Wednesday, 28 January 2015

ሄሊኮፕተር በመያዝ ወደ ሶስተኛ አገር የጠፉት የአየር ሃይል ባልደረቦች በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገለጹ


ሄሊኮፕተር በመያዝ ወደ ሶስተኛ አገር የጠፉት የአየር ሃይል ባልደረቦች በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገለጹ

ባለፈው ወር ሄሊኮፕተር ይዘው የጠፉት ሻምበል ሳሙኤል ግደይ፣ መቶ አለቃ ቢልልኝ ደሳለኝ እና ቴክኒሻን ጸጋ ብርሃን ግደይ በተረጋጋ እና በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለኢሳት ገልጸዋል።
ፓይለቶቹ በሚገኙበት ሶስተኛ አገር ውስጥ ሆነው ከኢሳት ጋር ግንኙነት የመሰረቱ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረገው የነጻነት ትግል አስተዋጽኦ ለማድረግ መዘጋጃታቸውን ተናግረዋል።
ሶስታችንም በአንድ ላይ የምንመደብበትን ጊዜ ስንጠብቅ ቆይተን ነበር ያሉት ፓይለቶቹ፣ አጋጣሚው ሲፈጠርላቸው ቀደም ብሎ ባወጡት እቅድ መሰረት መጥፋታቸውን ገልጸዋል።
ጉዞአቸውን ወደ ሶስተኛ አገር በሚያደርጉበት ወቅት ከራዳር እይታ ውጭ ለመሆን እስከ 10 ሜትር ድረስ ዝቅ ብለው መብረራቸውን የገለጹት ፓይለቶቹ፣ ካሰቡበት ቦታ ሲደርሱ ነዳጃቸው ማለቁን ተናግረዋል።
ለምን ወጣችሁ ተብለው የተጠየቁት ፓይለቶቹ፣ በአየር ሃይል ውስጥ የሚታየው ዘረኝነት፣ አድልዎና የአስተዳደር መበላሸት ይህን ውሳኔ እንዲወስኑ እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል።
እድሉ ቢገኝ አብዛኛው የአየር ሃይል አባል ስርአቱን ትተው ለመውጣት ዝግጁ መሆናቸውን ፓይለቶቹ ገልጸዋል። ፓይለቶቹ ሁኔታዎችን አመቻችተው ለኢሳት ቃለምልልስ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ የኢሳት የጋዜጠኞች ኤርትራ በተገኙበት ወቅት በተለያዩ ወራት ኤርትራ የተገኙነትን በርካታ የአየር ሃይል አባላት አነጋግረዋል።
የሱ 27 እና የሚግ 23 አብራሪዎችን ጨምሮ በርካታ የተዋጊ ሄሊኮፕተር ፓይለቶች ኤርትራ ከሚገኙ የተቃዋሚ ሃይሎች ጋር በመቀላለቀል በመታገል ላይ ናቸው። ኢሳት ከፓይለቶች ጋር ያደረገውን ቀለምልልስ በቅርቡ ይለቃል።
 ኢሳት ዜና

Tuesday, 27 January 2015

አዜብ ጌታቸው
የአርቲስት ሜሮን ጌትነት “አትሂድ” የተሰኘው ግጥም ሌላውንም አርቲስት እያነቃቃ ነው። ግጥሙ መቼም የአመቱ ምርጥ ግጥም ነው ብል አካበድሽ! አልያም የጾታ አድልዎ ነው እንደማልባል ተስፋ አደርጋለሁ። ብባልም ግድ የለኝም። ለለውጥ ያህል “የሴት ትምክህተኝነት” ይጀመር መሰለኝ።
የሆነው ሆኖ የአርቲስት ሜሮን ጌትነትን ግጥም ደግሜ ደጋግሜ ሰማሁት ። የህዝብን እውነተኛ ስሜት የተሸከመ ነው። በሃገራችን ኢትዮጵያ የሚገኙት “የጥበብ” ባለሟል ነን ባዮች በስራቸው ውስጥ በስህተት እንኳ እውነት እንዳይቀላቀል አበጥረው፤ አንጠርጥረው፤ እያንጓለሉ በሚጥሉበት መድረክ እውነትን እንደወረደ መስማት ያስደንቃል። ብርቅም ያደርገዋል። የሜሮን ግጥም ተወዳጅነት የሚመነጨው ከዚህ ላይ ይመስለኛል።
አነሳሴ የሜሮንን ግጥም ለመገምገም አይደለም። በምን አቅሜ!። ደግሞም እኮ የሜሮንን ግጥም ሕዝብ ገምግሞታል።በልማት ሰበብ ቤቱ የፈረሰበት ድሃ ህዝብ ሁሉ “የልብ አውቃ” ብሏታል። የአርቲስትና የጥበብ ትልቁ መገለጫው ደግሞ ይህ ነው፡፤ “የልብ አውቃ” መሆን። የህዝብን ልብ ማወቅ።
ሜሮን ጌትነት ብዙ ድራማና ፊልሞችን የሰራች፤ በወጣትነት እድሜዋ በህዝብ ዘንድ ግዙፍ ሊባል የሚችል እውቅና ያካበተች አርቲስት ነች፡፡ ይህ የሚነግረን ደሞ ጥሩ ኑሮ ልትኖር እንደምትችል ነው። ጥሩ ቤት፤ ጥሩ መኪና ....ብቻ ጥሩ ጥሩ ነገሮች ሁሉ ማግኘት የሚከብዳት አይደለችም።
የጥበብ ሰው ነችና በግጥሟ ያገኛናት ግን ግድግዳው የተሸነቆረበት የአንድ ድሃ ቤተሰብ አባል ሆና ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ያችን ሽንቁር ግድግዳ ለመድፈን የተቦካቺው ጭቃ ተዝቃ ተጣለች! ። አስቡት የዚህን ምስኪን ቤተሰብ ስቃይ። የሜሮን የምናብ ቤተሰብ ።
አርቲስት የህዝብ፤ ህዝብም የአርቲስት ነው የሚባለው ለዚህ ነው። ምቾትና ድሎት ያልተለየው ኑሮ እየኖረ እንኳ በምናብ ጉዞው ልትወድቅ አንድ ሃሙስ በቀራት ጎጆ የመሸበት እንግዳ ሆኖ ያድራል። የሚላስ የሚቀመስ ካጣ ቤተሰብ ጋር በባዶ ማዕድ አንድ ላይ ይሰየማል ። ርሃብ ስንት ቀን እንደሚሰጥ ጠይቆ ሳይሆን ተርቦ መልስ ለማግኘት ይጥራል። ባጠቃላይ የህዝብን ውሎ ውሎ፤ የህዝብን አዳር አድሮ፤ ስሜቱንም አደባባይ አውጥቶ ይተነፍስለታል። ሜሮንም ያደረገቺው ይህንኑ ነው። አካበድኩ እንዴ? አይመስለኝም።
