Monday, 18 April 2016

መንግሥቱ ኃይለማርያምን እንዴት ታደንቃለህ

መንግሥቱ ኃይለማርያምን እንዴት ታደንቃለህ በማለት መከራዬን አሳዩኝ እኮ መንግሥቱ ኃይለማርያም ጨካኝ አረመኔ ነው ይሉኛል አዎ ጨካኝ ነው ግን ከማን ጋር ተወዳድሮ ነው መንግሥቱ ጨካኝ የሆነው? ኢትዮጵያ መቼ ለሕዝቡ የሚያስብ መሪ አግኝታ ነው መንግሥቱ በተለየ መልኩ ጨካኝ ሊሆን የሚችለው?
አዎ መንግሥቱ ኃይለማርያም የሰሯቸው ጥፋቶች አሉ እነዚህን ግን መርሳት የለብንም
1. መሀይምነትን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ባደረገው ጥረት በወቅቱ ኢትዮጵያ ለአለም ሐገራት ተምሳሌት ሆና በዛ በዘረኛ ነጮች ጭምር እውቅና አግኝታ በUnited Nation Global initiatives on Education ተሸላሚ ሆና ነበር። ይህን የሰራው መንግሥቱ ኃይለማርያም ነው።
2. ስንቱ ፊውዳል ተቆጣጥሮት የነበረውን የሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብን መሬት ለድሀው ህዝብ በማከፋፈል ድሀ...ውን የቤት ባለቤት ማድረግ ያስቻለው መንግሥቱ ሐይለማሪያም የሚመራው ሥርአት ነው። አዲስ አበባ የሚገኙ ሰፈሮችን እንኳ ተመልከቱ ኮተቤ እንኳን የአራት ፊውዳሎች ይዞታ ነበረች። ከእነዚህ አራት ፊውዳሎች አንዷ ወይዘሮ አመለወርቅ ትባል ነበረ ወይዘሮ አመለወርቅ ደግሞ የማን ቅምጥ እንደነበረች ወይ አንብቡ አልያም ጠይቁ
3. ግልጊቤ ቁጥር አንድና ሁለት ግድቦችን የሰራው ማነው? ኢህአዴግ ያስመረቀውን የጣና በለስ ፕሮጀክት 90 ከመቶ በላይ ያሰራው ማነው?
4. በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወላጅ አልባ ህፃናትን ሰብስቦ ተገቢውን እንክብካቤ እየሰጠ ያሳደገውስ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም አይደለምን?
5. ሀገሪቱን በሰሜን ሻእቢያ፣ ህውሀት፣ ኢዲዩ በምስራቅ ሶማልያ በማእከላዊ ኢሕአፓ እየወጓት እንኳን ህዝቡን ከችግር የጠበቀው ማነው? ሌላም ሌላም መጨመር ይቻላል
ስለመንግሥቱ ጭካኔ ስታወሩ ይህንንም መጨመር አለባችሁ አለበለዛ በጭፍን መንግሥቱ ጨካኝ ነው ስትሉ ሀይቅ ዳር ነፋሻማ መሬት ላይ በጀርባቹህ አስተኝቶ የሚቀልባቹህ መሪ ያላቹህ ነው የምትመሰሉት።
በመጨረሻም ከመንግሥቱ ስህተቶች በጣም የሚያናድደኝን ልንገራችሁ "መንግሥቱ ኤርትራን መሸጥ ነበረበት ኤርትራ ብትሸጥ ኖሮ አሁን ያለው መንግሥት አራት ኪሎ አይገባም ነበር ሆኖም ይህንን እንዳያደርግ ሰውዬው በዳር ድንበር ቀልድ አያውቅም ቀ
‪#‎ኤርሚያስ_ቶኩማ‬


Thursday, 14 April 2016

ሰበር ዜና — አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌ ለትግራዩ ነጻ አዉጭ ቡድን ደህንነት ቢሮ ከፍተኛ እራስ ምታት ሆኗል

 April 14, 2016 0

በልኡል አለም
የተከበሩት የቀድሞ የግንቦት 7 ዋና ጸሐፊ ለወያኔ በግፍ ተላለፈዉ ሲሰጡ የእንግሊዝ የደህንነት አካላት ያዉቁ እነደነበር እና የየመን የጸጥታ ሐይሎች እንዲሁም የትግራይ ነጻ አዉጭ ቡድን በመተባበር እገታዉን እንዳካሄዱት ዛሬ ከብሔራዊ መረጃ ምንጭ ተገኝቷል።
የእንግሊዝ ከፍተኛ የደህንነት አባላትን ጨምሮ አጣብቂኝ ዉስጥ የከተቱት አንዳርጋቸዉ ጽጌ በአምነስቲ ኢንተርናሽናልና በሌሎች ሁለት ከፍተኛ ተደማጭነት ባላቸዉ የሰባዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች እንዲሁም በወላጅ አባታቸዉ የሚጎበኙ ሲሆን የተለያዩ የወያኔን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዲስኩር ያዘሉ መጽሐፎች፣ እና መጽሄቶች በተለይም የክቡሩን ታጋይ ሞራል በሚነካ መልኩ አንዳንድ አልባሌ ጽሁፎችን ያካተቱ መጣጥፎችም ሆን ተብለዉ እንዲሰጡት ቢደረግም በጀግናዉ አንዳርጋቸዉ ላይ እየታየ ያለዉ አልበገር ባይነት በወያኔያዊያን ላይ የበላይነቱን ይዟል።
በተልይም የደህንነት ቢሮዉ ሚስጥራዊና ልዩ ስብሰባ ያካሔደ ሲሆን የእንግሊዝ ባለስልጣናት እራሳቸዉን ከተጠያቂነት ባሸሸ መልኩ በተገላቢጦሹ ታጋይ አንዳርጋቸዉን እንድንፈታ እያስገደዱን ነዉ። “ሰባዊ መብት ጥሰቱ እስካልቆመና አንዳርጋቸዉ ጽጌ ካልተፈታ ወይም አስቸኳይ የሆነ የአቋም ለዉጥ በኢትዮጵያ በኩል እስካልተደረገ ድረስ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚሰረዝ ማሳስጠንቀቂያ አዘል ትእዛዝ ተሰጥቶናል” በሚል አጀንዳ ተንተርሶ የትግራይ ነጻ አዉጭ ቡድን ጭንቅ ዉስጥ ገብቷል።
እንዳይለቁት እሳት እንዳይዙት መአት!!!  ይሏል ይህ ነዉ!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ ! !

