የዘመናችን ታላቁ ቤተ መጻህፍት ተቃጠለ የአንድ ሽማግሌ ሞት የአንድ ታላቅ ቤተ መጻህፍት ቤት የመቃጠል ያክል ኪሳራ ነው ይባላል::
(በስሜነህ ጌታነህ)
(በስሜነህ ጌታነህ)
ይሃው ይሄ አዲስ አመት ከገባ በኋላ ይሄው መአተኛ መስከረም ሌላዉን ታላቅ የታሪክ ምሁር ዘዉዴ ረታን ነጠቀን::አምባሳደር ዘዉዴ ረታ በእዉነት ለመናገር እስከ ዛሬ ካነበብኳቸው የታሪክ መጽሃፍት ሁላ እጅግ በመረጃዎች እና በዶክመንቶች የበለጸገ እንዲሁም ማራኪ የቃላት ፍሰትን በዉስጡ ያጨቀ መጽሃፍ ጽፈው ያበረከቱልን ታላቅ ጸሃፊ ነበሩ::
ዘዉዴ ረታ በተለይ የኤርትራ ጉዳይ በተሰኘ መጽሃፋቸው የዛሬይቷ ኤርትራን ለመገልጠል ያበቃትን ምክንያት እና ኤርትራን ከእናት ሃገሯ ጋር ስለመቀላቀል የተደረገውን ታላላቅ የዲፕሎማሲ ጥረቶች አብጠርጥረው እና አንጠርጥረው አሳይተዉናል::ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የስልጣን ጉዞ በተሰኘው መጽሃፋቸውም አጼ ሃይለስላሴ የስልጣኑን እርካብ እንዴት አድርገው እንደተቆናጠጡ ምን አይነት ግለ ስብእና እንደነበራቸው ጨምሮ ሌሎች አበይት ታሪኮችን ከትበዉልን እንደ ሌሎች የታሪክ አዋቂዎች የጋን ዉስጥ መብራት ሳይሆኑ ለሌላው ጮራን የፈነጠቁ ታሪክን በግዙፍ መጽሃፍ እየጻፉ ያስረከቡን ሰው ነበሩ::
አብዛኛዎቹ ስለ ኤርትራ የሚጻፉ መጽሃፎች አንድም በጥላቻና በግልብ የሃገር ፍቅር የተጻፉ ሚዛናዊነት የጎደላቸው ሲሆኑ አንድም የመረጃ እጥረት የሚታይባቸው የተለበለቡ እንጂ ያልበሰሉ ጽሁፎች ነበሩ::
የአምባሳደር ዘዉዴ ረታ “የኤርትራ ጉዳይ”የተሰኘው በሻማ ቡክስ አታሚዎች የቀረበው መጽሃፍ ግን እጅግ የተለየ ድንቅ መጽሃፍ ነበር:: ሌላው ደግሞ ስለ አጼ ሃይለ ስላሴ ከዉልደት እስከ አገዛዝ ዘመናቸው የጻፉት ሁለት ትልልቅ መጽሃፋቸው ነው::የመጀመሪያው “ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የስልጣን ጉዞ” የሚለውና “የቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ መንግስት” የሚለው እጹብ ድንቅ መጽሃፋቸው ነው::
በቅርብ ጊዜ በሰጡት ቃለ ምልልሳቸው ላይ “እድሜ እና ጤና ይስጠኝ እንጂ ከህመም ጋር እየታገልኩም ቢሆን የቀረዉን መጽሃፌን እጨርሰዋለሁ” ብለው ቃል ገብተዉልን ነበር::አይ ሞት ክፉው ሳይጨርሱት ነጠቀን::ይብላኝ ለኛ ላላወቅነው እንጂ እርሳቸውማ ኖረዉበት ያወቁት ታሪክ ነው::
ለኛ እዉቀታቸውን ሊያካፍሉ ከእንግሊዝ ላይብረሪ እስከ ጣልያን ላይብረሪ ድረስ ከኪሳቸው በሚያወጡት ገንዘብ እየተንከራተቱ ባገኙት መረጃ የጻፏቸውና ያሳተሟቸው በደፈናው መጽሃፍ የሚባሉ ታላላቅ ጥራዞች ዛሬም ይሄ ትዉልድ በሚገባ አንብቦ እና መርምሮ በሚገባ የተረዳው አይመስለኝም::
እንግዲህ ታላቁን ቤተ መዛግብታችንን አጣን ዘዉዴ ረታም አረፉ::በሟች ማዘን የለም ባለ መጽናናት ነው ይሉ የለ::በቃ ቀሪ ቅርሳችን የእርሳቸው መጻህፍቶች ናቸው በእነርሱ እንጽናና እንጂ::
ክቡር አምባሳደር ዘዉዴ ረታ ነብስዎትን ፈጣሪ በአጸደ ገነት ያኑርልን:
ክቡር አምባሳደር ዘዉዴ ረታ ነብስዎትን ፈጣሪ በአጸደ ገነት ያኑርልን:
No comments:
Post a Comment