የሜሮንን በዚሁ ላብቃና ወደ ሌላዋ አርቲስት ላምራ። ውደ አርቲስት አስቴር በዳኔ። ዛሬ ሁለቱም ጀግኖቼ ሴቶች ናቸው። ግዜው የሴቶች ሆነ መሰለኝ?።
አርቲስት አስቴር በዳኔን በመጀመሪያ ያየኋት “ቀዝቃዛ ወላፈን” በተሰኝ ድራማ ነው። ከዚያ በኋላ አንድ ሁለት ድራማ ላይ ሳላያት የቀረሁ አይመስለኝም። እንደ ሜሮን ጌትነት በመሪ ተዋናይነት የሰራችባቸው ፊልሞች/ድራማዎች ብዙ አይመስሉኝም። ሳላያቸው ቀርቼ ከሆነ አላውቅም። እንደገባኝና በኢሳት ላይ ከተወልደ በየነ ጋር ካደረገቺው ቆይታ እንደተረዳሁት ፤ ከተዋናይነት በተጨማሪ የፕሮዲውሰርና ዳይሬክተርነትን ሙያ አዳብላ እንደያዘች ነው። ድንቅ ችሎታ ነው። ያም ሆነ ይህ አስቴር በዳኔ የጥበብ አምባ ሰው ነች። የጥበብ አምባ ሰዎች ደግሞ ትልቁ መለያቸው እውነትና የህሊና ነጻነት ነው ሲባል እሰማለሁ። የሁለቱ ቁርኝት “ያለ ፍርሃት እውነትን መግለጽ መቻል” ማለት ይመስለኛል። አስቴር በዳኔም ሰሞኑን ያረጋገጠቺው እውነትኛ የጥበብ አምባ ሰው መሆኗን ነው። ሃሰተኛ የጥበብ አምባ ሰው አለ ወይ? ብላችሁ ለምትጠይቁኝ፦ መልሴ የለም ነው። ሲጀመር እውነተኛ ካልሆኑ የጥበብም ሰው አይደሉምና ነው። (ተለጣፊ ልንላቸው እንችላለን ወይ? የሚል ጥያቄ የሰማሁ መሰለኝ ፤ በሏቸው ብቻ እኔ ልቀጥል ተውኝ)።
አስቴር በዳኔ ደደቢት በርሃ ላይ ከባለስልጣናቱና ከአርቲስት አምባ ጎረቤቶቿ ጋር ተሰይማለች። በደደቢት ባለስልጣናቱ ግብር ጥለው ምድረ ....እያበሉ ገድላቸውን በጀምስ ቦንዳዊ ስልት ይተርካሉ። እየበሉ! እየጠጡ! ዝም...” እንዳይባል የፈራው “የ”ሰራዊት ሰራዊት እጁ ቲማቲም እስኪመስል ያጨበጭባል። አስቴር በዳኔም ከጎረቤቶቿ ላለመለየት ይህንኑ አድርጋ ይሆናል። በኋላ ግን ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም ብላ ነው መሰለኝ ከአጨብጫቢው የሠራዊት “ሠራዊት” ለየት ያለ ነገር አደረገች። ለግብር ጣዮቹ ባለስልጣናት ህሊናዋ ውስጥ ሲጉላላ የነበረ ጥያቄ አቀረበች ።
ጉድ ፈላ! የአጨብጫዊ ሰራዊት “ሙድ” ነው የሚሉት ሙድ ተበጠበጠ። ብርንዶና ብላክ ሌብሉን አረከሰችባቸው። እሷ ግን ህሊናዋን አጸዳች።
ተቃዋሚ የሚለው ቃል! ጠላት የሚል ስሜት ይፈጥራልና ለምን ተፎካካሪ አይባልም። 23 አመት ስልጣን ላይ ቆይታችኋል አሁንስ በምርጫ ትወርዳላችሁ ወይስ....? አይነት ይዘት ያለው ጥያቄ ጠየቀች።(የጻፍኩት ቃል በቃል ሳይሆን ፍሬ ሃሳቡን ነው) ።
የሚገርመው ነገር አስቴር የጠየቀቺውን ጥያቄ ለመመለስ የሞከረው የሃገሪቷ መከላከያ ሰራዊት ቁንጮ የሆነው ኤታ ማዦር ሹሙ ጄነራል ሳሞራ ነው። (የአስራ አንደኛ ክፍሉ ብቸኛ አፍሪካው ጄነራል)። ይህ ሰው የአስቴርን ጥያቄ ለመመለስ ህገ መንግስቱ እንደማይፈቅድለት እንኳ አልተረዳም። የህገ መንግስቱን አንቀጽ ፹፯ የሚያውቀውም አይመስልም። በተለይ ደግሞ በህገ መንግስቱ አንቀጽ ፹፯ ተራ ቁጥር ፭ ላይ የተቀመጠው ሳሞራ የአስቴርን ጥያቄ መመለስ እንደማይችል የሚያስረግጥ ነው።
ስለ ብሄራዊው መከላከያ ሰራዊት ድንጋጌዎችን የያዘው አንቀጽ 87 ተራ ቁጥር 5፦ የመከላከያ ሰራዊቱ ለየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ወገናዊነት በሌለው መልክ ብሄራዊ ግዴታና ኃላፊነቱን ይወጣል። ይላል።
አጅሬ ግን ምን ገዶት! እውር ድንብሩን ለመመለስ ሞክረ። በተለመደው “ኢህአድጋዊ ተቃዋሚን የማጠልሸት” ዘይቤ ተቃዋሚዎች የሃገርን ጥቅም አሳልፈው ይሰጣሉ። ሰራዊት እንዲበተን፤ ሃገር እንድትጠፋ ይሰራሉ። አለና ህገ መንግስታዊ ሳይሆን ህገ - ህውአታዊ መልስ ሰጠ። በኋላ ላይ ሌሎቹ ባለስልጣናት እየዘባረቀ መሆኑን በጥቅሻ ነገሩት መሰል፤ እኔ ምድብተኛ ወታደር ስለሆንኩ ይህንን ጥያቄ ሌሎቹ ይመልሱ ብሎ ማይክ ሰጠ። ያም ሆነ ይህ አስቴር በዳኔ ህሊናዋ ያዘዛት ፈጸመች። በዛው ቅጽበት ደግሞ የሆዳቸውን ከተንበሪ ወለል አድርገው ከፍተው ምግብና መጠጡን በተሳቢ እያስጫኑ የሚያስገቡት የአጨብጫቢው ሠራዊት አባላት “በሰረገላ ቁልፍ የተከረቸመ” ህሊና ተንኳኳ። ... አይከፍቱት ነገር ቁልፉን ከየት ያምጡ...? ከተሸጠ ቆየ። የህሊናቸውን ኳኳታ ለማምለጥ ምን አማራጭ ነበራቸው....? ምንም! ለዚህ የዳረገቻቸውን አስቴር በዳኔን መርገምና መሸሽ ብቻ! ! አስቴርን ሸሹ.....! አስቴር እድፋቸውን የሚያሳይ መስተዋት ሆነችባቸው። ለምን አይሸሿት። አሁንም የአስቴርን በዚህ ላብቃና ወደ ሌላው አርቲስት ልለፍ።
