Sunday, 29 November 2015

ህወሀት ''ቅማንት'' የሚል አደገኛ ካርድ ስቧል

መሳይ መኮንን
ህወሀት ''ቅማንት'' የሚል አደገኛ ካርድ ስቧል። በኢትዮጵያ ምድር ላይ ተፈጽሟል ለማለት የሚከብድ እጅግ ዘግናኝ ድርጊት ተፈጽሟል። የማንነት ጥያቄ ተገቢ ቢሆንም በህወሀቷ ኢትዮጵያ ግን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ነው። የዲሞክራሲ ጥያቄ ባልተመለሰበት ሁኔታ፡ የማንነት ጥያቄ የጨቋኞችን ዕድሜ የሚያራዝም መድሃኒት ነው። ህወሀት ዲሞክራሲን ሊያመጣ ፈጽሞ የሚችል ድርጅት አይደለም። አፈጣጠሩና እወክለዋለሁ የሚለው ህዝብ የአናሳ ቁጥር ያለው በመሆኑ ከዲሞክራሲ መርህ(Majority rule-Minority right) ጋር የሚጻረር ነው።ቢፈለግ እንኳን አይቻለውም።
ለዚህም ነው የማንነት ጥያቄን በየቦታው እየቀሰቀሰ ህዝብን ከህዝብ እያናከሰ በስልጣን ላይ መቆየትን የመረጠው። እንዲህ አድርገን ካልገዛን በቀር ስልጣን ላይ መቆየት አንችልም ብለው ሟ...ቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በድብቅ የተናገሩት እንዳለ ነገ ከነገ ወዲያ ይጋለጣል።
እናም ህወሀት ዘንድሮ የሳባት የቅማንት ካርድ መጥፎ አየር ይዛ መጥታለች። በጣም አሰቃቂ በሆነ መልኩ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ቪዲዮ በማህበራዊ መድረኮች ተለቋል። ተመልክቼው ራሴን መቆጣጠር እስኪያቅተኝ ደንግጬአለሁ። ከመነሻው ሂደቱን ስንከታተል ስለነበረ ማን ከዚህ አሰቃቂ ድርጊት ጀርባ እንዳለ በሚገባ ተረድተነዋል። ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም በላይ ጥንቃቄ ልናደርግ የሚገባን ግዜ ላይ ደርሰናል። ድንበሩን ለማስረከብ በመጪው ወር ቀጥሮ ተይዟል። በጎንደር ዘግናኝ ድርጊት እየተፈጸመ ነው።
እነዚህ ሁለት ክስተቶች በአንድ ወቅት ላይ እንዲሆኑ የተደረገው ያለምክንያት አይደለም። ስለድንበሩ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ድምጹን እንዳያሰማ በመንደርና ጎጥ ተከፋፍሎ ሁሉም በየሰፈሩ እርስ በእርሱ እየተጠባበቀ፡ አጥር ሰርቶ፡ እየተደገዳደለ እንዲኖር አድርገውታል። በድንበሩ ጉዳይ ከሱዳንና ከህወሀት ወታደሮች ጋር እየተዋጋ የከረመው ይኧው የጎንደሩ ኢትዮጵያዊ ነው። ይህ ህዝብ ለድንበር ማካለሉ እንቅፋት እንዳይሆን ደግሞ ህወሀት ሌላ ካርድ ስቧል። የቅማንት የማንነት ጥያቄ። ጥያቄው ተገቢ አይደለም እያልኩኝ አይደለም። በህወሀት ተቀናብሮ ይህን ጊዜ ጠብቆ መነሳቱ እንጂ።
ጎንደር ሰሞኑን በተከሰተው ዘግናኝ ድርጊት ተወጥራለች። ለመጪው ሌላ የዕልቂት ዳመና አርግዟል። በመሃል የድንበሩ ማካለል ተፈጻሚ ይሆናል። ምን ይበጃል?
ድንበሩ የጎንደር ብቻ አይደለም። በስለት ተከታትፎ እየተገደለ ያለው ኢትዮጵያዊ ወገናችን ነው። እኔ እዚህ ቪዲዮውን መለጠፍ አልፈለኩትም። በየቦታ ስላለ ማየት የሚቻል ይመስለኛል።
ኢሳት ይህን የህወሀት የዕልቂት ድግስ ለማክሸፍ የሚቻለውን ያደርጋል። እንደ ዜጋ፡ እንደ ኢትዮጵያዊ፡ ከምንም በላይ እንደ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር፡ እኔም አቅሜና ሙያዬ በሚሰጠኝ ጉልበትና ዕድል ተጠቅሜ ይህን ኢትዮጵያውያን ላይ የተወረወረውን የጥፋት ሰይፍ ለመመከት ቃል እገባለሁ። ጎበዝ እንደ ትውልድ የምንፈተንበት ዘመን ላይ ነን። መሃሉ ላይ ነን። ወጀብ ከግራና ቀኝ ይዞናል። ተያይዘን ካልወጣን መሃሉ ላይ እንቀራለን። .....ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን ይታደጋት!!!!

No comments:

Post a Comment