Tuesday, 8 December 2015

ማር በሜንጫ ( ሄኖክ የሺጥላ )

ማር በሜንጫ ( ሄኖክ የሺጥላ )
እኛ ኢትዮጵያውያኖች ነን ፣ ስለዚህ እነ ሜንጫ ( <Ethiopia out of Oromoa> ) ሲሉን ፣ እንዴት ተደርጎ ? እንዴት ልጅ እናቷን ትወልዳለች ብለን ነበር ። እኛ የወያኔ በደልን የምንጠየፈው ወያኔ በዘር ተደራጅቶ አንድን ወይም ሁለትን ዘር ኢላማ አድርጎ የዘር ማጥፋት በየዕለቱ በመፈጸሙ ነው ፣ ይህንንም ስንል ወያኔን ( የኛን ቁስል የጠገበውን ዝንብ አራግፈን ሌላ ወያኔ መሳይ ፣ ቁስል የናፈቀው ዝምብ ይምጣ ማለታችን አይደልም ።) ይህንን ስንል በአሩሲ ፣ በባሌ ፣ በጉጂ ፣ በበደኖ ፣ በአርባባ ጉጉ እና ወዘተ የፈሰሰው የንጹሃን ኢትዮጵያውያን ደም ፍትሃዊ እና ሚዛናዊ የሕግ ፍርድ ስላገኘ አይደለም ዛሬ የኦሮሞ ልጆች ደም መፍሰስ የሚቆጨን ፣ ይህንን ስንል እስከሚገባኝ ያኛውም ይሁን ይሄኛው የዘር ማጥፋት ሴራ በበላይነት የተመራው በወያኔ መሆኑን ስለምንረዳ ፣ አትኩሮታችን ወያኔን ማስወገድ ላይ ይሁን ማለታችን ነው እንጂ ፣ የጠላታችን ጠላት ወዳጃችን ነው ማለታችን አይደለም ። የጠላታችን ጠላት ወድጃችን የሚሆነው የጋራ የሚያደርግ ነገር ሲኖረን ብቻ ነው ። የጋራ የሚያድረግ ስል ፣ የጠላታችን ጠላት ፣ አንቦ ላይ የተገደሉት የኦሮሞ ልጆች ጎንደር ላይ ከፈሰሰው የአማራ ልጆች ደም በምንም አይነት አይበልጥምም አያንስምም ብሎ ማመን ከቻለ ብቻ ፣ የሱ የእንተባበር ጥሪ ሰሚ ያገኛል ። ይህም ማለት አንቦ ላይ ለሚፈሰው ደም እሱ ሕጋዊ ወኪል ወይም ተጠሪ ነው ማለት አይደለም ፣ ወይም ደም ጎንደር ላይ ለፈሰሰው ደም አማራው ብቻ የሚባዝንበት እና በበላይነት የሚመራው የብቻ ኃላፊነት ነው ማለት አይደለም ። ግን ደሞ ፣ ያንተ ቁስል የነፍጠኛ ቁስል ነው ፣ የኔ ግን ዘላለም ሲብደል የኖረ ሕዝብ ቁስል ነው የሚለኝ ከሆነ < ብቻውን ቁስሉን ሲያክ ሊኖር ነው ማለት ነው !> ፣ < በዚህም ጎን እንደዚያው !>
ለዚህም ነው ሰሞኑን ጃዋር መሐመድ በ (ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ( OMN )) ቀርቦ ያደረገውን የእንተባበር ጥሪ ፣ ከጉንጫ አልፋ ፖለቲካና ፣ የመለዜናው ቃናን ከያዘ ብልጣ-ብልጥ የአፍ ፖለቲካ ባሻገር ፣ < ወይም ማር የተለወሰ መርዝ > እንደሆነም አድርጌ ያየሁት ።