አርቲስት ከምለው ገጣሚ ብለው ይሻላል። የማወራላችሁ ስለ ገጣሚ ታገል ሰይፉ ነው።
ታገል ሰይፉ ጥሩ ገጣሚ ነው። በተለይ በምስል እያቀናበረ የሚያቀርባቸው ስራዎቹ አስተማሪነታቸው የሳሳ ቢሆንም አዝናኝ ናቸው። ሌሎች በርካታ ስራዎች እንደሰራም አውቃለሁ። አሁን ላተኩር የፈለኩት ግን ሰሞኑን ለጆሮ በበቃው ቃለ ምልልሱ ላይ ነው።
ከኢትዮፕካ ሊንክ ጋር ባደረገው ረዥም ቆይታ ብዙ ነገሮችን አንስቶ ብዙ ነገሮችን ጥሏል፡፡ የኔን ትኩረት የሳቡት ግን ሁለት ነገሮች ናቸው። 1ኛው ደደቢት እንድሄድ ተጋብዤ ስለማላምንበት አልሄድም ብዬ ቀረሁ! የሚለውና 2ኛው መለስ ዜናዊ ለኪነ ጥበብ እድገት ምን አስተዋጾ አድርገዋል? ተብዬ ተጠይቄ፤ ምንም ! የሚል መልስ ሰጥቼ ነበር። ጠያቂዎቼ ግን ቆርጠው አላወጡትም። በማለት የተናገረው ነው። የመለሰው እንዳልል ጥያቄ አልቀረበለትም።
ደደቢት አልሄድም ብሎ ስለመቅረቱ የተናገረው ወቅታዊ ጉዳይ ስለሆነ ነው ብዬ መቀበል አልከበደኝም። ስለ መለስ ዜናዊ ለኪነ-ጥበብ እድገት ምንም አስተዋጾ ያለማድረግ በድፍረት ተናግሮ በሳንሱር መቀስ ስለ መቆረጡ ዛሬ ላይ መናገሩ ግን ምንም መነሻ ምክንያት ላገኝለት አልቻልኩም። ለኔ እንደገባኝ ታገል ሰይፉ በዚህ ቃለ መጠይቁ ለአድማጭ ሊያሲዝ የፈለገው ፡ የማላምንበትን ነገር አላደርግም ለማለት የማልፈራ፤ ባለስልጣናቱንም ቢሆን በድፍረት የምተች ፤ ለህሊናዬ እንጂ ለማንም ለምንም የማላጎበድድ .... ነኝ የሚለውን ጭብጥ ይመለኛል።
ደደቢት እንዲሄድ ሲጋበዝ ፤ ስለማላምንበት አልሄድም! ብሎ መቅረቱ የሚደነቅ ነው። ህሊና የማይቀበለውን ነገር በይሉኝታም ሆነ በፍርሃት ያለመፈጸም ድንቅ ስብዕና ነው። ለኔ ደግሞ ከሱ ድፍረት በስተጀርባ የታየኝ ግብዣቸውን ያጣጣለባቸው የደደቢት አንበሶች (ያልተለመደ)ትዕግስት ነው። ያም ሆነ ይህ ታገል ሰይፉንም ለድፍረቱ የደደቢት አንበሶችንም ለትዕግስታቸው ብራቮ ብናላቸው ኪሳራ የለውም።
በብራቮ ላልፈው ያልቻልኩት መለስ ዜናዊ ለኪነ-ጥበብ ምንም አስተዋጾ አላደረጉም ብዬ ደፍሬ ተናግሬ ነበር። ቆርጠው አወጡት የሚለው ወቅቱ ያለፈበትን ነገር ነው።
ይህን አባባሉን መቀበል ያቃተኝ ያለምክንያት አይደለም። አዎ! ታገል ሰይፉ መለስ ዜናዊ በሞቱ ግዜ ውዳሴ- ግጥሙን በምስል አቀናብሮ የእዝን መስጠቱን ሳስታውስና ለኪነ-ጥበብ ምንም አስተዋጾ አላደረጉም ብዬ ተናገርኩ ማለቱን ሳነጻጽር ፤ አልጣጣም ብሎኝ ነው። ታገል ለጠ/ሚሩ እዝን ካቀረበው ግጥም ጥቂቶቹን ስንኞች እንመልከት
እስካሁን መድከሜ፤
ላንቺም ላከላቴ
ድንቁርናሽ ሞቴ!
እድገትሽ ህይወቴ
ብልጽግናሽ ህልሜ
ዋ! ጀግናው ወንድሜ
ሳተናው .. በርሜጎ
ህመሙን ዋጥ አርጎ ....
በማለት ለኢትዮጵያ እድገት ሲሉ የራሳቸውን ህይወት አሳልፈው የሰጡ ሊቅ፤ የሴት፤ የህጻን ጠበቃ....ሲል መወድስ ያቀረበላቸውን ጠ/ሚር ለኪነ ጥበብ አስተዋጾ አላደረጉም ብሎ መውቀሱ በራሱ ተገቢ አይመስለኝም። አንድ ጠ/ሚር ስንቱን መሆን ይችላል? ። እሳቸው ጥሎባቸው ከራሳቸው ሌላ ጸሃፊ አይወዱ!
ደግሞስ ውዳሴያቸው በግጥም፤ በዘፈን፤ በዜና፤ በእንጉርጉሮ በጎዳና ተዳዳሪዎች እንኳ ሳይቀር ከየአቅጣጫው በሚዘንብበት ወቅት ለኪነ ጥበብ እድገት አስተዋጾ አለማድረጋቸውን የሚገልጸው አስተያየቱ ያለመቅረቡ ነው የሚያስደንቅ ወይስ ይህን ተናግሮ በዝምታ መታለፉ? ግራ የሚያጋባ ስሞታ...
ጠ/ሚሩ ለኪነ ጥበብ አስተዋጾ አላደረጉም ማለቱን ተጠራጥሬ አልያም ዋሸ ማለቴ አይደለም። ብሎ ሊሆን ይችላል። የኔ ጥያቄ ማለቱን ለምን አሁን ይፋ አደረገ? የሚል ነው።
ይህን የምለው(የምጠይቀው) ታገል ሰይፉ ከስርአቱ ባለስልጣናት ጋር ተሞዳሙዶና አጎብድዶ የሚኖር እንጂ እሱ እንደሚለው የህሊናው ታዛዥ አለመሆኑን በበርካታ ስራዎቹ ያሳየ መሆኑን ስለተገነዘብኩ ነው።
ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ያሳተመውን “በሚመጣው ሰንበት” የተሰኘ የግጥም መድበል በመታሰቢያነት ያበረከተው ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ልጆች ሲሆን በመጽሃፉ ላይ እንዲህ በሚል አስቀምጦታል፡፡
“አባታቸው ለሚወዳቸው ልጆቹ ፍቅር የሚሰጥበት ጊዜ ያጣ፡ ሙሉ እድሜውን ለህዝብ/ለሃገር/ የሰጠ ነበር መታሰቢያነቱም ለነሱ ለሰምሃል፡ ለማርዳና ለሰናይ ይሁን”
ታዲያ ለስነ ጽሁፍና ኪነ ጥበብ አስተዋጾ ላላደረጉ ጠ/ሚር ቤተሰብ የጥበብ ስራን በመታሰቢያነት ማበርከት ምን ማለት ይሆን?