Monday, 11 April 2016

የኦነግ የወጣቶች ክንፍ በማደራጀት ውጊያ ሊያካሄዱ ነበር የተባሉ 33 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የወጣቶች ክንፍን በማደራጀት ከመንግስት ጋር ውጊያን ሊያካሄዱ ነበር የተባሉ 33 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው ተዘገበ። ተጠርጣሪዎቹ በተለምዶ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ መኖሪያ ቤት የእምነት ስነስርዓት የሚያካሄዱ በመምሰል ለወጣቶች ክንፍ አባላት ሲመለምሉና ሲያደራጁ መቆየታቸውን ከሳሽ አቃቤ ህግ በክሱ አቅርቧል ሲል ሪፖርተር ገልጿል። ተጠርጣሪዎቹ መንግስት የኦሮሞን መሬት እየቆራረሰ በመሆኑ የኦሮሞ ህዝብ እጅና ጓንት በመሆን መንግስትን መዋጋት አለበት የሚል ቅስቀሳን ሲያካሄዱ መቆየታቸውንም በጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረበን ክስ ዋቢ በማድረግ በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ሃብቷሙ ሚልከሳ ጫሊ ኦና ረዳት ሳጅን ጫላ ፍቃዱ አብደታ የተባሉ ግለሰቦች የወጣቶቹ ክንፍ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር በመሆን እንቅስቃሴ ማካሄዳቸውንም አቃቤ ህግ በክሱ አመልክቷል። በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተጠርጣሪዎቹ በአንድ ግቢ ውስጥ 60 የሚሆኑ አባላትን በማሰባሰብና የኦነግን ባንዲራ እንዲይዙ በማድረግ ለድርጅቱ ለጊዜው መጠኑ ያልታወቀ ገቢ ማሰባሰባቸውንም ከሳሽ አቃቢ ህግ ባቀረበው የሽብርተኛ ክስ አስፍሯል። ባለፈው ህዳር ወር በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች ላይ የቀረበውን ክስ በመመልከት ፍርድ ቤቱ ለሚያዚያ 7 ፥ 2008 አም ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል። ተጠርጣሪዎቹ ከአራት ወራት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ቢገለጽም፣ እስካሁን ድረስ ለምን ክስ እንዳልተመሰረተባቸው የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን፣ በቅርቡ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ሰዎች የኦነግ አባላት ናችሁ ተብለው ለእስር መዳረጋቸውን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ። የመንግስት ባለስልጣናት ተቃውሞ በቁጥጥር ስር ዉሏል ቢሉም ተቃውሞው አሁንም ድረስ እልባት አለማግኘቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የታሰበው የዕርዳታ ማሰባሰብ ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲቆም የኢትዮጵያ መንግስት ትዕዛዝ ሰጠ

ኢትዮጵያውያን የድርቅ ተጠቂዎችን ለመታደግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ (OCHA) ከሌሎች ለጋሾች ጋር ያስተባበረው የዕርዳታ ማሰባሰብ ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲቆም የኢትዮጵያ መንግስት ትዕዛዝ ሰጠ። የኢሳት ምንጮች ከአዲስ አበባ እንደገለጹት ለአዲስ አበባው የኦቻ (OCHA) ተጠሪ ማሰባሰቢያውን የሰጡት የጠ/ሚኒስትሩ ልዩ መልዕከተኛ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ናቸው። 10.2 ሚሊዮን በቀጥታ በድርቁ ተጠቂ በመሆናቸው ሌሎች 8 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ በሶፍትኔት የታቀፉ የዕለት ድረሽ ምግብ ጠባቂ በመሆናቸው ለ18 ሚሊዮን ህዝብ ምግብ በማስፈለጉ ዓለም-አቀፍ ድርጅቶቹ እ/ኤ/አ ማርች 23/2016 የዕርዳታ ማሰባሰብ ዘመቻ መጀመራቸውም ታውቋል። ይህ በመገናኛ ብዙሃን የተጀመረው የዕርዳታ ዘመቻ የኢትዮጵያን ገጽታ ይጎዳል በሚል መንግስት እንደቆይ መወሰኑን መረዳት ተችሏል። ከ10 ቀናት በፊት እ/ኤ/አ ማርች 23/2016 ለኢትዮጵያውያን ዕርዳታ ለማሰባሰብ በፌስ ቡክ፣ ትዊተር እና በለጋሾች ዌብሳይት ዘመቻውን የጀመሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል የሆነው የሰብዓዊ ጉዳዮችን ቢሮ (OCHA) የአሜሪካ የዕርዳታ ድርጅት ዩ ኤስ ኤይድ (USAID) ሴቭ ዘ ችልድረን (SAVe The Childeren)፣ ዩኒሴፍ (UNICEF)፣ እና ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች መሆናቸውንም መረዳት ተችሏል። በተያዘው የምዕራብያውያኑ ዓመት 2016 ረሃብተኛ ኢትዮጵያውያንን ለመታደግ የሚያስፈልገው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ባለመገኘቱ አለም-አቀፍ ተቋማቱ ዘመቻውን ከፍተዋል። የጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ልዩ መልዕክተኛ የሚል ሹመት የተሰጣቸው የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስ ዘመቻው እንዲቆም አሳስበው ዕርዳታውን እንዳይሰባሰብ ለኦቻ (OCHA) ዳይሬክተር መናገራቸውን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የኦቻ (OCHA) ዳይሬከተር በበኩላቸው ለጋሾቹ ወደ ሚዲያ ዘመቻ ለመግባት የተገደዱበትን ሁኔታ አስረድተዋል። የድርቅ ተጎጂዎች ለመታደግ የሚያስፈልገው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የተገኘው ከግማሽ በታች 686 ሚሊዮን ዶላር ነው። ይህ በአለም-አቀፍ ለጋሾች በኩል የታየውን ደካማ ምላሽ ለማሸነፍ ሲባል ዘመቻው መከፈቱን አብራርተዋል። አምባሳደሩ የመንግስታቸው አቋም የማይቀየርና ዘመቻው መሰረዙ የግድ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ዕርምጃው የኢትዮጵያን መንግስት ገጽታ በአለም-አቀፍ ደረጃ ይካሄዳል በማለት ማሳሰባቸውም ተመልክቷል። በተጨማሪም ለገንዘብ ዕጥረቱ ለየትኛውም የምዕራብ ሚዲያ እንዳይሰጡም ማሳሰባቢያ ተሰጥቷቸዋል። በኢትዮጵያ የኦቻ ተወካይ ከአምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስ ማሳሰቢያ በኋላ፣ አለም አቀፍ ደረጃ ያለው ምላሽ ደካማ መሆኑን በመግለፅ፣ ዘመቻውን ለመክፈት የተገደደበትን ሁኔታ ያስረዱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አለ ያሉትንም አሳሳቢ ችግር ጠቅሰዋል። በሶማሊ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ክልል ላለፉት 60 ቀናት ድጋፍ ያላገኙ ተረጂዎች መኖራቸውን የጠቀሱ ስሆን፣ አምባሳደር በቂ ምግብ ወደብ ላይ አለ፣ ችግሩ ትራስፖርት ነው ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ የኢትዮጵያ ተጠሪ ሰለባዎቹ ያሉበት አሳሳቢ ሁኔታ በሚመለከት፣ መንግስት ውሳኔውን እንደገና እንዲመረምር መማጸናቸውም ተመልክቷል። ሆኖም አምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስ የመንግስት ውሳኔ የማይለወጥ መሆኑን አስረግጠው ካልተስማማችሁ ቢሯችሁን ዘግታችሁ መውጣት ትችላላችሁ ሲሉ ማሳሰባቸውን ለኢሳት በዝርዘር የደረሰው መረጃ ያሳያል። 10.2 ሚልዮን የድርቅ ተጠቂዎችን እንዲሁም በሶፍት ኔት የታቀፉ 8 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ 18.2 ሚሊዮን ዜጎች ለመታደግ ማርች 23/2016 የተጀመረው ዘመቻ የመንግስትን ማሳሰብያ ተከትሎ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ተቋርጧል። ዘመቻው የተከፈተው ለ90 ቀናት እንደነበርም ታውቋል።

