Wednesday, 2 December 2015

ለነፃነት፣ለማኅበራዊ ፍትህ ፣ ለዲሞክራሲ..

በጋዜጠኛ በፍቃዱ ሞረዳ
ለነፃነት፣ለማኅበራዊ ፍትህ ፣ ለዲሞክራሲ.. ስፍነት ኢትዮጵያ ዉስጥ እየተካሄደ ያለዉ የፀረ ጭቆና ትግል እስከዛሬዋ ቀን ድረስ እንደቀጠለ ነዉ፡፡ ለወደፊትም የሕዝብ ጥያቄ ተገቢዉን ምላሽ እስከሚያገኝ አይቆምም፡፡ በሠላማዊም፣ በትጥቅ አማራጭም፡፡
በማንኛዉም መልክ ለሚካሄደዉ ትግል ስኬታማነት ግን ድርጅት/አደረጃጀት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡አንድ ሕዝብ ምንም ያህል በጭቆና ማጥ ዉስጥ ቢዘፈቅ፣ምንም ያህል ጨቋኞችን ቢጠላ፣ምንም ያህል ቢጮህና ቢንጫጫ እስካልተደራጀ ድረስ የቱንም ወንዝ አይሻገርም፡፡ ጩኸቱ ሁሉ የቁራ ጩኸት፣ሥራዉ ሁሉ የእምቧይ ካብ ይሆናል፡፡ በሥርዓት ያልተራጀ ዜጋ፣በሥርዓት ያልተቀናጀ ትግል በየትኛዉም የሰዉ ልጅ የትግል ታሪክ አሸንፎ አያዉቅም፡፡
የሀገራችንንም የቅርብ ጊዜ የተቃዉሞ ልምዶችን በአብዛኛዉ ብንመለከት ...አወቃቀራቸዉ ከላይ ወደታች እንጂ ከታች ወደላይ ስለአልነበረ ኃይለኛ ነፋስ በሚመጣበት ጊዜ መቋቋም እያቃተዉ ለመንገዳገድ ብሎም ለመናድ ሲበቃ አስተዉለናል፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ተነሳስተዉ ለተቃዉሞ አደባባይ ይወጣሉ፤ከአገዛዙ የታጠቀ ኃይል ጋር ይጋጫሉ፤ሰዉ ይገደላል፤ሰዉ ይቆስላል…ሌላዉ ወደየቤቱ ይመለሳል፡፡
ነገ ሌላ ቦታ ሌላ ተቃዉሞ ይነሳል፤ተመሳሳይ እርምጃ ይወሰድበትና ይዳፈናል፡፡እንዲህ…እንዲህ እያለ ለዛሬዋ ቀን ደርሷል፡፡ ዛሬም ልክ እንደትናንቱ በምዕራብ ኦሮሚያ ሕዝቡ በአገዛዙ ላይ ያለዉን ተቃዉሞ በአደባባይ እየገለፀ ያገኛል፡፡ አግባብና ሊደገፍ የሚገባ ትግል ነዉ፡፡
ይሁንና ዛሬም እንደትናንት፣ምዕራቡ ሲጮህና ሲሞት፣ ምስራቁ ዝም የሚል ከሆነ፣ ደቡቡ ሲፋለም፣ ሰሜኑ ‹‹በእኔ እስካልመጣ…››ብሎ የሚሳለቅ ከሆነ፣ አሁንም ሆነ ወደፊት በለስ ከባለጠመንጃዉ ጋር ነዉ፡፡ ትርፉም መስዋዕትነትን ማብዛት ይሆናል፡፡ስኬታማ ትግል በአነስተኛ መስዋዕትነት ድል የሚመዘገብበት መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ ዋናዉን እየበላ ትርፍ የሚያሰላ ተላላ ነጋዴ መሆን ነዉ፡፡
በሌላ በኩል፣ ትግሉን ከርቀት ሆነዉ የሚያንቀሳቅሱ ወገኞች ካሉ፣ ጥረታቸዉን ማድነቅ እንደተጠበቀ ሆኖ ማድረግ ያለባቸዉን ሁሉ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ያደርጉት ዘንድ መጠየቅም አግባብ ይመስላል፡፡ ለጋ ወጣቶች ሕይወታቸዉን ዋጋ የሚከፍሉበትን ትግል ለወሬ ፍጆታ ፋይዳ ብቻ ዘላቂ ጥቅም ወደሌለዉ አቅጣጫ መግፋት እንዳይኖር መጠንቀቅ የሚያስችል የሞራል ብቃት ሊኖር ይገባል፡፡
በስልታዊነት/በስሌታዊነት እንጂ በስሜታዊነት የሚደረግ ግፊትም ሆነ የሚወሰድ እርምጃ ዉጤቱ ፀፀት ይሆናል፤የሕዝብን መከራና የገዥዎችን ዕድሜም ያራዝማል፡፡
ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር/structure ፣ስልታዊ አመራር(በቅርበትም በርቀትም)…ስሜታዊ ሳይሆን ስሌታዊ የሆነ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ/ተቃዉሞ…ለዉጤታማ ድል እንደሚያበቃ እያሰብን፣ ‹‹Aluta continua!›› እንላለን፡፡

No comments:

Post a Comment