በዚሁ መጽሃፍ ላይ ምስጋና ካቀረበላቸው ሰዎች አንዱ ደግሞ አቶ በረከት ስምዖን ናቸው። አቶ በረከትን እንዲህ ብሏቸዋል።
(“አንተ ከሩቅ ስትታይ ከፍተኛ ባለስልጣን ነህ፡፡ እየቀረቡህ እየቀረቡህ ሲመጡ ግን ከስልጣንህ ወርደህ ወደ ሰውነት ወደ ወዳጅነትና ወደ ወንድምነት መለወጥ ትጀምራለህ…”.)
የኔ መነጽር ደግሞ አቶ በረከት ደሞ የታገል ሰይፉን የሙያ አጋሮች/ጎረቤቶች (ለህሊናቸው ያደሩ ጋዜጠኞችን፤ ጦማሪያንና...) በሃሰትና በተቀናበረ ክስ ዘብጥያ እየጣሉ፤ ከሃገር እያሰደዱ ሲያሰቃዩ የኖሩ ባለስልጣን መሆናቸው ነው የሚያሳየኝ። እናም ይህን ሳስተውልና ታገል ሰይፉ ከኝህ ሰው ጋር ያለው ቅርበት ከወዳጅነት ልቆ ወደ ወንድምነት መዝለቁን ስመለከት የዚህ ገጣሚ “ለህሊናዬ ታዛዥ ነኝ” ጩህትን ለመስማትም ያቅለሸልሸኛል።
አሁንም በኔ እይታ አቶ በረከት ከቶውንም ለህሊናው የሚገዛ ወዳጅ ሊኖራቸው አይችልም። ያ ቢሆንማ ለህሊናቸው የተገዙት እነ እስክንድር ነጋ፤ ርዮት አለሙ ፤ ተመስገን ደሳለኝ ፤ አብርሃ ደስታ ፤ ሌሎችም እንደ ታገል ሁሉ ወዳጆቻቸውና ወንድሞቻቸው በሆኑ ነበር። እናም በታገል ሰይፉ የሰሞኑ ቃለ መጠይቅ ተደምማችሁ እጃችሁ ቲማቲም እስኪመስል ያጨበጨባችሁ ወገኖች ሆይ! ቆም ብላችሁ አስቡ። ይህን መሰል አጎብዳጅ ሰው ስታወድሱ እስክንድር ነጋ፤ ርዮት አለሙ ፤ ተመስገን ደሳለኝ... የታሰሩለትን አላማ እያጠለሻችሁ እንደሆነ ይታያችሁ።
የታገል ሰይፉ የሰሞኑ ቃለ መጠይቅ ። “በአስራ አንደኛው ሰዓት ህዝባዊነትን ለመከተብ” ከመፈለግ ውጭ ሌላ ምንም መገለጫ ያለው አይመስለኝም። ሰሞኑን ለሜሮንና ለአስቴር በዳኔ የተጨበጨበውን አይነት “የጀግና ሞገስ” ቢያስገኝልኝ ብሎ የወተወተው እንዳሰበው ፍሬ የያዘለት አይመስለኝም።ሊይዝለትም አይችልም...የበረከት ወዳጅ የኢትዮጵያዊውን ወገን ወዳጅነት ከሚያገኝ ዝሆን በመርፌ ቀዳዳ ....ይቀላል።
እኔም ታገል ሰይፉን በራሱ የግጥም ስልት እለዋለሁ፡
ይሄ ታገል ሰይፉ..
የገጣሚ አፋፉ
የበረከት ወዳጅ....
ለህሊናው ሰጋጅ...
ነኝ ብሎ ሲፈክር
ታዘበው እስክንድር..
በቃ በቃ ተውው ...
ይቅርብህ ጭብጨባው
እንደ ሜሮን ሞገስ
እንደ አስቴር መወደስ
አልተገኝም ይቅር...
ይልቅ ከወዳጅህ ከበረከት እደር ....
በቃ ተወው ይቅር ..
ከስንኙ ጋር የሚሄደውን ምስል እሱ ይርዳኝ።
እንደ ታገል ሰይፉ ሁሉ “ሞገስን ፍለጋ” በሚል ቃለ መጠይቅ ለህሊናቸው ተገዢ መሆናቸው ለማወጅ ድፍረት ወይም አጋጣሚው ስላላገኙ እንጂ በርካታ የኪነትና የጥበብ ባለሟል ነን ባዮች ብዙ ሊሉን እንደሚችሉ እገምታለሁ። ዓለም የቲያትር መድረክ ናት ነው ያለው? ሼክስፒር፡ እውነት አለው።
መደምደሚያ፦ በኢትዮጵያ የሚገኙ አርቲስቶች አይነት
አሁንም በኔ መነጽር እይታ የኢትዮጵያ አርቲስቶች በሶስት የሚከፈሉ ይመስሉኛል።
የመጀመሪያዎቹ የህሊናቸውን በር ሙሉ ለሙሉ ያልዘጉ ባገኙት አጋጣሚ የህዝብን እውነት በስራቸው አሾልከውም ቢሆን ለማሳየትና የህሊናቸውን ውጥረት ለማስተንፈስ የሚሞክሩ ናቸው፡፡ እነኚህ አርቲስቶች የእንጀራ ነገር ሆኖ እንጂ በስራቸው ደስተኛ አይደሉም። የማይመስል ነገር(የህዝብ እውነት ያልሆነ ስራ) ከመስራት እራሳቸውን ያሸሻሉ። ባጠቃላይ ሃቅ የሚያንቃቸው አይነቶች ናቸው።እነኚህ አርቲስቶች በተለይ ከሶስተኞቹ (አጎብዳጆች) ጋር ፍጹም አይስማሙም። በስራቸውም ብዙ ተጠቃሚ አይደሉም።
ሁለተኞቹ አይነቶች ልኑርበት አይነት ናቸው። ለገበያ ፍጆታ የሚሆን የፍቅር ዲስኩርና የወንጀል ስንክሳር እያመረቱ ከግራውም ከቀኙም ሳይጣሉ መኖር የሚሹ ናቸው። እነኚህ አይነቶቹ ሙያቸው እንደማንኛውም ስራ የእለት ጉርስ ከማሰገኘት ባለፈ የህዝብን እውነት የመግለጽ ልዩ ሃላፊነት ያለበት ሙያ መሆኑን ሊቀበሉ አይሹም። የህሊናቸውን ወቀሳ የሚሞግቱትም በዚህ እምነታቸው ነው። ገንዘብ እሳካገኙ የትኛውንም ስራ አይመርጡም።እነኚህ አይነቶቹ ከአንደኞቹም ከሶስተኞቹም ጋር ሰላም ለመፍጠር ይጥራሉ። ከየትኛውም ጋር እውነተኛ ወዳጅነትም አይኖራቸውም።
ሦሦተኞቹ የሰራዊት ፍቅሬ፤ አይነቶች ባለስልጣናቱን ለማስደሰት ጠብ እርግፍ የሚሉ ናችው። ህሊና አልፈጠረባቸው። (ፈጥሮባቸው ከነበረም ቦታው ለልማት ተፈልጎ ተነስቷል) ብቻ ራሳቸውንም ሙያቸውንም በውዴታ ለባለስልጣናቱ ያስገዙ ናቸው።
ወንዝን ወደ ሰማይ አትንነው በርሃ ላይ ዝናብ ለማዝነብ ቀና ደፋ የሚሉ ለህዝብና ለሃገር አሳቢ ባለስልጣናት እንዳሉን ለማሳየት ሆድ-ወለድ ድራማ የሚደርሱ አጎብዳጆች ናቸው።(የሰራዊት ፍቅሬን ሰማያዊ ፈረስ ልብ ይሏል) እነዚህ አርቲስት ነን ባዮች ፤ በተለይ በተራ ቁጥር አንድ ላይ ከተጠቀሱት ጋር አይስማሙም። ለመንግስት ባላቸው ቀርቤታና አመኔታ ከፍተኛ ጥቅም የሚያጋብሱ ቱጃሮች ናቸው።
በዚህ የመከፋፈያ መስፈርት ያልተጠቃለሉ የእውነተኛ አርቲስት መገለጫ የሆኑ እንዳሉም ሳንዘነጋ ነው። (ታማኝና ሻምበልን መጥቀስ በቂ ይመስለኛል)
በነገራችን ላይ ይህ የግሌ አመለካከት ነው። ሌላውም የራሱ የመከፋፈያ መስፈርት ይኖረው ይሆናል። አሳፋሪ አርቲስቶች እንዳሉ ሁሉ የሚያኮሩ አርቲስቶም አሉ። ነገር ግን የልማታዊውን መንግስት መልካም ገጽታ የሚያጠለሽ እኔን መሰል ጸሃፊ እግሌን እገሌን አከብራለሁ ብሎ ቢጽፍ ለአርቲስቶቹ ጥሩ ስለማይሆን እንጂ ስራቸውን እየዘረዘርኩ ባመስግናቸው ደስ ባለኝ ነበር።ለግዜው ግን አልፌዋለሁ።
በሜሮንና በአስቴር ወቅታዊ ስራዎች ላይ እየተንደረደርኩ የጀመርኩትን የዛሬን ጽሁፌን ልቋጭ እንደገና እየተንደረደርኩ ነው።
ከዚያ በፊት ግን አንድ ነገር ማለት እሻለሁ! የለውጥ አየር እየነፈሰ ነው። በሰላማዊም ይሁን በጸባዊ ትግል ብቻ! በምንም ይሁን በምን መንገድ፤ ይሄ መንግስት በመጨረሻው ሰዓት ላይ እንደሚገኝ እላችኋለሁ። ብዙ አመላካች ነገሮች አሉ....። አመላካች ነገሮቹንና ሌሎችም ትዝብቶቼን ይዤ ወደፊት ልመለስ። ለዛሬው ግን በዚህ ላብቃ።
የነገ ሰው ይበለን....