በመሰርቱ ውይይቱ ራሱ ብዙ ግድፈት የበዛበት ነው ። ለምሳሌ ጃዋር < ኢትዮጵያ ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት እናዳለ ይናገራል ፣ በኦሮሚያ አካባቢ ያሉ ገበሬዎች የተራቡት መሬታቸው በመንግስት ስለተነጠቀ ነው ይላል ፣ በአማራ ክልል አንድ ሄክታር መሬት አልተወረሰም ፣ ወይም ለባለሃብት በኢንቨስትመን ስም/ምክንያት አልተሰጠም ይላል ? ይህንን ያለው ስለ ወልቃይት ጠገዴ ስለማያውቅ አይደለም ፣ ጎንደር ላይ ዛሬ ድንበር ተካሎ ለሱዳን ተቆርሶ ሊሰጥ እንደሆነ ስለማያውቅ አይደለም ፣ በሁመራ ሰሊጥ ፣ ጥጥ ፣ እጣን እና ኑግ እየዘራ የምያጭደው ወያኔ እንደሆነ ስለማይረዳ አይደለም ፣ ባጭሩ ለጃዋር አማራው ላይ የሚደርሰው በደል በደል ሆኖ ስለማይታየው ነው ፣ ስለዚህ
አባት ዓለም ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ያለውን ለጃዋር ላስታውሰው
የት ሊደረስ
ዛሬ ሀቅ ቢቀለበስ
በጀርባችን ይከተላል ነገ የዳኝነት ፈረስ
መቻቻልን ማወቅ ነው እንጂ
ጠንቅቀን እንደ አባ መቻል
መሸቀል አይሰራም በቃል !
ዛሬ ጮሌ ሆኗል ሁሉም
ብልህነት እንጂ ብልጠት
አክትሞለታል ዘመኑም !
ስለዚህ ይገባናል ፣ ይህ የእንተባበር ጥር ከልብ የመነጨ እንዳልሆነ ። እንደ ጃዋር አባባል < እኛ በኦሮሞ ምድር ሌላ ሰው አይኑር አላልንም ! እንደውም ሰው እንፈልጋለን !> ይላል ። ይህ ልክ ከሆነ ( <Ethiopia out of Oromoa> ) ያለውን ጃዋር እንመን ወይስ ይሄ ሰው እንፈልጋለን ያለውን ። ወይስ ሰው የሚፈልገው ከደማስኮ ይሆን ? በመጀመሪያ ጃዋር የኢትዮጵያን ሕዝብ ለትብብር ለመጠየቅ የሚያስችል የሞራል ብቃት አለው ብዬ አላምንም።
እንድንተባበረው ከፈለገ ፣ እንደ ሕዝብ ይቅርታ ሊጠይቀን ይገባዋል ፣ ዝቶብናል ፣ ፈርጆናል ፣ እንደውም በሜንጫ ( እንደሱ አባባል መንጫ ማለት እንደ ቦክስ ነው ፣ በቦክስ ሊለን ዝቷል !) ። ያለበለዚያ ጃዋር ሆይ ያንተ ይቺ እንተባበር ጥሪ ማር በ -ሜንጫ ላሱ ነገር ትመስላለች ፣ ሙድ የላትም!!!
የግርጌ ማስታወሻ
ጃዋርን ያላማከረ እና ያላማከለ ለኢትዮጵያውያኖች ( ኦሮሞዎች ፣ አማራዎች ፣ ጉራጌዎች እና ወዘተ ) የሚደረግ የተቃውሞ ና የትግል ጥሪ ያስፈልጋል እያልኩ አይደለም ። እያልኩ ያለሁት የትግሉ ብሌን መሆን የሚፈልገው ጃዋር እና መሰሎቹ ከራሳቸው ባህሪ ስንነሳ ሕዝብ ሊከተላቸው ወይም ሊሰማቸው የሚችሉ ሰዎች አይደሉም ( ሕዝብ ስል የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለቴ ነው )። ይልቁንም ሌላ ህውሃት ፣ ሌላ ገዳይ ቡድን ፣ የተፈጠረውን እሳት ተጠቅሞ ፣ ከቻለ ይህ " አማርኛ ሲሰማ የተወደደ የሚመስለው የዋህ አማራ ካለ ፣ እሱን አበድኖ ፣ ወንድምህ ነኝ ብሎ ፣ ትግል መንግሎ ለመቆም የሚያደርጉት ብልጣ ብልጥነት ነው !" የጃዋር የለበጣ አማርኛ ሆድ የሚያስብሰው ካለ የራሱ ጉዳይ ነው ፣ እኔ ግን ስለ ጃዋር ሳስብ ጭንቅላቴ ውስጥ የሚመጣው ሜንጫው ነው !

No comments:

Post a Comment