅ እየበላን ሙቆን ብንኖር ይሻላል›› ቆይ እውነቱን እናውራ እንጅ ! የታለ ጥጋቡ … የታለ ስራው … የታለ አሹቁ….እንዴዴ ….ምናይነት በሰው ህይዎት ላይ መቀለድ ነው ይሄ ! ሰው እኮ እንስሳ አይደለም …በልቶ ጠጥቶ ሆዱ ከሞላ መተኛት ብቻውን በቂ ነው ሊባል አይገባም !
እከሌ መቶ ሽ ብር ከፍሎ ተሰደደ ለምን እዚሁ አይሰራባትም የሚል የዋህ ሒሳብ የሚያሰሉ ሰዎች ገጥመውኛል ….እጁ ላይ አፈር ከድቤ በልቶ ያጠራቀማትን ገንዘብ እየበላ አጨብጭቦ ከሚቀር ....ስደት ላይ ኢንቨስት ሊያደርግ ወሰነ በቃ ….ለምን አገሩ ላይ ስራ አይሰራባትም ….አገራችን ላይ ስራ እድል በሆነበት በዚህ ጊዜ መቶ ሽ ብር ምን እንደሚሰራ ሁላችንም እናውቃለን ….ቤት ልከራይ ቢባል የስድስት ወር ኪራይ የአመት ኪራይ በአንዴ በሚጠየቅባት አገር ….መቶ ሽ ብር እና ከዛ ያነሰ ብርን እንደትልቅ ካፒታል የሚቆጥር ሰው …ምናልባት ነፍሱ ድሮ ላይ የቆመ ሰው ይሆናል !
እናቴ ያሳደገችኝ እኮ እሷ ስር ተወሽቄ አሹቅ እንድበላ አይደለም ! የተሻለ ኑሮ እሻለሁ …ለእናቴ ላሳልፍላት እፈልጋለሁ … ቤት እፈልጋለሁ የተሻለ ትምህርት እፈልጋለሁ ማግባት መውለድ ለቤተሰቤ አለኝታ መሆን እፈልጋለሁ ! ልጆቸ ጥሩ ትምህርት ቤት እንዲማሩ ጥሩ እውቀት እንዲኖራቸው እፈልጋለሁ ….አሹቅ እየበላሁ ነገ ይሄንኑም አሹቅ ያጡ ልጆችን መፍጠር አልሻም ! አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ህዝብ የሚሰደደው ደላላ ስለደለለው ወይም አገሩን ስለጠላና …አገሩ ላይ ((ሚሊየነር መሆን ስለደበረው)) አይደለም ! ከእለት ጉርስ ያለፈ ነገር ማግኘት ዘበት ስለሆነበት ለፍቶ ጠብ የሚል ነገር ስላጣ ነው !! ዛሬን ብቻ አይደለም ማሰብ …ዛሬ ለፍቶ ጉልበቱን ገብሮ ይኑር ነገስ እድሜው ሲገፋ ነገስ ልጆች ሲወልድ ….ነገስ ነው ጥያቄው ! እህት ወንድሞቹ ለእግራቸው ጫማ ሲያጡ እየተመለከተ አሹቁን እየቃመ ቁጭ የሚል ልብ ያለው ሰው የለም !
ተው እንጅ ባለቢላዎቹ ሲገርሙን የብሶት አንገታችንን በቃል ስለታችሁ አትረዱን ! በመጀመሪያ ድግሪ ሁለት ሽ ብር እንኳን በማትከፍል አገር … ጠግባችሁ ተሰደዳችሁ ይባላል እንዴ ….ስደት በባህሪው እኮ ተፈጥሯዊ ህግ አለው ….ካልተሸለ ቦታ ወደተሸለ ቦታ መሄድ ማለት ነው ! አገራችን የተሻለች ብትሆንማ እንኳን እኛ ልንሄድ ሌሎችም ወደኛ በተሰደዱ ነበር ! ጠላታችን ድህነት ነው ብለን አውጀናል እኮ … አቅም ያለው ድህነትን ይፋለመው አቅም ያጣ ደግሞ ከጥላት ቀጠና ማፈግፈጉ የጦርነት ህግም ነው ! ጦርነት እውነት ነው ጨካኝ ጠላት ነው ….በመፎክር ብቻ አይመለስም ! ስጋህን ብቻ ሳይሆን ነፍስህንም አጋድሞ ያርድሃል !
ድህነት ያባረረውን ህዝብ ስደተኛን ተቀባዮቹ ግፍ ዋሉበት ይሄ ነው እውነቱ ! እስቲ አሁን ዝቅ ብሎ መስራትን ከጨርቆስ ልጆች የበለጠ ማን ያውቃታል …. ዝቅ ተብሎም ጠብ የሚል ነገር ጠፋ ሄዱ ! እና ስራ ንቀው እንል ዘንድ ተገቢ ነው እንዴ …. ለምን ወሬ እናሳምራለን …. አስር ጊዜ ‹‹ደላላ እያታለላቸው ›› ይላል ሚዲያው …ከኑሯችን የበለጠ ደላላ የለም ! እንደውም ለስደት የሚገፋፉ አንደኛ ደላሎች የማስታወቂያ ባለሙያዎች ናቸው !