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
አዜብ ጌታቸው!
azebgeta@gmail.com

Monday, 26 January 2015

ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በኖርዌይ ኦስሎ እንግሊዝ ኢንባሲ ፊት ለፊት በደማቅ ሁኔታ ተካሄደ 


  በኖርዌይ የሚኖሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በህብረት ሁነው ከ14፡00 _15፡00 ስዓት ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉ በደማቅ ሁኔታ አካሄዱ።
የሰልፉ ዋና አላማ የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሃፊ የነበሩትንና የሰባዊ መብት ተቆርቋሪ የሆኑትን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በአረመኔው፣ ሰው በላ፣ ጨቋኙና በአንምባ ገነኑ የወያኔ ፋሺስታዊ ቡድን የአለም አቀፍ የሰባዊ መብትን ህግ በጣሰ መንገድ በሰኔ 2014 ታፍነው እስኳሁንም ድረስ ፍትህ ተነፍገው በእስር ቤት መታሰራቸውን ለመቃወም እንዲሁም የእንግሊዝ መንግስት አርበኛው የነጻነት ታጋዩ አንዳርጋቸው እየተፈጸመበት ያለውን ተፈጥሮአዊና ዲሞክራሲያዊ የመብት ጥሰት ተመልክቶ ከእስር ሊወጣበት የሚችልበትን አፋጣኝ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ ለማሳሰብ ነው።
በተጨማሪም አንዳርጋቸው ከተያዘበት ቀን ጀምሮ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በወያኔ የተፈጸመውን የውንብድና ድርጊት በመቃዎም ለእንግሊዝ መንግሥት በተለያየ መልኩ የአገሩን ዜጋ ህይወት ይታደግ ዘንድ በተደጋጋሚ ለማሳሰብ ቢሞከርም አፋጣኝ እርምጃ አለመወሰዱ ብዙዎችን አስቆጥቷል።
አንዳርጋቸው አገር ወዳድ፣ ሰላም ፈላጊ፣ ነጻነትና ፍትህ ናፋቂ፣ ለህዝብና ለአገር ክብር ተቆርቋሪ፣ ከእራሱ እና ከሚወዳቸው ቤተሰቦቹ ይልቅ ለእናት አገሩ ኢትዮጵያ ጊዜውን፣ እውቀቱንና ህይወቱን የሰዋ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ጀግና መሆኑን በኩራት መስክረዋል። የውጭ ዜጎችም ሳይቀሩ ኢትዮጵያዊ ማንዴላ ብለው ሰይመውታል። ለዲሞክራሲ መከበር ለሚታገል አርበኛ እስርና እንግልት ኮቶ እንደማይገባ በተለይ የእንግሊዝ መንግሥት በትኩረት ሊመክርበት የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን እና በወያኔ ላይ ግፊትና ጫና መፍጠር እንዳለበት ሁሉም ተሰላፊዎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
እንዲሁም ሰልፈኞቹ የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ በታላቅ ድምጽና ስሜት የኖርዌይ ቅዝቃዜና በረዶ ሳይበግራቸው ለኢንባሲው አሰምተዋል። ከአሰሟቸው መፈክሮች መካከል ለአብነት ፣ “Andargachew is a freedom fithter, UK, were is your citizen, Free Andrgachew Tsige, Andargachew is our icon of democracy, where is your action , stop discrimination among citizens, Yes, we are all Andrgachew Tsige, Yes, Andargachew is an Ethiopian Mandela, Brtain don't support terrirost regim in Ethiopia, ” የሚሉት ይገኙበታል::
እንደተለመደው በድርጅቱ የተዘጋጀውን ደብዳቤ በድርጅቱ ተወካዮች በአቶ ይበልጣል ጋሹ እና በአቶ ዮናስ ዮሴፍ አማካኝነት ለእንግሊዝ ኢምባሲ ተወካይ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳዩ ትኩረት የሚሻና ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን በመግለጽ ህይወቱም በእጅጉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳለ በጥብቅ በማሳሰብ ደብዳቤውን በኢምባሲው ተወካይ አማካኝነት እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
በመጨረሻም ግፈኛው የወያኔ ቡድን በለመደው ተራ የሀሰት ወሬ በሚያወራበት ቴሌቪዥኑ ላይ ለትርጉም በሚያስቸግር መልኩ ቆራርጦና በጣጥሶ አንዳርጋቸውን ለማስወራት መሞከሩ የወያኔን ከንቱነት እና እውቀት ዓልባነቱ እንዲሁም ለህዝብና ለአገር የሚሰጠው ንቀት ይበልጥ ለዓለም መጋለጡ ለእኛ ለአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ህብርትና አንድነት ፈጥረን በእልህ፣ በቁጭትና በቁርጠኝነት ከበፊቱ በበለጠ ትግላችንን አጠናክረን እንድንቀጥል ትልቅ በር ከፍቶልናል፤ ለትግልና ለተቃውሞም ይበልጥ አነሳስቶናል። እንደ አርበኞችና ግንቦት ሰባት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችም ውህደት ፈጥረው በሁለገብ ትግል ዘረኛው ወያኔን ለማስወገድ ቆርጠው እንዲነሱ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ዓለሙ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። በተመሳሳይም የወጣቶች ክፍል ተወካይ አቶ ይበልጣል ጋሹ ወጣቶች ለፍትህ፣ ለነጻነትና ዲሞክራሲ ለሚደረገው ትግል አስትዋጾ ማድረግ እንዳለባቸው በአጽንኦት አሳስበዋል።
ወጣት ሁሉን ነገር የመለወጥ ኃይልና አቅም አለው!አምባገነን መንግሥትን ማስወገድ እንችላለን! ወያኔን ከኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ማስወገድ እንችላለን!
ዛሬም ነገም ሁላችንም አንዳርጋቸው ፅጌ ነን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
