Thursday, 10 December 2015

‹‹እኔ ስያዝ ያየ የ4 አመት ህጻን ለቀናት በፍርሃት ይቃዥ ነበር›› ጦማሪ ዘላለም ወርቃገኘሁ

‹‹እኔ ስያዝ ያየ የ4 አመት ህጻን ለቀናት በፍርሃት ይቃዥ ነበር›› ጦማሪ ዘላለም ወርቃገኘሁ
ዕለቱ ሀምሌ 1/2006 ዓ.ም ነበር፤ ሦስት ሰዓት አካባቢ ይሆናል፡፡ ገና ከእንቅልፌ መነሳቴ ነበር፡፡ እስከ ሰኔ 30/2006 ዓ.ም ድረስ የማስተርስ ዲግሪ መመረቂያ ጽሁፌን እየሰራሁ ስለነበር የተጠራቀመ ድካም ነበረብኝ፡፡ በዚህ ጠዋት አንድ የማውቀው ሰው ደውሎ ‹‹ፈልጌህ ነበር፣ አንዴ ወደ በር ወጣ በልልኝ›› አለኝ፡፡
ከዚያ በቅጡ እንኳ ሳልለባብስ ዓይኖቼን እያሻሸሁ ወደ በር ስወጣ አካባቢው ተከብቧል፡፡ ዞር ዞር ስል ፖሊስና ደህንነት ከቦኛል፡፡ ለሰከንዶች ያህል በድንጋጤ ተሞላሁ፤ በቃ ድርቅ ነበር ያልኩት፡፡ ወዲያው ግን ተመልሼ ተረጋጋሁ፡፡ የሆነ ስሜ ያለበት ወረቀት አጠፍ አድርገው አሳዩኝ፡፡ ከእኔ ስም በተጨማሪ ዳንኤል ሺበሺ የሚል ስም ማየቴ ትዝ ይለኛል፡፡ ሁኔታው ሁሉ ስለገባኝ ድንገት፣ ‹‹ታዲያ ውሰዱኛ!›› አልኳቸው፡፡ በቅጽበት የመጣልኝ ሀሳብ ከዚያ ቦታ ቶሎ ይዘውኝ መሄድ አለባቸው የሚለው ነበር፤ ምክንያቱም እናቴ ይሄን ካየች በድንጋጤ ትሞትብኛለች ብዬ ፈርቼ ነበር፡፡ ደግነቱ በሰዓቱ እናቴ ቤት አልነበረችም፤ ስለዚህ ቶሎ ይዘውኝ ከሄዱ በእንዲህ ያለ ሁኔታ በፖሊስ ተከብቤ ልታየኝ አትችልም፣ ያ ደግሞ ለእኔ ትልቅ እፎይታ ነበር፡፡
ሆኖም ከአካባቢው ቶሎ መሄድ የሚለው ሀሳቤ አልተሳካልኝም፤ ፖሊሶችና ደህንነቶች አካባቢውን ሁሉ ከዘጋጉ በኋላ ወደቤት ገቡ፡፡ ልክ ሲገቡ ፖሊሶቹ መሳሪያቸውን አነጣጥረው ነበር የሚራመዱት፡፡ ለመተኮስ የተዘጋጁ ነበር የሚመስሉት፡፡ በሰዓቱ ከእኔ ሌላ ሁለት የእህቴ ልጆች ግቢው ውስጥ ነበሩ፤ እየተጫወቱ ነበር፡፡ መሳሪያ የለበሱ ሰዎችን ውክቢያ አይተው ህጻናቱ በጣም ደነገጡ፤ አለቀሱ፡፡ አንደኛው ህጻን 4 አመቱ ነበር፡፡ በዚህ ቀን ባየው ሁኔታ ለቀናት ማታ ሲተኛ ይቃዥ ነበር፡፡ እንዲያውም ወንድሜ ይሄን ተመልክቶ እንዴት ህጻን ልጅ ፊት እንዲህ ታደርጋላችሁ በማለቱ ታስሮ ነበር፤ በበነጋታው ቢፈታም፡፡
