Wednesday, 25 March 2015

“ኢህአዴግ የህዝቡ ብሶት አደጋ እንደሚያስከትል አውቋል” ስትል የአዲስ አበባ የኢህአዴግ የሴቶች ሊግ ም/ል ሊቀመንበር ተናገረች

የሊጉ ም/ል ሊቀመንበር በመሆን ለአመታት ያገለገለችው ወ/ት እየሩሳሌም  አበረ  ከኢሳት ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ “የአዲስ አበባ ህዝብ እንደሚገነፍል በርካታ የዲሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እያነሳ ነው” ብላለች።የታፈነ የመልካም አስተዳደር እና የዲሞክራሲ ጩኸት አለ የምትለው ወ/ት እየሩሳሌም፣ ገዢው ፓርቲም ህዝቡ በከፍተኛ ብሶት ላይ እንደሚገኝና አደጋ ሊያስከትል እንደሚችልም ጠንቅቆ ያውቀዋል ብላለች።ከምርጫ 97 በሁዋላ ኢህአዴግ የተሳካለት ነገር ቢኖር ተቃዋሚዎችን ማፈን ነው የምትለው ኢየሩሳሌም፣ ህዝቡ በሚታየው ነገር ሁሉ ባለመርካቱ ገዢው ፓርቲ ቁጥጥሩን በማጥበቅ የህዝቡን ብሶት ለማፈን ይሞክራል ስትል አክላለች።ወ/ት እየሩሳሌም ድርጅቱን ጥላ ስደትን መርጣለች። ለረጅም አመታት የአዲስ አበባ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ እና በሌሎችም የስልጣን ሃላፊነቶች ላይ ሲሰሩ የቆዩት የኦህዴድ ድርጅት አባል የሆኑት ወ/ሮ አበባ ገብረስላሴም በቅርቡ ኢህአዴግን በመተው፣ በአሜሪካ ጥገኝነት ጠይቀዋል። ከወ/ት እየሩሳሌም ጋር የተደረገው ቃለምልልስ ሰሞኑን ይቀርባል።

የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ለ8ኛ ጊዜ ተመለሰ

• ኢብኮና የአዲስ አበባ አስተዳደር መገናኛ ኤጀንሲ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት መልሰዋል
• ‹‹አማራጫችን እንዳናቀርብ እየተከለከልን ነው›› አቶ ዮናታን ተስፋዬ
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የአዲስ አበባ አስተዳደር መገናኛ ኤጀንሲ የሰማያዊ ፓርቲን የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ‹‹አናስተላልፍም›› ብለው መመለሳቸውን ድርጅቶቹ ለፓርቲው በላኳቸው ደብዳቤዎች ገልጸዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ መጋቢት 16/2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የብሔራዊ ራዲዮ በአማርኛ ስርጭት የሚተላለፍ ‹‹መንግስታዊ አወቃቀር›› የሚል የቅስቀሳ መልዕክት ልኮ የነበር ሲሆን ባለፉት 24 አመታት ተግባራዊ የሆነው የጎሳ ፌደራሊዝም ለግጭት መንስኤ መሆኑን በመረጃ ዘርዝሮ ማቅረቡን የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
ይሁንና ኢብኮ ይህን የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹በተለያዩ ጊዜያት በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ተከሰቱ ያሉትን ግጭቶች በመዘርዘር በህዝቦች መካከል ሌላ ግጭት እንዲቀሰቀስና እንዲባባስ የሚያደርጉና ግጭት የሚያራግቡ፣ አንዱን ብሔር ከሌላ ብሔር የሚያገጩ ናቸው፡፡›› በሚል እንደማያስተላልፍ ገልጾአል፡፡ ከዚህም ባሻገር በመልዕክቶቹ ውስጥ ‹የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት›፣ እንዲሁም ‹የህወሓት/ኢህአዴግ ስርዓት› የሚለው አገላለጽ የፓርቲውን ህጋዊ መጠሪያ የማይወክል በመሆኑ›› በሚል እንደማያስተላልፍ ገልጾአል፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ ግጭቶች በአሁኑ ወቅትም የቀጠሉና የጎሳ ፌደራሊዝሙ እስካለ ድረስ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍሉ መሆናቸውን የገለጸው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ መልዕክቶቹ ከፓርቲው ማንፌስቶ የወጡ፣ ኢብኮ እንዳለው ለግጭት ሳይሆን ከግጭቶቹ መማር እንዲቻልና አሁን ያለው የጎሳ ፌደራሊዝም ከተስተካከለ ችግሮቹ እልባት እንደሚያገኙ በሚያሳይ መልኩ የተላለፈ መልዕክት ነው ብሎአል፡፡ ‹‹እኛ ያቀረብነው አማራጫችን ነው፡፡ አማራጫችን ስናቀርብ ደግሞ የጎሳ ፌደራሊዝም የፈጠረውም ቀውስም በማሳያነት ማቅረብ አለብን፡፡ ይህን እውነታ የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት ዘግበውታል፡፡ አብዛኛዎቹ መንግስትም ያመነባቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ስርዓቱ የሰራቸው ጥፋቶች ይፋ አውጥተን እንዳናቀርብ ስለተፈለገ መልዕክቱን መልሰውታል፡፡ በግልጽ አማራጫችን እንዳናቀርብ ተከልክለናል›› ሲል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ አስተዳደር መገናኛ ኤጀንሲ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹ከሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ ጋር የሚጻረር፣ ብሔር ብሄረሰቦችን ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዲያመሩ የሚገፋፋ፣ የሌላ ፖለቲካ ፓርቲን ስም የሚያጎድፍ ይዘት የተካተተባቸው›› ናቸው በሚል መልሷል፡፡ ይህ የሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ሲመለስ ለ8ኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የአባይ ግድብ ግንባታን በየደረጃው የሚቆጣጠረውን ስምምነት ፈረመች