የወጣቶች ክፍል

Thursday, 22 January 2015

ኢትዮጵያ፡ መገናኛ-ብዙሃን በመጥፋት ላይ ናቸው
(ናይሮቢ ጃንዋሪ 22፣ 2015 ዓ.ም.) – የኢትዮጵያ መንግስት ነጻ መገናኛ ብዙሃን ላይ በሚፈጽመው ስልታዊ ጫና ምክንያት ከግንቦት 2007ቱ ምርጫ አስቀድሞ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ ተስፋ አሰቆራጭ ሁኔታ ተፈጥሯል ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ዛሬ ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ። ባለፈው ዓመት መንግስት የጥቃት ዘመቻ ካካሄደባቸው በኋላ ስድስት የግል የህትመት መገናኛ-ብዙሃን ተዘግተዋል፣ ቢያንስ 22 ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን እና አሳታሚዎች በወንጀል ተከሰዋል እንዲሁም ከ30 በላይ ጋዜጠኞች አፋኝ የሆኑ ህጎችን መሰረት አድርጎ ሊፈጸምባቸው የሚችልን እስር በመፍራት ሃገር ለቀው ተሰደዋል፡፡
“’ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም’፡ የመገናኛ-ብዙሃን የመብት ጥሰት በኢትዮጵያ” በሚል የቀረበው ባለ 76 ገጹ ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት እ.ኤ.አ. ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ነጻ ጋዜጠኝነትን እንዴት እንዳሽመደመደው በዝርዝር አቅርቧል፡፡ እ.ኤ.አ. ከግንቦት 2013 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ወስጥ ከ70 በላይ በስራ ላይ ያሉ እና የተሰደዱ ጋዜጠኞችን ሂዩማን ራይትስ ዎች ቃለ-መጠይቅ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነታቸውን ስለተገበሩ ብቻ 19 ጋዜጠኞች እንዲታሰሩ እ.ኤ.አ. ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከ60 የሚበልጡ ሌሎች ደግሞ ሀገር ለቀው እንዲሰደዱ ያደረገውን የመንግስትን አንድ ወጥነት ያለው የጫና ማሳደር አፈጻጸም ሂደት መረዳት ለመረዳት ችሏል።
“የኢትዮጵያ መንግስት ነጻ መገናኛ-ብዙሃንን ጠቃሚ የመረጃ እና ትንታኔ ምንጭ አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ የስጋት ምንጭ አድርጎ በመቁጠር በሃገሪቱ የሚገኙ ነጻ ድምጾች ላይ ስልታዊ በሆነ መንገድ ጥቃት ይፈጽማል::” ያሉት የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮው “የኢትዮጵያ መገናኛ-ብዙሃን ለግንቦቱ ምርጫ ወሳኝ ሚና መጫወት አለባቸው፤ ነገርግን በርካታ ጋዜጠኞች የሚቀጥለው ጽሁፋቸው እስር ቤት ያስወረውረናል በሚል ስጋት ውስጥ ነው የሚገኙት።’’ ብለዋል።
አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ የህትመት፣ የቴሌቪዥን እና ሬድዬ ስርጭቶች በመንግስት ቁጥጥር ስር ናቸው፤ የቀሩት ጥቂት የግል የህትመት መገናኛ-ብዙሃን የመዘጋት እጣ እንዳይደርስባቸው ከመፍራት የተነሳ በአሳሳቢ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚሰሯቸው ዘገባዎች ብዙውን ጊዜ በራሳቸው ላይ ቅድመ-ምርመራ ያደርጋሉ፡፡
እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም. የተዘጉት ስድስት ነጻ የህትመት መገናኛ-ብዙሃን በመንግስት ባለቤትነት በተያዘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ህትመቶቹ ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው የሚል ውንጀላ ያለበት ዘገባን ጨምሮ ረዘም ላለ ጊዜ የማሸማቀቂያ ዘመቻ ሲካሄድባቸው ቆይቷል፡፡ ማሸማቀቂያው በህትመቶቹ የስራ ባልደረቦች ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ማድረስ፣ በማተሚያ ቤቶች እና አከፋፋዮች ላይ አሉታዊ ጫና መፍጠር፣ የፈቃድ አሰጣጥና እድሳትን ማዘግየት ብሎም በአዘጋጆቹ ላይ የወንጀል ህግ መመስረትን ያካትታል። በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ሃገር ለቀው ተሰደዋል፡፡ ሶስት የህትመት ባለቤቶች የወንጀል ህጉን በመጣስ ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን እያንዳንዳቸው ከሶስት ዓመት በሚበልጥ እስራት እንዲቀጡ በሌሉበት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ለክሱ ማስረጃ ሆነው የቀረቡባቸው የመንግስት ፖሊሲዎችን በመተቸት ያተሟቸው ጽሁፎች ናቸው።
ጥቂት ከፍ ያለ ታዋቂነት ያላቸው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ስቃይ በስፋት የታወቀ ሲሆን በደርዘኖች የሚቆጠሩ በአዲስ አበባ እና በክልሎች የሚገኙ ሌሎች ጋዜጠኞች በደህንነት ባለስልጣናት ስልታዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል።
በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ተመሳሳይ አካሄድ ያለው ነው ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ ትችት ያዘሉ ዘገባዎችን የሚጽፉ ጋዜጠኞች ዛቻ ያለበት የስልክ ጥሪ እና የአጭር ጽሁፍ የስልክ መልዕክት ይደርሳቸዋል፤ እንዲሁም የደህንነት ባለስልጣናት እና የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ወደ ስራና መኖሪያ ቤታቸው በመሄድ ያስፈራሯቸዋል። አንዳንዶቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደዚህ አይነት ማስፈራሪያዎች እንደደረሱባቸው ተናግረዋል፡፡ እንደእዚህ የአይነት ማስፈራሪያዎች ጸጥ ሊያሰኟቸው አሊያም በራሳቸው ላይ ቅደመ-ምርመራ እንዲያካሂዱ ሊሸማቅቋቸው ካልቻሉ አብዛኛውን ጊዜ ማስፈራሪያው የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሊያም እስር ይከተላል፡፡ በአብዛኛው ከሽብር ጋር በተያያዙ ክሶች የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው እና ፍትሃዊ ያልሆነ እና በተራዘመ የፍርድ ሂደት ያለፉ ጋዜጠኞች የወንጀል ጉዳዮች ላይ የፍርድ ቤቶች ገለልተኛነት እመብዛም ነው ወይም ጭራሹንም የለም።