በጣሊያኑዋ በቶሪኖ የተጠራው የመንግስት ስብሰባ በተቃውሞ ተበተነ

እሁድ ሚያዚያ 3፣ 2008 ዓም በጣሊያኑዋ የቶሪኖ ከተማ መንግስት ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ቦንድ ለመጨጥ እንዲሁም አወዛጋቢ የሆነውን የኮንዶሚኒየም ሽያጭ ለማከናወን እና የውጭ ምንዛሬ ለመሰብሰብ የጠራው ስብሰባ በከተማዋ በሚገኙ ኢትጵያውያን ተቃውሞ እንዲሰረዝ ተደርጎአል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ገና ከመነሻው ተቃውሞአቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ መሰረታዊ የሚባሉ የመብት፣ የእኩልነትና የኢኮኖሚ አስተዳደር ጥያቄዎችን አንስተው ተቃውአቸውን አሰምተዋል፡፡ አንድ አራተኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በተራበበት ሁኔታ፣ ቅድሚያ የሰዎችን ህይወት መታደግ ሲገባችሁ እናንተ ግን የት እንደምታደርሱት ለማይታቅ ገንዘብ ለመሰብሰብ አጀንዳ ከፈታችሁ፤ ይሄ ከአገርም በላይ ሰብአዊነትን የሚመለከት በመሆኑ ቅድሚያ ለሰው ልጅ ህይወት ስጡ ያሉት ዜጎች፣ ከ300 በላይ የኦሮሞ ወገኖች ባለቁበት ሰአት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ታስረው በሚሰቃዩበት በዚህ ወቅት፣ እንዲሁም በወልቃይት ጥያቄ ዙሪያ ዜጎች ስቃያቸውን እያዩ፣ እናንተ ምንም ሳይመስላችሁ፣ ስለ ውጭ ምንዛሬ ልትነግሩን አጀንዳ ከፈታችሁ፣ ይሄ ያሳፍራል ሲሉ በምሬት ትቃውአቸውን ገልጸዋል፡፡ በውጭ ለሚገኘው ዜጋ ቤት ከመጨነቃችሁ በፊት በቅድሚያ ቤት አጥቶ ለሚሰቃየው አገር ቤት ላለው ህዝብ ቤት ስሩለት በማለት፣ በአገር ቤት ህዝብ ቤት አጥቶ እየተሰቃዬ፣ በተሻለ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኘው በውጭ ለሚገኘው ዜጋ ቤት ለመስጠት የሚደረገውን ሩጫ በአስመሳይነት በመፈረጅ አውግዘዋል ኢትዮጵያውያኑበአገሪቱ ውስጥ የአንድ ብሄር የበላይነት መኖሩን፣ እንዲሁም ከ20 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ተርቦ እናንተ ኢሳትን ለማፈን ከፍተኛ ገንዘብ ታወጣላችሁ በማለት የሞራል ጥያቄ አንስተው ተቃውመዋል፡፡ አገሩን ለቀን ወጣንላቸው ፣ እዚህ ደግሞ ገንዘባችንን ፡፡ ሊወስዱ ይመጣሉ በማለት ተቃውሞአቸውን በማሰማት መንግስት ስብሰባውን ለመሰረዝ ተገዱዋል፡፡ በፊላደልፊያም ተመሳሳይ ተቃውሞ መደረጉ ታውቆአል፡፡

የሶስት ኢትዮጵያውያን ንብረት ነው የተባለ 356 ሺ ዶላር በቻይና የጉአንግዙ መገኘቱን የቻይና መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ

በቻይና የጉአንግዙ ግዛት በሚገኝ አንድ አለም-አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የሶስት ኢትዮጵያውያን ንብረት ነው የተባለ 356 ሺ ጥሬ ዶላር መገኘቱን የቻይና መገናኛ ብዙሃን ሰኞ ዘገቡ። በአንድ ሻንጣ ተሞልቶ የነበረው ይኸው ከፍተኛ ገንዘብ በአየር መንገዱ መሳፈሪያ አካባቢ ለጉዞ በነበሩ ሁለት የኮንስትራክሽን ሰራተኞች መገኘቱንና የንብረቱ ባለቤት ናቸው ለተባሉት ሶስቱ ኢትዮጵያውያን መሰጠቱ ታውቋል። 356ሺ ጥሬ ዶላር ገንዘብን የያዘው አነስተኛ ሻንጣ በዋናው የአየር ማረፊያው መግቢያ ላይ መገኘቱንና ሁለቱ ግለሰቦች ለፖሊስ ማስረከባቸውን የቻይናው ዜና አገልግሎት ዢንሁዋ ሰኞ ዘግቧል። የሻንጣው ባለቤት አድራሻ ለማግኘት በማሰብ ሁለቱ ቻይናውያን ሻንጣውን ቢፈቱም አይተውት የማያውቁት ገንዘብን በሻንጣው በማየታቸው ድንጋጤ እንዳደረባቸውና ገንዘቡን ለፖሊስ እንዳስረከቡ ቻይናውያኑ አስረድተዋል። ገንዘቡን የቆጠሩት የቻይና የጸጥታ ሃይሎችም የገንዘቡ ባለቤት ናቸው ለተባሉ ሶስቱ ኢትዮጵያውያን ያስረከቡ ሲሆን፣ የሶስቱ ኢትዮጵያውያን ማንነት ግን ይፋ አልተደረገም። ይህን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ በበርካታ ሃገራት በጥሬ ይዞ መንቀሳቀስ የማይፈቀድ ቢሆንም፣ የቻይና የጸጥታ ሃይሎች ግን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የሰጡት ዝርዝር የለም። የባለ መቶ ኖቶቹን 356ሺህ ሶላር (ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ) የያዙት ኢትዮጵያውያን ገንዘቡን ለምን ጉዳይ እንደያዙትና ለምን አላማ ሊያዉሉት እንደነበርም የቻይና ፖሊሶች የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት ሶስት ቀን ወደ ቻይናው ጓንጉዙ አየር ማረፊያ በረራን እንደሚያደርግ ለመረዳት ተችሏል። ከወራት በፊት በአውሮፕላን እቃ መጫኛ ክፍል ውስጥ ተደብቆ ስዊድን ሃገር ከገባ በኋላ በሃገሪቱ የፖለቲካ ጥገኝነትን የጠየቀ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ በመንግስት ባለስልጣናት ዶላር በሻንጣ እየተደረገ እንደሚወጣ ለኢሳት መግለጹ ይታወሳል። ከኢትዮጵያ ጋር የቅርብ ወዳጅነት አላት በምትባለው ቻይና በርካታ በለስልጣናት ለተለያዩ ጉዳዮች በየጊዜው እንደሚጓዙባትም ይነገራል።

Friday, 8 April 2016

በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ስርዓት አተገባበር ጥያቄ እንዳስነሳ የብሪታኒያው ዘ-ጋሪድያን ዘገበ

 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ልዩነቶችንና አመለካከቶችን በተገቢው ሁኔታ ሊስተናገዱ ባለመቻላቸው በሃገሪቱ ተቃውሞ ኣየተባበሱ መምጣቱን የብሪታኒያው ዘ-ጋሪድያን ጋዜጣ የተለያዩ መረጃዎች ዋቢ በማድረግ አርብ ዘገበ። በተለያዩ ክልሎች መጠኑን እያሰፋ የመጣው ይኸው ተቃዎሞ በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ስርዓት አተገባበርና በዴሞክራሲያዊ የመብት ጥያቄዎች ላይ ጥያቄ አስነስቶ እንደሚገኝም ጋዜጣው አስነብቧል። በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ በትንሹ 266 ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን ያወሳው ጋዜጣው አስተዳደራዊ ጥያቄን ባነሱ የኮንሶ ማህበረሰብ ዘንድም የሃይል እርምጃ መወሰዱን አመልክቷል። የሃገሪቱን የብሄር ብሄረሰቦች መብት በመጠቀም በደቡብ ክልል የተነሳውን ይህንኑ ጥያቄ ተከትሎ የኮንሶ ማህበረሰብ መሪ የሆኑን ካላ ገዛኸኝ በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበረም ዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ በዘገባው አውስቷል። በአማራ ክልል ከቅማት ማህበረሰብ የአስተዳደር ጥያቄ ጋር በተያያዘ ለአመታት የቆየ ተቃውሞ ሲሰማ መቆየቱን የዘገበው ጋዜጣው በሃገሪቱ የፖለቲካ አመለካከቶችና ልዩነቶች በአግባቡ ሊስተናገዱ ባለመቻላቸው በመንግስት ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎች እየተባባሱ መምጣታቸውን አስነብቧል። በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውንና ብሄርን ማዕከል ያደረገው የፌዴራሊዝም ስርዓትም የተጠበቀውን ያህል መረጋጋትና ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ እንደማይችልም በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰሩ አካላት ገልጸዋል። የፌዴራል መንግስት በክልሎች ሊያካሄድ ባሰበው የኢኮኖሚና ተዛማች ጉዳዮች ዙሪያ ከህብረተሰቡ ጋር ምክክሮችን ማካሄድ ቢጠበቀበትም እየሆነ ያለው ግን የዚህ ተቃራኒ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌዴራሊም ባለሙያ የሆኑት አቶ አሰፋ ፍሰሃ ለዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ አስረድተዋል። የፌዴራል መንግስት ክልሎችን ሳያማክር ሰፋፊ የስኳር ፋብሪካዎችንና ሌሎች ፕሮጄክቶችንም በራሱ ስልጣን እያከናወነ እንደሚገኝ ጋዜጣው የተለያዩ መረጃዎች በምሳሌነት በማቅረብ ዘግቧል። ገዢው የኢህአዴግ መንግስት በቅርቡ በተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ መቶ በመቶ ማሸነፉን ያወሳው ጋዜጣው ውጤቱን ተከትሎ መቀስቀስ የጀመረው ተቃውሞ በፓርቲው የበላይነት ላይ ችግሮች እየገጠሙት እንደሆነ ማሳያ ነው ሲል ዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል። በሃገሪቱ ያለው የፌዴራል ስርዓትም ከተለያዩ አካላት ዘንድ ጥያቄ እየቀረበበት እንደሚገኝም ጋዜጣው አክሎ ዘግቧል።

