Tuesday, 28 April 2015

ወይ ይች ሀገር!!

ወይ ይች ሀገር!!
ሼህ መሀመድ ሁሴን አል አሙዲን ለክሊንተን ፋውንዴሽን በ2006 ዓመተ ምህረት 20 ሚሊዮን ዶላር መስጠታቸውን ፒተር ስዋይዘር የተባሉ ጸሀፊ በቅርቡ ለህተመት በሚያበቁት መጽሀፋቸው ላይ በይፋ አጋልጠዋል። (እንኳን 20 ለምን 200 ሚሊዮን ዶላር አይሰጣቸውም? ብለን ዝም እንዳንል፤ ስጦታው የተሰጠው በኢትዮጵያ መንግስት ስም መሆኑ ያማል።ይህንንም አል አሙዲ -ለፋውንዴሽኑ በጻፉት ደብዳቤ አረጋግጠዋል። ለምን በኢትዮጵያ መንግስት ስም ሰጡ? የስጦታው ምክንያት ምንድነው?የሚል ጥያቄ ከተነሳ፤ አል አሙዲ በዚያው በስጦታ ደብዳቤያቸው ላይ ፦የቡሽ አስተዳደር የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ-በክሊንተን ጊዜም ሳይቀየር እንዲቀጥል መማጸናቸው(መጠየቃቸው)ተመልክቷል።
ያንንም ተከትሎ በባለቤታቸው ስም ገንዘቡን የተቀበሉት የወቅቱ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሄላሪ ክሊንተን የአሜሪካ መንግስት በኢህአዴግ ላይ ማእቀብ እንዲጣል ያረቀቀው አዋጅ እንዲሰረዝ ፣ ይልቁንም አሜሪካ ለኢህአዴግ አስፈላጊውን እርዳታ እንድትሰጥ ማስደረጋቸውን ደራሲው አጋልጠዋል።
(እየተዛቀ የሚወጣው የሻኪሶ (የሀገሬ)ወርቅ፤ ሀገሬን ለማፈን እንደሚውል መስማት እንዴት ያማል!!!)
“ኢህአዴግ እንድሆን ያጠመቀኝ አሰፋ ማሞ ነው” አል-አሙዲ
ለማንኛውም ይህ የአል አሙዲን እና የክሊንተን ጉዳይ በፎክስ ኒውስ ሰፊ ሽፋን ያገኘ ወቅታዊ አጀንዳ ሆኗል። ሊንኩ ከታች አለ፤ ያዳምጡት፦ አረዳው ፎክስ ኒውስ ትልቅ አጀንዳ ነው የሰጠህ። ለጊዜው እገሊትና እገሌን ተዋቸውና ይህን ጉዳይ ተወያይበት፣ተነጋገርበት..ከዚህ (ከሀገር)የሚበልጥ አጀንዳ የለም።
http://www.realclearpolitics.com/…/fox_news_special_the_tan…


ስንታየሁ ቸኮል በደህንነቶች ታፈነ!

ስንታየሁ ቸኮል በደህንነቶች ታፈነ
የቀድሞው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ የነበረው እና በአሁኑ ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው አቶ ስንታየሁ ቸኮል ዛሬ ሚያዝያ 20/2007 ዓ.ም በደህንነቶች ታፍኖ ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዱን ምንጮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ጠዋት 12 ሰዓት ላይ አራት ሲቪል የለበሱ ደህንነቶች ‹‹ትፈለጋለህ!›› በማለት በመኪና አፍነው ወዳልታወቀ ቦታ የወሰዱት ሲሆን ለእስሩ ምንም አይነት ምክንያት ወይንም መጥሪያ እንዳልሰጡት ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡ ቤቱን የፈተሹት አራቱ ደህንነቶች ምክንያታቸውን እንዲያስረዱት የጠየቀው አቶ ስንታየሁ ላይም ከፍተኛ ድብደባ እንደፈፀሙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ መንግስት የከፈተበትን የጥላቻ ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳሰበ

ሰማያዊ ፓርቲ መንግስት የከፈተበትን የጥላቻ ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳሰበ
April 27, 2015
Semayawi Parties latest press conferenceመንግስት ሊቢያ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ላይ አሰቃቂ እርምጃ የወሰደውን አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም ራሱ በጠራው ሰልፍ ላይ ከህዝብ የገጠመውን ተቃውሞ ተከትሎ ሰማያዊ ላይ የጥላቻ ዘመቻ እንደከፈተበትና ይህንን የጥላቻ ዘመቻውን እንዲያቆም ሰማያዊ ፓርቲ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አሳስቧል፡፡Semayawi Parties latest press conference
መንግስት የጠራውን ሰልፍ ከማንም ተቃዋሚ ፓርቲ ቀድሞ የደገፈው ሰማያዊ እንደሆነ የገለጸው መግለጫው ‹‹የዜጎችን ስቃይ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል የፈለገው ህወሓት/ኢህአዴግ ሰማያዊ ፓርቲ በወገኖቻችን ላይ ለሚደርሰው በደል መፍትሄ እንዲሰጥ መወትወቱ፣ የፖለቲካ ልዩነታችንን ወደ ጎን አድርገን በሰልፉ ላይ መገኘታችን እንዳላስደሰተው ከሰልፉ ቀን ጀምሮ በፓርቲያችን ላይ የተከፈተው ዘመቻ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡›› ብሏል፡፡
ከሰልፉ ማብቃት ጀምሮም ጉዳዩን ገና ፖሊስ ሳይመረምረው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን ሰማያዊ ፓርቲ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት እየጣረ ነው በሚል መወንጀላቸውን፣ የመንግስት ሚዲያዎች ሰማያዊ ፓርቲ ሁከትና ብጥብጥ ሊያስነሳ ነው ብለው ሚዛናዊ ያልሆነ መረጃ ማሰራጨታቸውንና አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም ተብለው በተጠሩ ሰልፎችም ሁሉ መንግስት ሰማያዊ ፓርቲ ለመቃወም እየተጠቀመባቸው መሆኑን መግለጫው አትቷል፡፡
በተጨማሪም በሰልፉ ዕለት የሰማያዊ አባላት ገና ሰልፉ ሳይጀመርና መስቀል አደባባይ ሳይደርሱ እንዲሁም ሰልፉ ካበቃ በኋላ እየታደኑ ሲታሰሩ መስቀል አደባባይ ላይ የተያዙት የኢህአዴግ አባላት ከቀበሌ ደብዳቤ እያመጡ መፈታታቸው መንግስት ሰማያዊን በሀሰት ለመወንጀል መነሳቱን ያሳያል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል 6 ያህል የሰማያዊ አባላት በታሰሩበት ሁኔታ መንግስት 7 አመራሮችና 20 ያህል አባላት ታስረዋል ማለቱ ትክክል አለመሆኑንና ከመጀመሪያውም 6 አባላቱ የታሰሩበት መንገድና አሁንም በሰማያዊ ላይ የሚቀርበው ክስ መሰረተ ቢስ ነው ብሎታል፡፡
‹‹ይህ በህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት አማካኝነት እየቀረበ ያለው ክስ እና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ህወሓት/ኢህአዴግ ለዜጎች ህይወት የማይጨነቅ እና በዜጎች ሞት የራሱን የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ እና ጠንካራ ተቃዋሚ የሆነውን ሰማያዊ ፓርቲን ለማጥቃት እየተጠቀመበት መሆኑን በተጨባጭ የሚያሳይ ነው፡፡›› ሲልም የመንግስትን ተግባር ተቃውሟል፡፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተሰጠበትን ጉዳይ ተጠርጣሪ ከማለት ይልቅ ወንጀለኞች ናቸው በማለት በህገወጥ ስራ እንደተሰማራ ያሳያል ሲልም ወቅሷል፡፡
‹‹መንግስት እና የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ከዚህ አኩይ ተግባራቸው የማይታቀቡ ከሆነ፣ የሰማያዊን ስም በሀሰት በማጠልሸት ስራ ላይ የተሰማሩ የመንግስት ተቋማትን እና ግለሰቦችን በህግ ፊት ለማቆም ይገደዳል›› ያለው መግለጫው ሌሎች ተከታታይነት ያላቸውን እርምጃዎችም እንደሚወስድና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሰማያዊ ፓርቲ ለሚያደርጋቸው ህዝባዊ ጥሪዎች በንቃት ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በአማራ ክልል ብቻ እሚካሄድ ሰሞኑኛ ወንጀል