“ተገቢ ባልሆኑ የወንጀል ክሶች እና ሌሎች ማሸማቀቂያ መንገዶች ነጻ ድምጾችን በማፈን ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ጋዜጠኞች ከሚያስሩ ሀገሮች አንዷ እየሆነች ነው፡፡” የሚሉት ሌፍኮው “መንግስት ያለአግባብ የታሰሩ ጋዜጠኞችን ባስቸኳይ መፍታት አለበት እንዲሁም የመገናኛ-ብዙሃን ነጻነትን ለመጠበቅ የህግ ማሻሻያ ማድረግ አለበት፡፡”ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛኞቹ የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከመንግስት ጋር ትስስር ያላቸው ናቸው፣ መንግስት ከሚያራምዳቸው አቋሞች ብዙም አያፈነግጡም፤ እንዲያውም የመንግስት ፖሊሲዎችን ያስተዋውቃሉ፣ የልማት ውጤቶችን ያወድሳሉ፡፡ ከ80 በመቶ የሚበልጠው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው በገጠራማ አካባቢዎች በመሆኑ እና ሬድዮ እስከአሁን ድረስ ዋናው የዜና እና መረጃ ማግኛ ምንጭ ከመሆኑ አንጻር ሬድዮን መቆጣጠር ለፖለቲካው ከፍተኛ አስፈለጊነት አለው። የፖለቲካ ክስተቶችን የሚዘግቡ ጥቂት የግል ሬድዮ ጣቢያዎችም በአካባቢ የመንግስት ባለስልጣናት ስራዎቻቸው የሚታረሙበት እና ለስርጭት የቅድሚያ ፈቃድ የሚያገኙበት አሰራር አለ። ፈቃድ ካገኘው ይዘት የሚያፈነግጡ አሰራጮች ጥቃትና ወከባ ይደርስባቸዋል፣ ይታሰራሉ፣ በበርካታ አጋጣሚዎችም ሃገር ለቀው ለመሰደድ ይገደዳሉ።
መንግስት በዲያስፖራ ባለቤትነት የተያዙ የውጭ የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ስርጭቶች አየር ሞገዶችን በተደጋጋሚ ያፍናል፤ ድረ-ገጾቻቸውንም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ያደርጋል።፡፡ ለእነዚህ ብሮድካስተሮች የሚሰሩ ሰራተኞች ዛቻ እና ማስፈራሪያ ይደርስባቸዋል፤ እንዲሁም የመረጃ ምንጮቻቸው እና በዓለም ዓቀፍ መገናኛ-ብዙሃን ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች ማስፈራሪያ ይደርሳቸዋል። እነዚህን ስርጭቶች የተመለከቱ ወይም ያዳመጡ ሰዎችም ጭምር ለእስር ተዳርገዋል፡፡
መንግስት የጋዜጠኞች ማህበራት ለመመስረት የሚደረግ ጥረትን በማደናቀፍ፣ ለግል መገናኛ-ብዙሃን የሚሰጥ ፈቃድ ወይንም እድሳትን በማዘግየት፣ ባሉት ጥቂት ማተሚያ ቤቶች እና አከፋፋዮች ላይ አሉታዊ ጫና በማሳደር እንዲሁም በመንግስት መገናኛ-ብዙሃን የስራ ቅጥርን ከገዢው ፓርቲ አባልነት ጋር በማያያዝ በርካታ በግልጽ የማይታዩ ግን ደግሞ ውጤታማ የሆኑ አስተዳደራዊ እና ከቁጥጥር ጋር የተያያዙ ገደቦችንም ስራ ላይ ያውላል።
ማህበራዊ ድረገጾችም ከፍተኛ ገደብ ይደረግባቸዋል፤ እንዲሁም በዲያስፖራዎች የሚመሩ በርካታ የኢንተርኔት ጦማሮች እና ድረ-ገጾች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ተደርገዋል። በሚያዚያ ወር ዞን ዘጠኝ በመባል የሚታወቁ እና በሃገሪቱ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በተለይ ለወጣት ኢትዮጵያዊያን ትንታኔ የሚያቀርቡ የኢንተርኔት ጦማሪያን ስብስብ አባላት የሆኑ ስድስት ጦማሪያንን መንግስት አስሯል። በሃገሪቱ የጸረ-ሽብር አዋጅ እና የወንጀል ህግ መሰረትም ክስ ተመስርቶባቸዋል። ከሌሎች ታዋቂ ጋዜጠኞች ጋር በአንድነት እየታየ የሚገኘው ክሳቸው ፍትሃዊ የፍርድ ሂደትን ሊያዛቡ የሚችሉ በርካታ ግድፈቶች ተስተውለውበታል። እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 14 የፍርድ ሂደቱ ለ16ኛ ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶበታል። ተከሳሾቹም ከ260 ቀናት በላይ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን እስር እና ክስ በተለይ ተችት የሚያቀርቡ ጦማሪያን እና የኢንተርኔት ላይ ተሟጋቾችን ጨምሮ በኢትዮጵያ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ የፍርሃት ድባብ እንዲሰፍን አድርጓል።
እየጨመረ የመጣው መገናኛ-ብዙሃን ላይ የሚፈጸም አሉታዊ ጫና በግንቦት ወር በሚካሄደው ምርጫ የሚኖረውን የመገናኛ-ብዙሃን ይዞታ ያለጥርጥር ይጎዳዋል ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዎች፡፡
“ከግንቦቱ ምርጫ አስቀድሞ መንግስት የመገናኛ-ብዙሃን ነጻነትን በተመለከተ ከፍተኛ ማሻሻያ ለማድረግ አሁንም ጊዜ አለው::” ያሉት ሌፍኮው “አፋኝ ህጎችን ለማረም እና የታሰሩ ጋዜጠኞችን ለመፍታት የሚያስፈልገው የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንጂ ረጅም ጊዜ ወይንም ከፍተኛ ሃብት አይደለም፡፡” ብለዋል።
“የኢትዮጵያ መንግስት ነጻ መገናኛ-ብዙሃንን ጠቃሚ የመረጃ እና ትንታኔ ምንጭ አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ የስጋት ምንጭ አድርጎ በመቁጠር በሃገሪቱ የሚገኙ ነጻ ድምጾች ላይ ስልታዊ በሆነ መንገድ ጥቃት ይፈጽማል። የኢትዮጵያ መገናኛ-ብዙሃን ለግንቦቱ ምርጫ ወሳኝ ሚና መጫወት አለባቸው፤ ነገርግን በርካታ ጋዜጠኞች የሚቀጥለው ጽሁፋቸው እስር ቤት ያስወረውረናል በሚል ስጋት ውስጥ ነው የሚገኙት።”
