Monday, 23 February 2015

የአለም ባንክ በኢትዮጵያ የተፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በጽሞና እንዲያቸው ተጠየቀ

የአለም ባንክ በኢትዮጵያ የተፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በጽሞና እንዲያቸው ተጠየቀ

አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ድርጅት ሂውማን ራይትስ ወች ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ በአለም ባንክ ድጋፍ በኢ...ትዮጵያ ውስጥ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ፣ የባንኩን ፖሊሲ የሚጻረሩ ሆነው መገኘታቸውን የአለም ባንክ የውስጥ የምርመራ ክፍል ማሳወቁን ገልጿል። ይሁን እንጅ የባንኩ ማኔጅመንት በባንኩ የውስጥ የምርመራ ቡድን የቀረበውን ሪፖርት የሚቃረንና ባንኩን ከተጠያቂነት የሚያድን ሌላ ሪፖርት አቅርቧል። የአለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ በምርመራ ክፍሉና በማኔጅመንቱ የቀረቡትን ሁለት የተለያዩ አስተያየቶችን ለማየት ከሶስት ቀናት በሁዋላ ይሰበሰባል።
የምርመራ ክፍሉ፣ ከጋምቤላ አካባቢ የተፈናቀሉ ሰዎች ያቀረቡትን አቤቱታ ተንተርሶ ምርመራ ያካሄደ ሲሆን፣ በምርመራውን የአለም ባንክ ራሱ ያወጣውን ፖሊሲ መጣሱን አረጋግጧል። በሂውማን ራይትስ ወች አለማቀፍ የገንዘብ ተቋማትን አስመልከቶ ምርምር የሚያደረጉት ጄሲካ ኢቫንስ እንደተናገሩት ፣ የአለም ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ለሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ተገቢውን ቢታ አልሰጠም። ተመራማሪዋ፣ ባንኩ በኢትዮጵያ ላይ የሚያከናውነውን ፕሮግራም መቀየር ፣ በዚሁ ፕሮግራም ለተጎዱት ችግረኞች መፍትሄ መስጠት ሲችል ያንን አላደረገም ብለዋል።
በሰፈረ ፕሮግራም በርካታ ዜጎች ለችግር መዳረጋቸውንና መንግስት ያከናወነው ሰፈራ ፕሮግራም ከአለም ባንክ ፕሮጀክት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል። በባንኩ የምርመራ ቡድን የቀረቡትን ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳቦችን ተግባራዊ እንደማድረግ፣ የባንኩ ማኔጅመንት በተቃራኒው አሁን የሚታየውን ችግር የሚያጠናክር ሌላ የድርጊት መርሃ ግብር ነድፏል ሲል ሂውማን ራይትስ ወች ገልጿል።
የምርመራ ቡድኑ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በሰብአዊ መብት ዙሪያ ላይ የሚሰሩ የሲቪል ሶሳይቲ ተቋማትን ለመቆጣጠር የወጣው ህግ እንዲሻሻል አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን አለመውሰዱ በመግለጫው ጠቅሷል ።
የአለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የማኔጅመንቱን መልስና አዲስ የወጣውን የድርጊት መርሃ ግብር በመመለስ፣ የምርመራ ቡድኑ ባነሳቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ሂውማን ራይትስ ወች ጠይቋል።
ለትክክለኛ ልማት እንቅፋት የሆነው የሰብአዊ መብት ጉዳይ ትኩረት ያገኝ ዘንድ በባንኩና በኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል ውይይት ሊካሄድ እንደሚገባውም የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ጠይቋል።
ለጋሽ አገራት በኢትዮጵያ የሚታዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ግምት ውስጥ እንደማይከቱ የሚያመለክተው መግለጫው፣ በፕሮጀክቶች የድሆችን ተሳትፎ እንዲሁም ከሚለገሰው ገንዘብም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ፕሮግራም መነደፍ እንዳለበት ድርጅቱ አስታውቋል።


Thursday, 5 February 2015



ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ከተናገሯቸው ታሪካዊ ንግግሮች በጥቂቱ !