ጋዜጠኛ አበበ ገላው የኢሳት አለም-አቀፍ ዳይሬክተር ሆኖ ተሾመ

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ቦርድ ለኢሳት አለም-አቀፍ አዲስ ዳይሬክተር መሾሙን ይፋ አደረገ። የቀድሞውን የኢሳት አለም አቀፍ ዳይሬክተር አቶ ነዓምን ዘለቀ በክብርና በምስጋና የሸኘው የኢሳት ቦርድ ጋዜጠኛ አበበ ገላው የኢሳት አለም አቀፍ ዳይሬክተር እንደሆነ ከኤፕሪል 1 ፥ 2016 ጀምሮ መሾሙን አስታውቋል። 
በአሁኑ ወቅት በካሊፎርኒያ ግዛት ሲልከን ቫሊ የሚገኘው ጋዜጠኛ አበበ ገላው ከኢሳት አስተዳደር ቦርድ በተሰጠው ሹመት መሰረት በቀጣዩ ሳምንት ወደ ዋሽንግተን በመምጣት ሙሉ ጊዜውን በኢሳት ውስጥ እንደሚሰራም ለመረዳት ተችሏል። እኤአ ከ2011 ጀምሮ እስከ 2013 በኢሳት ውስጥ ሲያገለግል የነበረው ጋዜጠና አበበ ገላው፣ ላለፉት 3 ሳምንታት ካሊፎርኒያ ግዛት ሲልከንቫሊ በሚገኝ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ውስጥ ሲሰራ ቆይቷል። የኢሳት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ነዓምን ዘለቀ ሙሉ ጊዚያቸውን በኢሳት ውስጥ ለማሳለፍ በስራ መደራረብ ሳቢያ ባለመቻላቸው አዲስ ዳይሬክተር ሲያፈላልግ የቆየው የኢሳት ቦርድ ጋዜጠኛ አበበ ገላው ከተገመገሙ ዕጩዎች ውስጥ ለቦታው ብቁ ሆኖ በመገኘቱ በዳይሬክተርነት መሾሙን አስታውቀዋል። ቦርዱ ኢሳትን በዳይሬክተርነት ለረጅም ዓመታት ለመሩት ለአቶ ነዓምን ዘለቀ እንዲሁም ካለበት ተደራራቢ ሃላፊነቶች በተጨማሪ የኢሳትን ዳይሬክተርነት በተጠባባቂነት ለወራት ሲመራ ለቆየው ለአክቲቪስት ታማኝ በየነ ምስጋናውን አቅርቧል።

Thursday, 7 April 2016

በ2016 በድርቅ እና በጎርፍ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ተመድ ገለጸ

በተያዘው የፈረንጆች አመት (2016) ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በኢትዮጵያ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጠ። ድርቁ እያደረሰ ካለው ጉዳት በተጨማሪ የጎርፍ አደጋም ለሰዎቹ መፈናቀል ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ድርጅቱ በወቅታዊው የኢትዮጵያ የድርቅ ሁኔታ ዙሪያ በወጣው ሪፖርት አመልክቷል። አሁን በሃገሪቱ ተከስቶ ካለው የድርቅ አደጋ አንጻርም በቂ የህክምና አገልግሎቶች ተሟልተው አለመገኘታቸውን የገለጸው ድርጅቱ በድርቁና በጎርፍ አደጋ የሚከሰተው ጥፋትም የበርካታ ሰዎችን ህይወት ሊቀጥፍ እንደሚችልም አሳስቧል። በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎችም የወባ በሽታን ጨምሮ ህጻናትን በአጣዳፊ የሚገድሉ ተላላፊ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ ሊከሰቱ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አክሎ ገልጿል። በድርቁ ሳቢያ በተፈጠረው የምግብ ኣጥረት ክፉኛ የአካልና የጤና ጉዳት ደርሶባቸው የሚገኙ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ህጻናትም እየተባባሰ በሚሄደው የድርቅ አደጋ ያልተጠበቀ አደጋ ሊገጥማቸው እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። ወደ ሁለት ሚሊዮን አካባቢ የሚደርሱና በምግብ እጥረት ላይ የሚገኙ እርጉዝ እናቶችም በምግብ እጥረቱ ምክንያት እርግናቸው ሊጨናገፍ እንደሚችል ድርጅቱ አሳስቧል። ለተረጂዎች የሚደርስ የእህል እርዳታ በጅቡቲ ወደብ ቢደርስም በወደቡ የተፈጠረ መጨናነቅ የእርዳታ እህሉ ለተረጂዎች በወቅቱ እንዳይደርስ ታውቋል። የጫኑትን የእህል አቅርቦት ማውረድ ያልቻሉ ከ10 በላይ መርከቦችም ወደሱዳንና ሶማሊላንድ በርበራ ወደብ እያቀኑ መሆናቸውን የመንግስት ባለስልጣናት መግለጻቸው ይታወሳል። ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ከተጋለጡት ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መካከልም 3.6 ሚሊዮን የሚሆኑት የህክምና ድጋፍን የሚፈልጉ እንደሆነ ታውቋል። በስድስት ክልሎች ተከትስቶ ያለው የድርቅ አደጋ መባባስን ተከትሎ ወደ ረሃብ ደረጃ ሊደርሱ ይችላሉ የሚባሉ ወረዳዎች ቁጥርም ኣየጨመረ መምጣቱን የእርዳታ ተቋማት በመግለጽ ላይ ናቸው። ሰሞኑን በጅጅጋ ከተማ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ50 የሚበጡ ደግሞ የገቡበት አለመታወቁ መገለጹም ይታወሳል።