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በጋራ የፈረሙት አዲሱ ስምምነት ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ በሙሉ ነጻነት የምትሰራውን ስራ እንደሚገድብ ከአረብኛ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመው  ሰነድ አመልክቷል።ሰነዱ ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት በምታደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴና በየትኛውም የግንባታ ደረጃ ላይ አለማቀፉ አጥኝ ቡድን ለሚሰጠው አስተያየት ተገዢ በመሆን እንድትተገብር ይገልጻል። አጥኝ ኮሚቴው የግድቡ ግንባታ የግብጽንና ሱዳንን የውሃ ድርሻ መጠንይቀንሳል ወይም በግብጽና ሱዳን አካባቢያዊ ሁኔታ ላይ ተጽአኖ ያመጣል የሚል ድምደማ ላይ ከደረሰ ካሳ እስከመክፈል የሚያደርስ ግዴታም መጣሉ ተመልክቷል።አጥኚ ቡድኑ የመጨረሻውን የጥናት ውጤት ይፋ ካደረገ በሁዋላ ሶስቱም አገራት እንደሚቀበሉት የተስማሙ ሲሆን፣ ምናልባት አጥኝ ቡድኑ ግድቡ በግብጽና ሱዳን ላይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ያስከትላል ብሎ ቢወስን ኢትዮጵያ የግድቡን ቅርጽ እስከመቀየር ልትደርስ ትችላለች።

ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ፣ ከግብጽና ሱዳን የውሃ ማጠራቀሚያዎችን የሚጎዳ ከሆነም ኢትዮጵያ አገራቱን ፈጥና የማሳወቅና ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርባትም ስምምነቱ ይገልጻል።የስምምነቱ አብዛኛው ክፍል ኢትዮጵያ ስለምትፈጽማቸው ግዴታዎች ትኩረት ያደረገ ነው። ግብጽና ሱዳን ለአባይ ወንዝ የሚያበረክቱት የውሃ ድርሻ ካለመኖሩ አንጻር ስምምነቱ በዋነኝነት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን መብት የሚገድብ ብቻ ሳይሆን፣ የአባይ ግድብ
ግንባታ እጣ ፋንታን ከኢትዮጵያ እጅ አውጥቶ በአለማቀፍ አጥኚዎች እጅ እንዲሆን የሚያደርገው ነው በሚል ትችት እየቀረበበት ነው።ይሁን እንጅ ሶስቱም አገራት ስምምነቱን በማወደስ ለተግባራዊነቱ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

Saturday, 21 March 2015

ተቀላቀሉን፤ ካልሆነም በያላችሁበት ቦታ ተደራጁ!

ተቀላቀሉን፤ ካልሆነም በያላችሁበት ቦታ ተደራጁ!