በአማራ ክልል ብቻ እሚካሄድ ሰሞኑኛ ወንጀል 

በአማራ ክልል አሁንም ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት እንደቀጠለ ነው። የወያኔ ሎሌዎች በየገጠሩ እየዞሩ አማራውን ጠመንጃችሁን ካላስመዘገባችሁ ማዳበሪያ አታገኙም እያሉ በማስፈራራት አማሮች ሳይወዱ በግድ ጠብመንጃቸውን እያስመዘገቡ ይገኛሉ። ያስቸግራሉ የተባሉትን ደግሞ እየተቀሙ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህም እየተደረገ ያለው ሁለት ነገር ነው፤ 
1- እንደተለመደው ወያኔ ለአማራው ባለው የማይለውጥ ጥላቻና ንቀት የተነሳና ፤
2- ኮሽ ባለች ጊዜ የተመዘገበውን ጠብመንጃ በየቤቱ ለመልቀም ያመቸው ዘንድ ነው። ወያኔ ሌት ተቀን እንደሚደሰኩረው መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲ ካሰፈነ፡ አማራውን ለምን ጠመንጃውን ይቀማል? በትግራይ ህዝብ ላይ የማያደርገውን በአማራው ህዝብ ላይ የመሳሪያ መቀማትና የትጥቅ ማስፈታት ያለምክንያት አይደለም “ጅብ ቀን ቀን የምትደበቀው ለምንድነው ሲሉት፡ ሌሊት ሌሊት የምሰራውን ስለማውቅ ነው” እንዳለው ሁኖበት እንጂ። እና በአማራው ህዝብ ላይ ወያኔ እየሰራው ያለው ጉድ ወይንም ወንጀል እንዳለ ከዚህ በላይ ምን ይኖራል? በነገራችን ላይ ይሄ መሳሪያ ማስፈታት ገንዘብ የሚያስገባ መሆኑም መዘንጋት የለበትም። ከሁሉም የሚያበሳጨው ግን ለህዝብና ለሀገር ሲል አጥንቱን የከሰከሰን፥ ደሙን ያፈሰሰንና እንደጧፍ የነደደት ህዝብ ማክበር ሲገባ፡ በነፍጠኝነትና በጠላትነት ተፈርጆ ማንም እየተነሳ ሲገድለው፤ ሲሰድበው፤ ሲያንኳስሰውና ሲዘለፈው ቆሞ የሚያይ አማራ ሲገኝ ነው። አማራው ዛሬ ማንም ጎጠኛ እየተነሳ አፉን ሊያፍታታበት የቻለው አማራው ለራሱ ሳይኖር ለሌላው ኖሮ ሳለ አማራውን ወያኔና በወያኔ ብርና ዶላር ገፋፊነት ወረቀት የሚያበላሹ ቅጥረኞቹ ጸሀፊና ጋዜጠኛ በሉኝ ባዮች አማራውን የስህተትና የጥፋት ቋት በማድረግ ለህዝብና ለአገር ያደረገውን አንዳች ነገር እንደሌለ በመካድ ነጋ ጠባ ውንጀላን በመደርደር ዋሾ ቅጥረኛ በመሆናቸው ነው። ከነዚህ ቅጥረኞች በተጨማሪ ተማርን ብለው የአማራን ታሪክ አጣመው በምሁርነት ካባ የሚጽፉ ሆዳሞችም አልጠፉ። እነዚህም ቢሆኑ በጠላትና በፈረንጅ ትምሀርት ቤቶች ገብተው የክህደትና መሀይምነት ዶክተሮች የሆኑ ናቸው። በነገራችን ላይ ወያኔ በአማራ ላይ የሚያደርሰው ሁሉ የጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻ አካል ነው። ይህንን ዝም ብሎ የሚያይ የአማራ ልጅ ያልታደለና የተደየነ ብቻ ነው። የወያኔው የእጅ ስራ የሆነው ብዓዴን እንደሆነ የአማራን ህዝብ ከከዱትና ከጠሉት ከራርመዋልና የአማራን ህዝብ ይታደጋሉ ብሎ መጠበቅ ፋይዳ ቢስነት ነው። ብዓዴን ስለአማራ ይሉኝታን ከገደለ ከርሟል። በዚህም የተነሳ ወያኔ ካፈጣጠሩ አንስቶ በብዓዴን ሽፋን የአማራን ህዝብ ከማጥፋት ሌላ ራሱም በቀጥታ ተሰማርቶ ህዝባችንን እየፈጀው ይገኛል። ስለዚህ መላ ያማራ ተወላጅ የሆንህ ሁሉ ቆሻሻውንም ከጫንቃህ ላይ አንሳና ተነሳ። ስለዘርህ ስትል ዛሬውኑ ስርየትንና ንጹህነትን ፈላጊ ሁን። እና በዚህ ያደቆነኝ ሰይጣን ይጨርሰኝ ባዮች በበዙበት አገራችን ውስጥ የህዝባችን መጥፋት የሚቆጭህ ወዲህ በለኝ። የተማርን ነን የምንል የአማራ ተወላጆች ደግሞ የአማራውን ሙሉና ሀቀኛውን ታሪክ እናስተምር! ሁላችንም አማራን ስለመታደግ የምንችለውን ሁሉ እናደርግ ዘንድ ጥሪ አስተላልፍላችኋልችሁ።