በአማራው ክልል ፕሬዚዳንት ላይ ያነጣጠረ ግምገማ እየተካሄደ ነው

በቅርቡ በአማራ ክልል ተነስተው የነበሩትንና እስካሁንም መቁዋጫ ያልተገኘላቸውን የቅማንትና የወልቃይት ጠገዴን ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄን ተከትሎ ለደረሰው ደም መፋሰስ የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳጋቸውን ተጠያቂ በማድግ የህዝቡን ጥያቄ ለማፈን በመሩዋሩዋጥ ላይ መሆኑን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ገልጸዋል፡፡ የወልቃይት ጥያቄ የአቶ ገዱ የአመራር ችግር እንጅ የአማራ ህዝብ ጥያቄ አይደለም በሚል፣ ፕሬዚዳንቱን ከብአዴን አባላት እና ከህዝቡ ጋር በማጋጨት፣ ጥያቄው ተዳፍኖ እንዲቀር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን እነዚህ ወገኖች ይገልጻሉ፡፡ ከመጋቢት 23 ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በሁሉም ዞኖች ሲካሄድ በሰነበተው የብአዴን የህዋስ ግምገማ ፣ ሁለት አላማዎችን ለማሳካት መታቀዱን የሚገልጹት ታዛቢዎች፣ አንደኛው፣ የአማራ መብት አልተጠበቀም፣ አማራ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገባውን ቦታ አላገኘም፣ የወልቃይት ጠገዴ፣ የሱዳን መሬትና ሌሎችም ተያያዝ ጥያቄ ያነሱ የድርጅቱን አባላት፣ በጠባነትና በተቃዋሚ አጀንዳ አራማጅነት በመክሰስ ነጥሎ ለመምታ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የወልቃይት ጠገዴን ጥያቄ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የግል አጀንዳ በተለይም ከትግራይ ክልል መሪ ከአቶ አባይ ወልዱ ጋር ባላቸው ቅራኔ የተነሳ የተፈጠረ ነው በሚል፣ጥያቄዉን ግልሰባዊ ይዘት በመስጠት፣ ህዝባዊነቱን መንጠቅ የሚል ነው፡፡ በዚህም መሰረት፣ በግምገማው ወቅት፣ የህዝብ ጥያቄዎች ናቸው በሚል የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያነሱ በነበሩ የብአዴን አባላት ላይ በየመድረኩ የማሸማቀቅና የማስፈራራት ስራ በመስራት አንገታቸውን እንዲደፉ ተደርጎአል፡፡ በእነዚህ አባላት ላይ በሂደት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችልም ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡ በሌላ በኩል ሆን ተብሎ በህወሃት የደህንነት አባላት እና ለህወሃት ታማኝነተን አላቸው በሚባሉ የብአዴን አባላት በተቀነባረው ስብሰባ አቶ ገዱን በስም እየጠቀሱ፣ የወልቃይት ችግር የግለሰብ ችግር መሆኑን ለማሳየት ጥረት ተደርጎአል፡፡ በግምገማዎች ላይ ሁሉ የሁለቱ ክልሎች መሬዎች ስም ሲነሳ የቆየ ሲሆን፣ የአቶ አባይ ስም እንዲጠራ የተፈለገው፣ አባላቱን ለማሳመንና ጉዳዩ ሴራ ያለበት እንዳይመስል ነው ይላሉ፡፡ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ የህዝብ ጥያቄ ሳይሆን የግለሰብ መሪዎች ጥያቄ ነው በማለት፣ ብአዴን ጥያቄው እንደማይመለከተውና ችግሩን የፈጠሩት መሪዎች መሆናቸውን በማሳየት፣ ጥያቄው ተዳፍኖ እንዲቀር ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡ የግምገማ ውጤቱ በሂደት የሚታይ ቢሆንም፣ የወልቃይት ጥያቄ እየገፋ የሚሄድ ከሆነ፣ አቶ ገዱን በማንሳት ጥያቄውን ለማዳፈን ሙከራ ለደረግ ይችላል፡፡ በዚህ ግምገማ ላይ የወልቃይት ህወሃት የወልቃይትን ጥያቄ የግለሰብ ጥያቄ አድርጎ በማቅረብ ለማዳፈን እየሄደበት ያለው ርቀት ችግሩን እንደማይፈታው ይናገራሉ፡፡ አብዛኛው የብአዴን መካከለኛና ተራ አባላት ብአዴን 25 አመታት ሙሉ የህወሃት ታዛዥ መሆኑን የሚቃወሙ ሲሆን፣ ሰሞኑን በተካደው ግምገማም ይህ ተቃውሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ ብሎ ተሰምቶአል፡፡ ከህወሃት ጋር ቅርብ ግንኙነት አላቸው የሚባሉት የብአዴን ከፍተኛ መሪዎች፣ ታች ያለው አባሉ እያነሳ ያለውን ጥያቄ የማደግፉና በጥርጣሬ የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ከፍተኛ አመራሩ እርስ በርስ ለስልጣን በሚያደርጉት ፉክክር፣ አንዱ ሌላውን አሳልፎ እየሰጠ መሆኑን ታዛቢዎች አክለዋል፡፡ በሌላ በኩል የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ከህወሃት ጋር በእየለቱ ግጭት ውስጥ እየገባ መሆኑን ከአካባቢው የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የህወሃት ካድሬዎች የወልቃይትን የአማራ ማንነት ይደግፋሉ የሚሉዋቸውን እየተከታተሉ በማስፈራራት ላይ ሲሆኑ፣ በህዝቡ መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት አካባቢውን አስፈሪ አድርጎታል፡፡ ህወሃት ጥያቄውን ለመመለስ እየተከተለው ያለው መንገድ አካባቢውን ወደ እርስ በርስ ግጭት እንዳይከተው የአካባቢው ነዋሪዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በሌላ ዜና ደግሞ መጋቢት27ቀን 2008 ዓም የሚከበረውን የመድሐኒዓለም ክብረበአል ለማክበር ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ዋልድባ አብረንታንት ገዳም የሄዱ ምዕመናንን ታጣቂዎች አርማደጋ ላይ በማስቆም ከ200 በላይ የሚሆኑትን ንብረታቸውን ሙሉ በሙሉ እንደዘረፉዋቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የገዳሙ አባቶች ለኢሳት ተናግረዋል፡፡ ዘራፊዎቹ 4 ሲሆኑ፣ ሁለቱ ይፈትሻሉ ሁለቱ ደግሞ ህዝቡን ያስቆማሉ ያሉት አባቶች፣ ክላሽ፣ ጩቤና ገጀራ መያዛቸውንም አክለዋል፡፡