March 20,2015
ህወሓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ስለሚያደርሰው ዘርፈ ብዙ በደል ብዙ የተነገረለትና የተፃፈበት ብቻ ሳይሆን እየኖርንበት ያለ ሀቅ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብም የሚደርስበትን ስቃይ መታገስ ወደማይችልበት ጫፍ መድረሱ በሰበብ አስባቡ በሚፈነዳዱ ተቃውሞዎች የሚታይ ሀቅ ሆኗል።
በሌሎች አገሮች እንዲህ ዓይነት የሕዝብ ምሬት ሲኖር በጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ጥሪ ሕዝብ ግልብጥ ብሎ አደባባይ ይወጣል። ከሕዝብ አብራክ የወጣው ጦር ሠራዊትና ፓሊስ ከተበደለው ሕዝብ ጎን በመቆም አምባገነኖችን አስወግዶ የሽግግር መንግሥት ያቆማል። በቅርብ ጊዜያት በሕዝባዊ እምቢተኝነት መንግሥት በተቀየረባቸው አገሮች ያየነው እንደዚህ ዓይነቱን ሀቅ ነዉ።

አገራችን ውስጥ ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ በእጅጉ ይለያል። ህወሓት ኢትዮጵያ ውስጥ የገነባው የጦርና የፓሊስ ሠራዊት አመራር በዘር የተደራጀ በመሆኑ የሕዝቡን አጠቃላይ ብሶት ደግፎ ሊቆም ይችላል ብሎ መጠበቅ አይቻልም። ሠራዊቱ እንደ ተቋም ከተበደለው ሕዝብ ጎን እንዲቆም በመጀመሪያ በራሱ በሠራዊቱ ውስጥ ሥር ነቀል ለውጥ መካሄድ አለበት።በዚህ አቅጣጫ የሚሠሩ ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ሠራዊቱ ዘረኛ ገዢዎቹን አስወግዶ እስኪመጣ መጠበቅ አይቻልም፣ አይገባምም። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነት በሕዝባዊ አመጽ መታገዝ አለበት የሚለው ሁለገብ የትግል የትግል ስትራቴጂ ተመራጭ እንዲሆን ያደረገው ዋነኛ ምክንያት የሠራዊቱ ዘረኛ አወቃቀር ነው። በመረጥነው የትግል ስትራቴጂ መሠረት በሁለቱም ግንባሮች – ማለትም፣ በሕዝባዊ አመጽ እና በሕዝባዊ እምቢተኝነት ግንባሮች ሥራዎች መሠራት አለባቸው። ሁለገብ የትግል ስትራቴጂ እምንፈልገው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ላይ እንዲያደርሰን የኢትዮጵያ ሕዝብ በሁለቱም የትግል ስትራቴጂዎች አኳያ መደራጀት ይኖርበታል። ሕዝባዊ የአርበኛ ሠራዊት ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ሁሉ በኢትዮጵያከተሞችና ገጠሮች፤ በሥራና በመኖሪያ አካባቢዎች በምስጢር የተደራጁ ሕዝባዊ የአርበኛ ሲቪል ክበቦችም በብዛት መደራጀት ይኖርባቸዋል።
በዚህም ምክንያት አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ከህወሓት ዘረኛ ፋሽስታዊ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት የሚመኝ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲደራጅ ጥሪ ያቀርባል! እያንዳንዱ ነፃነት ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ከሚያምነውና ከሚመስለው ወዳጁ ጋር ይቧደን፤ ቡድኑንም በሥርዓትና በሚስጢር ያደራጅ።