አሹቅ ብሉ ዳቦ ብሉ ….የተፈጠርኩት አሹቅ እየበላሁ ጮማ የሚቆርጡ ሰዎችን ምራቄን እየዋጥኩ እንድመለከት አይደለም ! ለዚህ ደግሞ ሰው ነኝና መጀመሪያ አገሬ ላይ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ ለመስራት እሞክራለሁ …. አገሬ የልፋቴን ካልከፈለችኝ በተለይ ደግሞ ከእኔ በታች የሚደክሙትን እያነሳች አናቴ ላይ ካስቀመጠች … ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ከሌለ …ከሰውነቴ ይልቅ ባለኝ ገንዘብና ደረጃ የምመዘን ከሆነ ….እንደሰው የምቆጠርበት ተንቄም ቢሆን የተሸለ የገንዘብ አቅም የተሸለ ነገር የማገኝበት ቦታ ሁሉ ምርጫየ የማይሆንበት ምክንያት የለም !
‹‹እናትህ እቅፍ ውስጥ ሁነህ አሹቅም በልተህ ቢሆን መኖር ይሻላል ››ይሉት ቀልድ …አሹቅ እየበላህ የእኔን ማስታወቂያ እየተመለከትክ በአምሮት ኑር ከማለት ውጭ ምን ትርጉም ይኖረዋል ! እንዴ ራሳቸው የማስታወቂያ ባለሙያዎቹ አይደሉ እንዴ …‹‹ለበዓል ለእናትሽ ብር ላኪ በዚህ ባንክ መንዝሪ›› እያሉ የተሰደደው ሁሉ ሃብታም የተሰደደው ሁሉ ላኪ መንዛሪ መሆኑን እንቁልልጭ እያሉ ለስደት የሚገፉን …የምን ዞሮ ‹‹አሹቅ ቂጣ›› እያሉ በሰው ቁስል እንጨት መስደድ ነው ! እስቲ ሃቁን እናውራ በቴሌቪዥን ከሚሰራጩ ማስታወቂያዎች አንድ እንኳን ‹‹የአሹቅ በሊታዎች›› ማስታወቂያ አይታችሁ ታውቃላችሁ ?…. አሹቅ እየበላሁ ነው ኢንሹራንስ የምገባው? ….አሹቅ እየበላሁ ነው የተንፈላሰሰ ቪላ በሶስት ጊዜ ክፍያ የምገዛው ?…አሹቅ እየበላሁ ነው ….መኪና የማማርጠው? ….አሹቅ እየበላሁ ነው ዱባይ ያለ ምግብ ቤት የምዝናናው? …. አሹቅ እየበላሁ ነው ባለምናምን ኮከብ ሆቴል የምዝናናው ?… አሹቅ እየበላሁ ነው ለቴሌቶን ሚሊየን ብር የማዋጣው?
‹‹ፍሪጅ ከሌለዎት ምኑን ኖርኩት ይላሉ ›› የምባለው ፍሪጁን አሹቅ እንዳስቀምጥበት ነው ??…..ለምን ስራችን እና ስብከታችን ዬቅል ይሆናል ….በእርግጥ ስደት አስቀያሚ ነው ….ግን አገር ላይ በድህነት እንደመገፋት የባሰ አሰቃቂ ነገር የለም ! ሚሊየኖች በቤት ኪራይ ችግር በተንገሸገሹበት ሰዓት … እልፎች በስራ አጥነት ችግር ድግሪያቸውን እንደዣንጥላ እራሳቸው ላይ አድርገው በየማስታወቂያ ሰሌዳው ስር በሚንከራተቱባት ሰዓት ‹‹ጠግባችሁ ተሰደዳችሁ ›› ማለት …ሌላ እርድ ነው ! እንደው እነዚህ ወገኖቻችን በግላጭ በአደባባይ በግፍ ሲገደሉ አየን እንጅ በየጓዳው ስንቱ ነው የተራዘመ የችግር ሞት የሚሞተው ?! አሁንም ደላላ መርገም ስደተኛውን ተቀፅላ ስም እየለጠፉ ማሸማቀቅ መፍትሔ አይሆንም ….ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ….ለህዝቡ እንደልፋቱ የሚከፈልበት ስርዓት …. ሙስናን የሚፀየፍ አስተዳደር …. እናም ጠንካራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና አፈፃፀም ያስፈልገናል ! ‹‹አህያውን ፈርተን ዳውላውን ››አይነት ከንቱ ልፈፋ የትም አያደርስም ! ህይዎት ብዙ መሻት ብዙ የማይገደብ ፍላጎት አላት …..ሰው በአሹቅ ብቻ አይኖርም!