ቤት እንደገቡ ፍተሻ ጀመሩ፡፡ እያንዳንዷን ነገር አስሰዋል፡፡ እያንዳንዷ ወረቀት ላይ አስፈርመውኛል፡፡ በጣም ረጂም ጊዜ የወሰደ ፍተሻ ነበር ያደረጉት፡፡ እናቴ ሳትመጣ ቶሎ እንዲጨርሱ ብመኝም ሊጨርሱ አልቻሉም፡፡ ስልክ እየተደዋወሉ ስለሚያገኙት ወረቀት ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ አንድ ‹‹ቃሊቲን በጨረፍታ›› የሚል ጽሁፍ ያለበት ጋዜጣ ሲያገኙ፣ ‹‹ይሄ ምንድነው የሚለው?›› አሉኝ፡፡ ‹‹ቃሊቲን በጨረፍታ›› አልኳቸው፡፡ እነሱም የፌዝ እየሳቁ ‹‹በጨረፍታ ሳይሆን በደንብ ታየዋለህ›› አሉኝ፡፡ ለማስፈራራት የተጠቀሙት እንደሆነ በማሰብ ዝም አልኳቸው፡፡
ሶስት ሰዓት የጀመረው ፍተሻ እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ዘልቋል፡፡ ሳትመጣ እንዲወስዱኝ ብፈልግም እናቴ መጣች፡፡ በህይወቴ እናቴ እንዲያ ፊቷ ሲለዋወጥ አይቼያት አላውቅም፡፡ በጣም ደነገጠች፡፡ በኋላ ቀስ እያለች እየተረጋጋች መጣች፤ እንዲያውም በኋላ ላይ ምኝታ ቤቷን ቆማ ያስፈተሸችው ራሷ ናት፡፡ ፍተሻው ሲያልቅ ከነጋ ስላልበላሁ በጣም እርቦኝ ነበር፡፡ ትዝ ይለኛል...ፓስታ ነገር ነበር እሱን በላሁ፡፡ ‹‹እንሂድ›› ሲሉኝ እናቴ ‹‹ልጄን የት ነው የምትወስዱት?›› አለቻቸው፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ‹‹ማዕከላዊ›› አላት፡፡ እኔም በዚሁ የምሄድበትን አወቅሁ፡፡
መኪና ላይ ወጥቼ ከፊትና ከኋላ በታጠቁ ሰዎች በመኪና ታጅቤ ወደ ማዕከላዊ ወሰዱኝ፡፡ እኔን ለመያዝ ወደ አስራ ሁለት ፖሊሶችና አራት ደህንነቶች ነበሩ የተሰማሩት፡፡ ማዕከላዊ እንደደረስን ተመዝግቤ ወደ ውስጥ እንድገባ ተደረግሁ፡፡ መጀመሪያ የገባሁበት ቤት ውስጥ የተቀበለኝ ድምጽ በኦሮምኛ ቋንቋ ስለነበር አልተረዳሁትም፡፡ እኔ የገባሁበት ክፍል ውስጥ የነበሩት እንዳለ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ ‹‹እስር ቤቶች ቋንቋቸው ኦሮምኛ ነው›› የሚለው ዓረፍተ ነገር በአዕምሮየ መጣ፡፡ ሁሉም በኦሮምኛ ሲያወሩኝ ኦሮምኛ እንደማልችል ነገርኳቸው፤ አማርኛ የሚችሉት አወሩኝ፡፡ ከመካከላቸው አበበ ኡርጌሳ የሚባል ልጅ በጣም አረጋጋኝ፡፡ አወራን፡፡ የሚያወራኝ ስላገኘሁ ደስ አለኝ፡፡

No comments:

Post a Comment