ከእንግዲህ “ምን እንሥራ? ትግሉን እንዴት እንርዳ?” እያሉ ለሚጠይቁ ወገኖቻችን በሙሉ መልሳችን “ከቻላችሁ ተቀላቀሉን፤ ካልሆነም በያላችሁት ተደራጁ” የሚል ነው። ድርጅት ኃይል ነው። መደራጀት በራሱ ትልቅ ሥራ ነው። ድርጅት ድርጅት የሚሆነው ደግሞ በሥርዓት ሲዋቀርና በሥነሥርዓት ሲመራ ነው። ስለሆነም ነፃነት ናፋቂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሌላ አደራጅና አስተባባሪ እንዲመጣለት ሳይጠብቅ በራስ አነሳሽነት እንዲደራጅ ይህ ጥሪ ተላልፏል።
በሥርዓት የተደራጀ ስብስብ ሲኖር የሚሠራ ሞልቷል። ይህንን መንገርም አያስፈልግም። የተደራጀ ስብስብ ራሱ ሥራዎችን አቅዶ መሥራትም ይችላል። የሚከተሉት ነጥቦች ለአብነት ተዘርዝረዋል።
  1. የተደራጀ ስብስብ ጠላትና ወዳጁን ይለያል። የጠላቱን ጥንካሬና ድክመቱን ከራሱ ጥንካሬና ድክመት ጋር መዝኖ የወገን ኃይልን ጥንካሬ የሚያጎለብቱ፤ ድክመቶቹን የሚቀንሱ እርምጃዎችን በመውሰድ አቅሙን ይገነባል።
  2. የተደራጀ ስብስብ የጠላትን እንቅስቃሴ እየሰለለ መረጃ ለነፃነት ኃይሎች እንዲደርስ ያደርጋል።
  3. የተደራጀ ስብስብ የተቀናጀ የሕዝባዊ እንቢተኝነት ተግባራትን ይፈጽማል። ለምሳሌ፣በሥርዓቱ የደረሰበትን ምሬት በወረቀት ገንዘብ፣ በአስፋልት፣ በታክሲዎችና በግድግዳዎች ላይ ይጽፋል፤ ገንዘቡን የኤፈርት ንብረት ከሆነው ውጋጋን ባንክ ያስወጣል፤ መዋጮዎችና ግብር ያጓትታል ከዚያም አልፎ አልከፍልም ይላል።
  4. የተደራጀ ስብስብ በሥርዓቱ ላይ ለማመጽ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ሁኔታች ተሟልተው አመጽ ሲቀሰቅስ ደግሞ ትግሉ ግቡን ሳይመታ እንዳይበርድ ፀንቶ ይቆማል።
  5. የተደራጀ ስብስብ ወዳጆቹን አስተባብሮ በጥንካሬው ላይ ተመርኩዞ በአካባቢው ባለ የህወሓት ኃይል ላይ ክንዱን ያነሳል።
በአርበኞች ግንቦት 7 እምነት የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተባባሪና መመሪያ የሚጠብቅበት ጊዜ አልፏል። ህወሓት የዘረጋው የአፈና ሥርዓት የጠበቀ ትስስርና ቁጥጥር ያለው ድርጅት ማቆም እንዳይቻል አድርጓል። ስለሆነም ያለን አማራጭ በርካታ ያለዘወትር የበላይ አካል ትክክል ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉ ስብስቦችን በመላው የአገራችን ክፍሎች በአፋጣኝ ማደራጀት ነው። ይህንን ደግሞ ማድረግ ይቻላል።
ወቅቱ ህወሓትን ከጫንቃችን ላይ ለማውረድ የምንደራጅበት ነው። ድርጅት ኃይል ነው፤ አደራጅና አስተባባሪ ሳንጠብቅ በራስ ተነሳሽነት ዛሬውን እንደራጅ!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