በአምቦ ወህኒ ቤት አንድ ወጣት በደረሰበት አሰቃቂ በድብደባ ተገደለ

አምቦ ወህኒ ቤት ውስጥ የታሰረ አንድ ወጣት በድብደባ መገደሉን ወላጅ እናቱ ለኢሳት ገለጹ። ላለፉት 10 አመታት በወህኒ ቤት ውስጥ የቆየው ወጣት ጌጡ በቀለ ቶሎሳ፣ ህይወቱ ያለፈው ከአምቦ ወህኒ ቤት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ እጅ አለበት በሚል በደረሰበት ድብደባ መሆኑም ተመልክቷል። በፖለቲካ ሳቢያ ከ10 አመት በፊት ወህኒ ቤት መግባቱ የተገለጸው ወጣት ጌቱ በቀለ፣ እዚያው እያለ በመጣበት ተጨማሪ ክስ ወህኒ ቤት ውስጥ እንዲቆይ መደረጉን ከወላጅ እናቱ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል። የመጣበትም ተጨማሪ ክስ በአካባቢው ከተገደለ የኦህዴድ ካድሬ ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ ገዳዩ አንተነህ በሚል ተወንጅሎ መቆየቱንም መረዳት ተችሏል። ወላጅ እናቱ በቅርቡ ወህኒ ቤት ሄደው ሲጎበኙ ጤነኛ የነበረው ጌቱ በቀለ ቶሎሳ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ህይወቱ ማለፉን አስረድተዋል። ሆስፒታል መግባቱን ገልጾ በላከላቸው መልዕክት ሊጎበኙት ሲሄዱ አስከሬኑ መላኩ እንደተነገራቸው አስረድተዋል። አስከሬኑን ለማግኘት የደረሰባቸውን መጉላላትም ያስታወሱት የሟች ወጣት ጌቱ በቀለ ቶሎሳ እናት፣ አስከሬኑ ሲደርሳቸው ከፍተኛ ድብደባ ያደረሱበት መሆኑን ገልጸዋል። ሟች ወጣት በአካሉ ላይ በደረሰበት ድብደባ ከፊል ሰውነቱ በፋሻ መጠቅለሉንም ለኢሳት አስረድተዋል።

የቤት ለቤት ፍተሻ የመርካቶ ነጋዴዎችን አበሳጭቶአል

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በፖሊስ ሀይል እየታገዘ መደብሮቻችንን መፈተሽ መጀመሩ ህገወጥ እርምጃ ነው በሚል የመርካቶ ነጋዴዎችተቃውመዋል። አንዳንድ ነጋዴዎች ለአዲስ አበባው ሪፖርተራችን እንደነገሩት ፖሊሶች በድንገት ሱቆቻችንን በመውረር ፍተሻ እናደርጋለን በሚል ለእያንዳንዱ እቃ በህጋዊ መንገድ የገባበትን ማስረጃ ካላቀረባችሁ ብለው እንደሚያዋክቡ፣ አንዳንዶች ማስረጃዎችን እስከሚያሰባስቡ እድል እንኩዋን ሳይሰጡዋቸው እቃዎቻቸውን ኮንትሮባንድ ናቸው በሚል ጭነው እየወሰዱ መሆኑ አሳዛኝ ነው ሲሉ በምሬት ገልጸዋል። ነጋዴዎቹ አያይዘውም በተለይ ሞባይሎች፣ ፍሪጆች፣ ቴሌቪዥኖችና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መንግስት በላካቸው ሀይሎች እየተዘረፉ መሆኑን ተናግረዋል። ባለስልጣኑ በበኩሉ ኮንትሮባድን ለመቆጣጠር በመርካቶ አካባቢ በተመረጡ 7 ሱቆች ላይ ሰሞኑን ድንገተኛ ፍተሻ በማካሄድ ግምታቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሆነ የኤሌክትሮኒክስ የኮንትሮባንድ እቃዎች ይዣለሁ ብሎአል። ባለፉት ወራት በተመሳሳይ ሁኔታ በ29 ሱቆች ላይ እርምጃ መውሰዱንና በድርጊቱ የተጠረጠሩ ነጋዴዎችን እንደሚከስ አስታውቆአል። በዚህ ምክንያት በመርካቶ በተለይ አንዋር መስጊድ አካባቢ በርካታ ሱቆች አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን ለመገንዘብ ተችሎአል።