ያሉት የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮው

Wednesday, 21 January 2015

ኢትዮጵያን   እየመሩ ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በሙሉ በጥቂት ቀናት ትምህርት ብቻ  ከአንድ የውጪ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪ እንዲያገኙ መደረጋቸው ተመለከተ።

ሀገሪቱ የምትመራበትን  ፖሊሲ ከመጠምዘዝ ጀምሮ ድርጊቱ በሀገርና በህዝብ ላይ የከፋ ተጽእኖ እንዳለው የተገነዘቡ ኢትዮጰያውያን በዩኒቨርሲቲው ላይ  የተቃውሞ ዘመቻ እያስተባበሩ ነው።
አዲስ አበባ የሚገኘው ኢንተርናሽናል ሊደር ሺፕ ኢንስቲትዩት አማካይነት የሚቀርቡለትን ባለስልጣናት በአጭር ቀናት ኮርስ በማስተርስ ዲግሪ እያንሸበሸ ያለው ፤በእንግሊዝ ሀገር የሚገኘው የግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ ነው። በአይ ኤል አይ ድረገጽ እንደተመለከተው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሁሉም የሀገሪቱ ባለስልጣናት በቀናት ኮርስ  ከአንድ ትምህርት ቤት ማለትም ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ  የማስተርስ ዲግሪ እንዲወስዱ ተደርገዋል።
እነሱም፦አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣ የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አዲሱ ለገሰ፣የቀድሞው የኮሙኒኬሽን ሚኒስትርና የ አሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ አማካሪ በረከት ስምኦን፣የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሀመድ ኡመር፣የቀድሞው የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ጁነዲን ሳዶ፣ የቀድሞው የ አዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ፣የ ኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሙክታር ከድር፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ሸፈራው ተክለማርያም፤ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን፣ የትምርት ሚኒስትር ሽፈራው ሽጉጤ፣ የሲቪል ሰርቪስ ምክትል ሚኒስትር አስቴር ማሞ፣ የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትርና የ አሁኑ የ አዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ፣የሴቶች፣ የህጻናትና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዘነቡ ታደሰ፣የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባ ኤ ካሳ ተክለብርሀን፣የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደሴ ዳልክዬ ዱካሞ፣የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አብርሐም ተከስተመስቀል፣የቀድሞ መከላከያ ሚኒስተርር ሲራጅ ፈርጌሳ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ዳውድ መሀመድ አሊ፣የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ተከስተ ረባ አያና፣በፌዴሬሽን ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሙፈሪያት ካሚል አህመድ እና በመከላከያ ሚኒስትር የምእራብ እዝ አዛዥ ሜጀር ጀነራል  ብርሀኑ ጁላ ጋላቻ ናቸው።
በኢንተርናሽናል ሊደር ሽፕ ኢንስቲትዩት ድረ-ገጽ ከተዘረዘሩት ከነኚህ ባለስልጣናት ባሻገር  የሀገሪቱ ጀነራሎችና የጦር አዛዦች እንዲሆም የየዞኑ የቢሮ ሀላፊዎች በሙሉ  በሶስትና አራት ቀናት ኮርስ ከዚሁ ከግሪንዎች ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪ መያዛቸውን   በአንድ ወቅት በዩኒቨርሲቲው መምህር የነበሩት ዶክተር ታደሰ ብሩ  ይናገራሉ።
የማስተርስ ዲግሪ ከወሰዱት ከነኚህ ሹመኞች መካከል  በጣት የሚቆጠሩ ጥቂቶች በራሳቸው የተማሩ ቢሆንም፤ በርካታዎቹ የ2ለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚገባ ስለማጠናቀቃቸው ትክክለኛ ማረጋገጫ ማቅረብ አይቻልም። ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከትምህርት ሚኒስትሩ ጀምሮ አሉ ለሚባሉ የሐገሪቱ ሹማምንት ሁሉ የማስተርስ ዲግሪ በዚህ መልክ መታደሉ በሀገሪቱ ፖሊሲዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ያለው ተጽ እኖ ከፍተኛ እንደሆነ ዶክተር ታደሰ ያብራራሉ።
የግሪንዊች ዩኒቨርሲቲንም  “ሀገሪቱን እጅ የጠመዘዘ፣ሀገሪቱን እኪሱ ያስገባ ተቋም”ብለውታል ዶክተር ታደሰ። የትምህርት ሚኒስትሩ ዕፈራው ሽጉጤ ከዚሁ ከግሪንዊች ተቋም መመረቃቸው የሚፈጥረን የጥቅም ግጭት  ዶክተር ታደሰ ሲያብራሩም፦ ይህ ድርጊት ለዩኒቨርሲቲውም እፍረት ነው፤ለሀገራችንም ጉዳት ነው ያሉት ዶክተር ታደሰ፤ የዩኒቨርሲቲውን ድርጊት ለመቃወም  ፒቲሺን  ፈርሞ የማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን በማውሳት፤ ኢትዮጰያውያን  በተቃውሞ ዘመቻው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
 ኢሳት ዜና