Thursday, 19 March 2015

136 መምህራን የሥራ ማቆም አድማ መቱ

136 መምህራን የሥራ ማቆም አድማ መቱ
• ‹‹ከአሁን በኋላ ለመምህራን ማህበርና ለአልማ አንከፍልም!››
በምስራቅ ጎጃም ዞን የደብረወርቅ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 136 መምህራን ዛሬ መጋቢት 10/2007 ዓ.ም የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለፁ፡፡ መምህራን ላይ እየተፈፀመ ያለውን የአስተዳደር በደል ተከትሎ 92 መምህራን ‹‹እኛ በደል እየደረሰብን ቢሆን መምህራን ማህበር ችግራችን እየፈታልን ባለመሆኑ ከአሁን በኋላ አባል እንዳልሆንን እንዲታወቅ፣ በየወሩ ከደመወዛችን እንዳይቆረጥብን›› በሚል ፊርማ አስገብተዋል፡፡ ከመምህራን ማህበር በተጨማሪ በየወሩ ከደመወዛቸው ለአልማ የሚቆረጠው ገንዘብም እንዲቆም መምህራኑ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ባለፉት የመምህራን ስልጠናዎች የምስራቅ ጎጃም መምህራን ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራበት ማሳሰቢያ ተሰጥቶ እንደነበር የገለጹት መምህራኑ በተለይ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ የሆነው አቶ ዘላለም ጌታነህ የወረዳው መምህራን ማህበር ፀኃፊ ከሆኑ በኋላ ጫናዎች እንደበዙባቸው ገልጸዋል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና መምህራን ማህበር ፅ/ቤት የሚሰራው አቶ ዘላለም ዕጩ መሆኑ ከታወቀ በኋላ መምህራኑ አራት ጊዜ እንዲፈርሙ የተጠየቁ ሲሆን ይህም አቶ ዘላለም ለመምህራን ማህበሩ እያደረገ ባለው አስተዋጽኦና በፖለቲካ አቋሙ ምክንያት እየተፈፀመ ያለ በደል ነው ብለዋል፡፡
የመምህራኑን ፊርማ ተከትሎም መጋቢት 9/2007 ዓ.ም የወረዳው ምክር ቤት 18 ያህል መምህራንን ብቻ ጠርቶ ‹‹እንወያይ›› ባለበት ወቅት መምህራኑ ‹‹ካወያያችሁ ሁላችንም አወያዩን እንጅ እኛን ብቻ ነጥላችሁ ልታወያዩን አይገባም፡፡›› በማለታቸው ምክር ቤቱና መምህራኑ ሳይግባቡ ተለያይተዋል፡፡ መምህራኑ በትናንትናው ዕለት ስራ ገበታቸው ላይ እያሉ ተጠርተው ‹‹እንወያይ›› ቢባሉም በዝምታ ተቃውሟቸውን በመግለፃቸው የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ በለጠ ገሰሰ ‹‹አንወያይም ብላችሁ አምጻችኋል፡፡ ስለዚህ ነገ ስራ እንዳትገቡ፡፡ ስራ ገብታችሁ ትምህርት ቤቱ ውስጥ የሰው ነፍስ ቢጠፋ ተጠያቂዎቹ እናንተ ናችሁ፡፡›› በሚል እንደዛቱባቸው መምህራኑ ገልጸዋል፡፡ የወረዳው የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅረአዲስ ሙሉሰው በበኩላቸው ‹‹ለአንድ ቀን ብቻ ሳይሆን ለአንድ ወርም መግባት የለባቸውም›› በሚል መምህራኑ ላይ ቅጣት እንዲወሰን መጠየቃቸው ተገልጾአል፡፡