በአበረታች መድሃኒት ምክንያት የኢትዮጵያ አትሌቶችና አትሌቲክስ ማኅበር ቅጣት ይጠብቃቸዋል

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ ተደርጎ የማያውቅ ድርጊቶች በቅርቡ ከዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ማኅበርና ከመገናኛ ብዙሃን በኩል መደመጥ ተጀምርዋል። ውጤታማው የኢትዮጵያ የመሃከለኛና የረዥም ሩጫ ተወዳዳሪዎች አበረታች መድሃኒት መጠቀማቸውን የፀረ አደንዛዥ እጽ ተቆጣጣሪ ድርጅት በምህጻረ ቃሉ ዋዳ /WADA/ አስታውቋል። ዓለምአቀፉ አትሌቲክ ማኅበር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ማኅበር የሯጮችን የደም ምርመራ ናሙና ውጤት ካላቀረበ በኢትዮጵያ ላይ ቅጣት እንደሚጥል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ማኅበር የሕክምና ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አያሌው ጥላሁን እንዳሉት ''ከ150 አስከ 200 በሚሆኑ ሯጮች ላይ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ምርመራ እንደሚጀምር ገልጸዋል። ዶክተር አያሌው አክለውም ''እኛ ምርመራውን ካላደረግን በቅርቡ ከማንኛውም ውድድሮች የሚያግድ ቅጣት እንደሚጣልብን ዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ማኅበር አሳውቆናል'' በማለት የሁኔታውን አሳሳቢነት ተናግረዋል። የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማኅበር ፕሬዝዳንት ሰር ሰባስቲያን ኮባሳለፍነው ወር ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከዋነኞቹ ተጠርጣሪዎቹ አምስቱ አገራት ሩሲያ፣ ኬንያ ፣ ሞሮኮ፣ ቤላሩስና ዩክሬን ተርታ መመደቧን አሳውቀዋል። ኢትዮጵያና ኬንያ እያንዳንዳቸው ሶስት ሯጮች ላይ እገዳ መጣላቸውን አስታውቀዋል። ዘጠኝ የኢትዮጵያ ሯጮች አበረታች መድሃኒት ሳይጠቀሙ እንዳልቀሩ ጥርጣሬ መኖሩንና ማጣራቱንም እንደሚቀጥል ማኅበሩ አስታውቋል። የአበረታች መድሃኒት ቁጥጥሯ ደካማ የተባለችው ሩሲያ ከማንኛውም ውድድሮች የታገደች ሲሆን ኬኒያና ኢትዮጵያም አስቀድመው ካላሳወቁ እገዳውን ሊጥል እንደሚችል ዓለምአቀፉ አትሌቲክ ማኅበር ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አሾሸትድ ፕሬስ ዘግቧል።

Wednesday, 6 April 2016

ኢትዮ-ቴሌኮም ያልተቀረጡ ስልኮችን በአገልግሎት ላይ እንዳይውሉ የሚያደርግ ቁጥጥርን ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

በኢትዮጵያ የስልክ አገልግሎትን በብቸኝነት እየሰጠ የሚገኘው ኢትዮ-ቴለኮም በተለያዩ መንገዶች ወደ ሃገሪቱ የገቡና ያልተቀረጡ ስልኮችን በአገልግሎት ላይ እንዳይውሉ የሚያደርግ ቁጥጥርን ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ። ኢኪዩፕመንት አይደንቲቲ ሬጂስተር የተሰኘ ቴክኖሎጂን አገልግሎት ላይ ለማዋል በዝግጅት ላይ የሚገኘው ድርጅቱ በሃገሪቱ ያሉ ሁሉ የእጅ ስልኮች ምዝገባ እንደሚያደርጉም ገልጿል። በምዝገባው ያልተካተቱና በስጦታና በተለያዩ መንገዶች ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ስልጎችም ተገቢው ምርመራ ካልተካሄደባቸው በስተቀር በአገልግሎት ላይ እንዳይዉሉ የሚደረግ መሆኑን የኢትዮ-ቴሌኮም ሃላፊዎች ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል። በተለያዩ መንገዶች ወደሃገሪቱ የገቡና በአገልግሎት ላይ የሚገኙ ስልኮችም በምን መልኩ ህጋዊ መደረግ እንዳለባቸው ከቀናት በኋላ ጉዳዩ የሚመከለታቸው አካላት ምክክርን ያካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የብሪታኒያ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን በልዩ ሁኔታ ለመከታተል ወሰነ

የብሪታኒያ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ በእስር ላይ የሚገኙትን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን በልዩ ሁኔታ ለመከታተል ወሰነ። የሃገሪቱ መንግስት የዜጋውን መብት ለማስጠበቅ የተቻለውን ሁሉ አላደረገም ሲሉ የቀረቡ አቤቱታዎችንና ተቃውሞዎችን ዋቢ በማድረግ ኮሚቴው የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለመከታተል እንደወሰነ የብሪታኒያ መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዘግበዋል። የብሪታኒያ መንግስት ለሰብዓዊ መብት መከበር በቂ ትኩረት አለመስጠቱን የተቸው የፓርላማው የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሃገሪቱ በሰብዓዊ መብት አያያዝ የጎደፉ ስም ያላቸውን ሃገራት ለማውገዝ እንኳን አለመድፈሩ ስጋትን እንዳሳደረም አመልክቷል። የአውሮፓ ፓርላማና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ከእስር እንዲለቀቁ ጥያቄን ቢያቀርቡም፣ የብሪታኒያ መንግስት ተመሳሳይ ጥያቄን አለማቅረቡም በኮሚቴው ትችት ቀርቦበታል። በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በሃገሪቱ መንግስት ላይ ተቃውሞን ያቀረበው ኮሚቴው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን ጨምሮ ሌሎች አበይት ጉዳዮችን በልዩ ሁኔታ ለመከታተል እንደወሰነ ይፋ አድርጓል። በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ካሜሩን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲያነሱም የተለያዩ አካላት ግፊት እያደረጉ እንደሆነም ታውቋል። ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ በተጨማሪ የብሪታኒያ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ በግብፅ በእስር ላይ የሚገኝን የአንድ የአየርላንድ ታዳጊ ወጣት ጉዳይንም በልዩ ሁኔታ እንደሚከታተለው ገልጿል። ታዳጊ ወጣቱ ከሶስት አመት በፊት በካይሮ ከተማ በተካሄደ አንድ የተቃዋሚ ሰልፍ ላይ ተሳታፊ ሆኗል ተብሎ በቁጥጥር ስር ውሎ የሚገኝ ሲሆን የሞት ቅጣት ይተላለፍበታል ተብሎ ተሰግቷል። የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የሆነውና የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን የሚከታተለው ሪፕሪቭ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ማያ ፎያ ፓርላማው የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በልዩ ሁኔታ ለመከታተል መወሰኑ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን አስታውቀዋል። የብሪታኒያ አጋር የሚባሉት ኢትዮጵያ ግብፅ ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየፈጸሙ እንደሆነም ሃላፊዋ አክለው ገልጸዋል።