- ሰው ሁሉ እኩል ስለሆነ ማንም ሰው ሰውን ባሪያ አይበል ።
...
- ሁሉም ሰው በየኃይማኖቱ ይደር ።
- ድኻ እወደደበት ቦታ ይቀመጥ ። በዘር ፣ በወገን ልዩነት አይከልከል ።
- የመሬት ጥያቄ ላቀረቡ የውጭ አገር ሰዎች ንጉሡ የሰጡት መልስ፡- ‹‹ የኛ አገር ፍትሐ ነገሥት ልዑሎች መሬት ይሽጡ አይልም ። ያገሬ መሬት ባለቤቱ ሌላ ነው ። ከአባቶቻቸው እየተቀበሉ ያቆዩት መሬት ነው ።... መሬቱ የሁሉም ስለሆነ አይሸጥም ። ማንም ሰው መሬቱን ሊሸጥ አይችልም ። መሬትን መሸጥ፣ መስጠትም የሚችለው የመሬቱ ጌታ ነው ››
- ለመንግሥት ተሿሚዎች የሰጡት መመሪያ፡- ‹‹… እንቅልፍ ሳትወዱ ፣ መጠጥ ሳታበዙ፣ ገንዘብን ጠልታችሁ ተግታችሁ ሥራችሁን ፈጽሙ ። እኔ እናንተን ስለአመንኩ እናንተም የምታምኑትን ፣ ገንዘብ የማይወደውን፣ ድኻ የማይበድለውንና የሚረዳችሁን ሰው እያመለከታችሁኝ ከሥራው በመግባት መንግሥታችንን እርዱ ››
- በጣም ወደኋላ የቀረን ሕዝቦች ነን ። ገና የሚሠራ ብዙ ሥራ ስላለ ወጣቶቻችን መማር አለባቸው ።
- አባት ያለህ የአባትህን እሰጥሀለሁ፤ አባትህን መርቅ ። አባት የሌለህ አባትህ እኔ ነኝና ደጅ ጥናኝ ።
- እኔ ቤት እንጀራ የለም ። እንጀራ ያለው ትምህርት ቤት ስለሆነ ፤ እሠራሁት ትምህርት ቤት ልጆቻችሁም እያስገባችሁ አስተምሩ ።
- የኔ ርስት ኢትዮጵያ ናት ፤ የግል ርስት አልፈልግም ። ደግሞስ የተሾምነው እርስት ከተካፈልን ለሕዝቡ ማን ያካፍለዋል?
- ሐገራችን አንድትለማ የሚቀርቡንን ሁሉ በታላቅ ደስታና በአክብሮት እንቀበላቸዋለን ። በሌላ ለሚመጡብን ግን ፤ ሁላችን ሳናልቅ ሀገራችንን ለባዕድ አሳልፈን እንሰጥም ።
- የሚጠሉህን ሰዎች ከማጥፋት ፤ የሚጠላብህን ማጥፋት እንዲሉ ፤ የሸፈቱባቸውን ፣ የወጉአቸውንና ያሤሩባቸውን ሰዎች በጋብቻ ፣ በዝምድና ወይም ወዳጅ አድርገው ያቀርባሉ እንጂ ክፉን በክፉ መመለስና መበቀልን አይሹም ።
 -አንድ የፈረንሳይ ዜጋ የቦታ ግዥ ፈቃድ ሲጠይቃቸው ምኒልክ በሰጡት መልስ ፡- ‹‹ ያገሬ መሬት የሁሉም
ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ፤ መሬት መሸጥ መለወጥ የሚችለው ሕዝቡ ነው ። ደግሞስ የውጭ ዜጎች መሬት እንዲገዙ ከፈቀድኩና ባለመሬት ከሆኑ ፤ ለኔ ምን ቀርቶ እገዛለሁ ? ›› አሉ ።
ምንጭ ፡- የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ መጽሔት ቁጥር 1. ነሐሴ 1992 ዓ.ም
ከገጽ 16 እስከ 17