መምህራኑም ለምክር ቤቱ ‹‹በቃል የነገራችሁንን ውሳኔ በጽሁፍ ስጡን›› የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ውሳኔው በጸሁፍ ሊሰጣቸው እንዳልቻለና የወረዳውን ባለስልጣናት ውሳኔ የሰሙት 136 መምህራን ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የስራ ማቆም አድማው ዛሬ ጠዋት ከተጀመረ በኋላ ተማሪዎች 3፡20 ላይ ክፍል ጥለው በመውጣት መምህራኑን መደገፋቸው ተገልጾአል፡፡
ደብረወርቅ የሰማያዊ ፓር ሊቀመንበር የኢ/ር ይልቃል ጌትነት የትውልድ ቦታ መሆኑን ተከትሎ የብአዴን ካድሬዎች በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
‹‹እኔ አሸባሪ አይደለሁም፡፡ ኢህአዴግ አሸባሪ ነው፡፡ ለሽብር ሀሳቡም ፍላጎቱም የለኝም›› ዳንኤል ሺበሺ
‹‹የተባለውን ለነገር አለማድረጌን ከእኔ በላይ የከሰሰኝ መንግሥት ጠንቅቆ ያውቃል›› ሀብታሙ አያሌው
‹‹ለእኔ ብቸኛው አሸባሪ ህወሃት/ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ የህወሃት/ኢህአዴግ ተቃዋሚ ነኝ›› አብርሃ ደስታ
‹‹ይሄ 19ኛ ችሎት የጦር ፍርድ ቤት ችሎት እየመሰለ ነው›› የሺዋስ አሰፋ
‹‹ሃይማኖቱንና ማኅበረሰቡን ከሚፈራ ህዝብ ወጥቼ እንዲህ አይነት ተግባር አልፈጽምም›› ባህሩ ታዬ
————————
ዛሬ መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙት እና በእነዘላለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ ያሉ 10 ሰዎች ቀርበው ነበር፡፡ መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመቀበል እና ከ1-5ኛ ተራ ቁጥር ያሉ ተከሳሾች በእስር ቤቱ ደረሰብን ብለው ባቀረቡት አቤቱታ ላይ አስተያየት ካላቸው ለመቀበል መሆኑን የችሎቱ የግራ ዳኛ ገልጸዋል፡፡
የተከሰሾቹን የጽሑፍ አስተያየት በጠበቃ ተማም አባቡልጉ በኩል ቀርቦ ከመዝገብ ጋር ከተያያዘ በኋላ ተከሳሾቹ በየተራ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ የግራ ዳኛው በመናገር 1ኛ ተከሳሽን ‹‹በክሱ ላይ እንደቀረበው ወንጀሉን ፈጽመሃል ወይስ አልፈጸምክም?›› ሲሉ ጠየቁት፡፡
ዘላለምም ‹‹አቃቤ ሕግ ባላደረኩት ነገር ህጉን መደገፍ ስለሚሆንብኝ ምንም መልስ አልሰጥም›› ሲል ዳኛው ‹‹በሥነ ሥርዓት ሕጉ ክሱን ክደው ተከራክራል› በሚል መዝግበነዋል›› በማለት መዝገብ ላይ አሰፈሩ፡፡
2ኛ ተከሳሽ አቶ ሃብታሙ አያሌው በበኩሉ ‹‹የተባለውን ለነገር (ሽብር) አለማድረጌን ከእኔ በላይ የከሰሰኝ መንግሥት ጠንቅቆ ያውቃል፤ እረዳለሁም፡፡ አቃቤ ሕግ ለምን እንደከሰሰኝም አውቃለሁ፡፡ የቆምኩለትን ሕጋዊ ፓርቲንም አፍርሶታል፡፡›› ብሏል፡፡
3ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሺም ‹‹ሽብር የሚባለውን ነገር የሰማሁት ከሟቹ ኦሳማ ቢንላዳንና ከዘቶ መለስ ዜናዊ ነው፡፡ አደረክ ለተባልኩት ነገር ሃይማኖቴ፣ ዓላማዬ …አይፈቅድም፡፡ በዚህ ምክንያት ቤቴ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡ እኔ አሸባሪ አይደለሁም፡፡ ኢህአዴግ አሸባሪ ነው፡፡ ለሽብር ሀሳቡም ፍላጎቱም የለኝም፡፡ መንግሥት ፓርቲዬን ለማፍረስ የፈነቀለው …›› ብሎ ሳይጨርስ ፍርድ ቤቱ ንግግሩን እንዲያቋርጥ አስገድዶታል፡፡