Wednesday, 25 March 2015

“ኢህአዴግ የህዝቡ ብሶት አደጋ እንደሚያስከትል አውቋል” ስትል የአዲስ አበባ የኢህአዴግ የሴቶች ሊግ ም/ል ሊቀመንበር ተናገረች

የሊጉ ም/ል ሊቀመንበር በመሆን ለአመታት ያገለገለችው ወ/ት እየሩሳሌም  አበረ  ከኢሳት ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ “የአዲስ አበባ ህዝብ እንደሚገነፍል በርካታ የዲሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እያነሳ ነው” ብላለች።የታፈነ የመልካም አስተዳደር እና የዲሞክራሲ ጩኸት አለ የምትለው ወ/ት እየሩሳሌም፣ ገዢው ፓርቲም ህዝቡ በከፍተኛ ብሶት ላይ እንደሚገኝና አደጋ ሊያስከትል እንደሚችልም ጠንቅቆ ያውቀዋል ብላለች።ከምርጫ 97 በሁዋላ ኢህአዴግ የተሳካለት ነገር ቢኖር ተቃዋሚዎችን ማፈን ነው የምትለው ኢየሩሳሌም፣ ህዝቡ በሚታየው ነገር ሁሉ ባለመርካቱ ገዢው ፓርቲ ቁጥጥሩን በማጥበቅ የህዝቡን ብሶት ለማፈን ይሞክራል ስትል አክላለች።ወ/ት እየሩሳሌም ድርጅቱን ጥላ ስደትን መርጣለች። ለረጅም አመታት የአዲስ አበባ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ እና በሌሎችም የስልጣን ሃላፊነቶች ላይ ሲሰሩ የቆዩት የኦህዴድ ድርጅት አባል የሆኑት ወ/ሮ አበባ ገብረስላሴም በቅርቡ ኢህአዴግን በመተው፣ በአሜሪካ ጥገኝነት ጠይቀዋል። ከወ/ት እየሩሳሌም ጋር የተደረገው ቃለምልልስ ሰሞኑን ይቀርባል።

የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ለ8ኛ ጊዜ ተመለሰ

• ኢብኮና የአዲስ አበባ አስተዳደር መገናኛ ኤጀንሲ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት መልሰዋል
• ‹‹አማራጫችን እንዳናቀርብ እየተከለከልን ነው›› አቶ ዮናታን ተስፋዬ
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የአዲስ አበባ አስተዳደር መገናኛ ኤጀንሲ የሰማያዊ ፓርቲን የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ‹‹አናስተላልፍም›› ብለው መመለሳቸውን ድርጅቶቹ ለፓርቲው በላኳቸው ደብዳቤዎች ገልጸዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ መጋቢት 16/2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የብሔራዊ ራዲዮ በአማርኛ ስርጭት የሚተላለፍ ‹‹መንግስታዊ አወቃቀር›› የሚል የቅስቀሳ መልዕክት ልኮ የነበር ሲሆን ባለፉት 24 አመታት ተግባራዊ የሆነው የጎሳ ፌደራሊዝም ለግጭት መንስኤ መሆኑን በመረጃ ዘርዝሮ ማቅረቡን የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
ይሁንና ኢብኮ ይህን የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹በተለያዩ ጊዜያት በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ተከሰቱ ያሉትን ግጭቶች በመዘርዘር በህዝቦች መካከል ሌላ ግጭት እንዲቀሰቀስና እንዲባባስ የሚያደርጉና ግጭት የሚያራግቡ፣ አንዱን ብሔር ከሌላ ብሔር የሚያገጩ ናቸው፡፡›› በሚል እንደማያስተላልፍ ገልጾአል፡፡ ከዚህም ባሻገር በመልዕክቶቹ ውስጥ ‹የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት›፣ እንዲሁም ‹የህወሓት/ኢህአዴግ ስርዓት› የሚለው አገላለጽ የፓርቲውን ህጋዊ መጠሪያ የማይወክል በመሆኑ›› በሚል እንደማያስተላልፍ ገልጾአል፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ ግጭቶች በአሁኑ ወቅትም የቀጠሉና የጎሳ ፌደራሊዝሙ እስካለ ድረስ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍሉ መሆናቸውን የገለጸው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ መልዕክቶቹ ከፓርቲው ማንፌስቶ የወጡ፣ ኢብኮ እንዳለው ለግጭት ሳይሆን ከግጭቶቹ መማር እንዲቻልና አሁን ያለው የጎሳ ፌደራሊዝም ከተስተካከለ ችግሮቹ እልባት እንደሚያገኙ በሚያሳይ መልኩ የተላለፈ መልዕክት ነው ብሎአል፡፡ ‹‹እኛ ያቀረብነው አማራጫችን ነው፡፡ አማራጫችን ስናቀርብ ደግሞ የጎሳ ፌደራሊዝም የፈጠረውም ቀውስም በማሳያነት ማቅረብ አለብን፡፡ ይህን እውነታ የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት ዘግበውታል፡፡ አብዛኛዎቹ መንግስትም ያመነባቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ስርዓቱ የሰራቸው ጥፋቶች ይፋ አውጥተን እንዳናቀርብ ስለተፈለገ መልዕክቱን መልሰውታል፡፡ በግልጽ አማራጫችን እንዳናቀርብ ተከልክለናል›› ሲል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ አስተዳደር መገናኛ ኤጀንሲ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹ከሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ ጋር የሚጻረር፣ ብሔር ብሄረሰቦችን ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዲያመሩ የሚገፋፋ፣ የሌላ ፖለቲካ ፓርቲን ስም የሚያጎድፍ ይዘት የተካተተባቸው›› ናቸው በሚል መልሷል፡፡ ይህ የሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ሲመለስ ለ8ኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የአባይ ግድብ ግንባታን በየደረጃው የሚቆጣጠረውን ስምምነት ፈረመች

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በጋራ የፈረሙት አዲሱ ስምምነት ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ በሙሉ ነጻነት የምትሰራውን ስራ እንደሚገድብ ከአረብኛ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመው  ሰነድ አመልክቷል።ሰነዱ ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት በምታደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴና በየትኛውም የግንባታ ደረጃ ላይ አለማቀፉ አጥኝ ቡድን ለሚሰጠው አስተያየት ተገዢ በመሆን እንድትተገብር ይገልጻል። አጥኝ ኮሚቴው የግድቡ ግንባታ የግብጽንና ሱዳንን የውሃ ድርሻ መጠንይቀንሳል ወይም በግብጽና ሱዳን አካባቢያዊ ሁኔታ ላይ ተጽአኖ ያመጣል የሚል ድምደማ ላይ ከደረሰ ካሳ እስከመክፈል የሚያደርስ ግዴታም መጣሉ ተመልክቷል።አጥኚ ቡድኑ የመጨረሻውን የጥናት ውጤት ይፋ ካደረገ በሁዋላ ሶስቱም አገራት እንደሚቀበሉት የተስማሙ ሲሆን፣ ምናልባት አጥኝ ቡድኑ ግድቡ በግብጽና ሱዳን ላይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ያስከትላል ብሎ ቢወስን ኢትዮጵያ የግድቡን ቅርጽ እስከመቀየር ልትደርስ ትችላለች።

ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ፣ ከግብጽና ሱዳን የውሃ ማጠራቀሚያዎችን የሚጎዳ ከሆነም ኢትዮጵያ አገራቱን ፈጥና የማሳወቅና ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርባትም ስምምነቱ ይገልጻል።የስምምነቱ አብዛኛው ክፍል ኢትዮጵያ ስለምትፈጽማቸው ግዴታዎች ትኩረት ያደረገ ነው። ግብጽና ሱዳን ለአባይ ወንዝ የሚያበረክቱት የውሃ ድርሻ ካለመኖሩ አንጻር ስምምነቱ በዋነኝነት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን መብት የሚገድብ ብቻ ሳይሆን፣ የአባይ ግድብ
ግንባታ እጣ ፋንታን ከኢትዮጵያ እጅ አውጥቶ በአለማቀፍ አጥኚዎች እጅ እንዲሆን የሚያደርገው ነው በሚል ትችት እየቀረበበት ነው።ይሁን እንጅ ሶስቱም አገራት ስምምነቱን በማወደስ ለተግባራዊነቱ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።