4ኛ ተከሰሽ አብርሃ ደስታ መናገር ከመጀመሩ በፊት ‹‹ድርጊቱን መፈጸም አለመፈጸምህን ብቻ ተናገር›› ተብሎ ከችሎቱ ተነግሮት ነበር፡፡ አብርሃም በተረጋጋ መንፈስ ‹‹መልሱ እሱ አይደለም፤ የፈለኩትን እናገራለሁ፡፡ ሀሳቤን ልግለጽ›› ሲል ተናገረ፡፡ ዳኞች ሳይዋጥላቸው እንዲናገር ፈቀዱ፡፡ ‹‹ክሴ ከአሸባሪ ጋር በመገናኘት …የሚል ነው፡፡ አሸባሪ ለሚፈልገው ዓላማ ሰላማዊ ያልሆነ /ሰውን የሚጎዳ ድርጊት የሚያስፈጽም ነው፡፡ ለእኔ ብቸኛው አሸባሪ ህወሃት/ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ ህወሃት/ኢህአዴግ ተቃዋሚ ነኝ …›› የግራ ዳኛው የአብርሃን ንግግር አቋረጡትና ‹‹ክሱ ላይ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚል የለም፡፡ ክሱን መቃወም አለመቃወምህን ብቻ ተናገር›› አሉት፡፡ አብርሃም ‹‹ሕወሃት /ኢህአዴግ፣ ደህንነቱ ማፊያ ነው … ›› ዳኞቹ በድጋሚ አቋረጡት፡፡ አብርሃ ‹‹አልጨረስኩም›› ቢልም ዳኞቹ ከዚህ በላይ ሊሰሙት አልፈቀዱም፡፡
5ኛ ተከሳሽ የሺዋስ አሰፋም ‹‹ዛሬ ለመጨረሻ ጊዜ ነው የምናገረው፣ ስሙኝ›› ሲል ለችሎት ገለጸ፡፡ ዳኞቹ ክሱን መቃወም አለመቃወሙን ብቻ እንዲናገር ገለጹለት፡፡፡ የሺዋስ ‹‹ትንሽ ሁለት ደቂቃ የምትሞላ ንግግር ነች፡፡›› አላቸውና ቀጠለ፡፡ ‹‹ሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 75/4 ላይ ልዩ ፍርድ ቤት ስለማቋቋም ይደነግጋል፡፡ ይሄ 19ኛ ችሎት የጦር ፍርድ ቤት ችሎት እየመሰለ ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ዳኞች ነጻ ስለመሆናቸው ይደነግጋል፡፡ የእኔ ችግር ችሎቱ ላይ ነው፡፡…›› ዳኞች የየሺዋስን ንግግር አቋረጡት፡፡ የሺዋስም ‹‹ዛሬ ብቻ ነው የምናገረው›› በማለት እንዲህ አለ፡- ‹‹በሕገ-መንግሥቱ ላይ ዳኞች ነጻ መሆን እንዳለባቸው ቢቀመጥም የመርማሪ እና ዐቃቤ ሕጎችን ሀሳብ ብቻ የሚሰማው፤ እኛን አይሰማ አሻንጉሊት ፍርድ ቤት ነው፡፡…›› የሺዋስም መናገር የቻለው ይሄን ብቻ ነው፤ ዳኞች ድጋሚ አስቁመውታል፡፡
6ኛ ተከሳሽ፣ ዮናታን ደግሞ ‹‹ያለፈቃድ እንድትናገሩን እየተገደድን ነው›› ብሏል፡፡ 7ኛ ተከሳሽ (ስሙን የዘነጋሁት) ‹‹የተቀነባበረ ክስ ስለሆነ ምንም ማለት አልችልም፡፡›› ሲል 8ኛ ተከሻሽ ባህሩ ታዬም ‹‹ሃይማኖቱንና ማኅበረሰቡን ከሚፈራ ህዝብ ውስጥ ወጥቼ እንዲህ አይነት ተግባር አልፈጽምም፣ አለፈጸምኩምም፡፡ …ጊዜ እውነቱን ይፈርዳል›› ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡ 9ኛ እና 10ኛ ተከሳሾችም ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምንም›› ብለዋል፡፡
ችሎቱም ‹‹ለአንድ ወር የለንም›› ካሉ በኋላ 15 የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለግንቦት 13፣ 14 እና 17 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡


Sunday, 8 March 2015

የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ለአራተኛ ጊዜ በሚዲያ እንዳይተላለፍ ተከለከለ

የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ለአራተኛ ጊዜ በሚዲያ እንዳይተላለፍ ተከለከለ
• ኢቢሲ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹አላስተላልፍም›› ብሎ መልሷል
• ‹‹ኢቢሲ ከገዥው ፓርቲ ጋር ወግኗል›› አቶ ዮናታን ተስፋዬ
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹አላስተላልፍም›› ብሎ መመለሱን ዛሬ የካቲት 29/2007 ዓ.ም ለፓርቲው በላከው ደብዳቤ ገልጾአል፡፡ ኢቢሲ በደብዳቤው ‹‹የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በምስሉ ግርጌ የተቀመጠው እንዲሁም በቅስቀሳ መልዕክታችሁ ውስጥ አልፎ አልፎ የሚታየው ሰንደቅ አላማ ምስል የሀገሪቱን ሰንደቅ አላማ የማይወክልና ህገ መንግስቱን…. የሚፃረር ሆኖ አግኝተነዋል›› በሚል እንደማያስተላልፍ ገልጾአል፡፡
በሌላ በኩል ‹‹ይህ የኢቢሲ ተግባር የሰማያዊን ፕሮግራም ላለማስተላለፍ ሆን ተብሎ የተሰጠ ሰበብ ነው›› ያለው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን ተስፋዬ በህገ መንግስት የተከለከለውን ቅድመ ምርመራ ኢቢሲ እየተገበረው ነው ሲል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
‹‹ህግ ተጥሷል ከተባለ እንኳን ፕሮግራሙ ከተላለፈ በኋላ እንከሰስ ነበር እንጅ ባልረባ ምክንያት አላስተላልፍም ብለው መመለስ አልነበረባቸውም›› ያለው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ሰንደቅ አላማ የሚውለበለበውን እንጅ ከዛ ውጭ ያለን ማናቸውንም ነገር የሚመለከት አይደለም ሲል ኢቢሲ የፓርቲውን መልዕክት ላለማስተላለፍ ያቀረበውን ሰበብ ተችቷል፡፡ አቶ ዮናታን አክሎም ‹‹በአዋጅ 654/201 ላይ የሰፈረው ህግ አንድም ቦታ ተሰቅሎ ስለሚውለበለብ፣ ከመኪና ከሚውለበለብ እና በአደባባይ ከሚያዝ ሰንደቅ አላማ ውጭ ስለ ሌላ አንዳችም የሚከለክለው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ኢቲቪ ለገዥው ፓርቲ በመወገን ፕሮግራማችን እንዳይተላለፍ እያደረገ ነው›› ሲል ወቅሷል፡፡
በተያያዘ ዜና ፓርቲው ነገ የካቲት 30 በሬድዮ ፋና ከአንድ ሰዓት ዜና በኋላ ለሚተላለፈው ፕሮግራም ትናንት ስድስት ሰዓት መልዕክቱን ለራዲዮ ጣቢያው ለማስገባት ቢሞክርም ‹‹ዘግተው ወጥተዋል፣ ሰኞ ነው የሚገቡት፡፡ ሰኞ አስገቡ›› በሚል የሰማያዊ ፓርቲን መልዕክት መልሰዋል፡፡ የፓርቲዎች መልዕክት ከሚተላለፍበት 36 ሰዓት ቀድሞ እንዲገባ እንደተባለ የገለጸው አቶ ዮናታን ሰኞ ጠዋት የሚተላለፍን መልዕክት ‹‹ሰኞ ጠዋት አምጡ›› ብሎ መመለስ ላለማስተላለፍ እንደወሰኑ ያሳያል ብሏል፡፡
ከአሁን ቀደም ኤፍ ኤም 96.3 ሁለት ጊዜ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬድዮ አገልግሎት አንድ ጊዜ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት የመለሰ ሲሆን ይህኛው ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡

አርቲስት ብርሃኑ ተዘራ ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹ወገኔ›› የተሰኘውን ሙዚቃ እንዲቀሰቅስበት ፈቀደ

አርቲስት ብርሃኑ ተዘራ ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹ወገኔ›› የተሰኘውን ሙዚቃ እንዲቀሰቅስበት ፈቀደ
አርቲስት ብርሃኑ ተዘራ በቅርቡ ‹‹ወገኔ›› በሚል ያወጣውን ዜማ ሰማያዊ ፓርቲ ለቅስቀሳ እንዲጠቀምበት መፍቀዱን ለፓርቲው በላከው ደብዳቤ ገልጾአል፡፡ ኤፍ ኤም 96.3 ሰማያዊ ፓርቲ ለቅስቀሳ በላከው መልዕክት ላይ በማጀቢያነት የተጠቀመበት ሙዚቃ የባለ መብቱን ፈቃድ አላገኘም በሚል የቅስቀሳ መልዕክቱን መመለሱ ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) የሰማያዊ ፓርቲን የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ‹‹እንደገና አስተካክሎ ካልላከ ለማስተላለፍ እቸገራለሁ›› በሚል መመለሱን ለፓርቲው በፃፈው ደብዳቤ አስታወቀ፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹በ2007 ዓ.ም አዲስ ላወጡት ‹‹ወገኔ›› የተሰኘው ነጠላ ዜማ ያለውን አክብሮት እየገለፀ፣ እርስዎ በስራዎ የገለጹትና ፓርቲውም የሚታገልላት አንድነቷ የተጠበቀላት ኢትዮጵያ እንድትኖር ለሚሰራው ስራ ይጠቀምበት ዘንድ ሙዚቃውን እንዲፈቅዱልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡›› ብሎ በደብዳቤ በጠየቀው መሰረት አርቲስቱ ፓርቲው ‹‹ወገኔ›› የተሰኘውን ዜማ ለቅስቀሳ እንዲጠቀምበት መፍቀዱን ገልጾአል፡፡
አርቲስ ብርሃኑ ተዘራ ለሰማያዊ በፃፈው ደብዳቤ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ‹ወገኔ› የተሰኘውን ሙዚቃዬን ለመጠቀም የጠየቀኝን ፈቃድ በሙሉ ፍላጎቴ መፍቀዴን በፊርማዬ አረጋግጫለሁ፡፡›› ሲል ገልጾአል፡፡