Tuesday, 9 December 2014

በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት እናወግዛለን !!!
በአብዛኛው በወጣት ወንዶችና ሴቶች የተገነባው ሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነበት የዘጠኝ ፓርቲዎች ኅበረት፣ “ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” የተሰኘ የአንድ ወር መርሀ ግብር አውጥቶ፤ ችግሮችን ተጋፍጦ አብዛኛውን ተግባራዊ አድርጓል። የመርሀ ግብሩ አቢይ አካል የነበረውና በህዳር 27 እና 28 ሊከናወን ታድቆ የነበረው የ24 ሰዓት የአደባባይ ተቃውሞ ግን በአገዛዙ የኃይል እርምጃ ምክንያት በታቀደው መንገድ ሊከናውን አልቻለም። የህወሓት ቅልብ የሆኑት ሲቪል የለበሱ ሰላዮችና የፌደራል ፓሊስ በተቃውሞው ተሳታፊዎች ላይ ኢሰብዓዊ የሆነ ጥቃት ፈጽመዋል።
ከጅምሩ፣ የፓርቲዎቹ ኅበረት የተቃውሞ ማሳወቂያ ደብዳቤውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለማስገባት የገጠመው ችግር የህወሓት አገዛዝ የመንግሥትን መዋቅር ለፓ...ርቲ ሥራ፤ የመንግሥት ተቀጣሪዎችን ደግሞ እንደ ህወሓት አገልጋዮች የሚጠቀምባቸው መሆኑ አንዱ ማሳያ ሆኗል። ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርጉ ማሳወቅ የፈለጉት ፓርቲዎች ህወሓት የዘረጋውን አፋኝ ሥርዓት የሚታገሉ በመሆናቸው ብቻ ደብዳቤዓቸውን የሚቀበል እንኳን አጥተው ተጉላልተዋል። ለሰልፉ ቅስቀሳ ማድረግም በራሱ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ወጣቶች ተንገላተዋል፣ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል። ያም ሆኖ ውጣ ውረዶች ታልፈው ቅዳሜ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ. ም. ደረሰ።
የኅበረቱ አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና ጥሪውን የሰማ ሕዝብ ወደ መስቀል አደባባይ ማምራት ሲጀምር ሲቪል የለበሱ የአገዛዙ ታጣቂዎች እና ፌደራል ፓሊሶች ከሰንደቅ ዓላማዎችና መፈክሮች ባለፈ አንዳች ነገር ያልያዙትን እድሜያቸው ከሃያዎች ያልዘለሉ ውድ የኢትዮጵያ ልጆችን ደብድበዋል፤ ብዙዎቹም አፍነው በአሰቃቂ ሁኔታ እያንገላቱ ወደ እስር ቤቶች ወስደዋል። ወጣቶች ተወልደው ባደጉበት አገር፤ ስሜታቸውን በነፃነት ለመግለጽ በመድፈራቸው ብቻ በጭካኔ ተረግጠዋል፤ ተፈንክተዋል፤ እጅና እግሮቻቸው ተሰብሯል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህ የህወሓትን ፋሺስታዊ እርምጃ አጥብቆ ይቃወማል። ግንቦት 7፣ ህወሓት ከስልጣን እስካልተወገደ ድረስ እንዲህ ዓይነቱን ፋሺስታዊ ተግባር መፈፀሙን የማይተው እኩይ ኃይል እንደሆነ ያውቃል፤ በዚህም ምክንያት የትግላችን ግብ ህወሓትን ማስወገድና በምትኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ ያገኘ መንግሥት መመሥረት መሆን ይኖርበታል ብሎ ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል።
ግንቦት 7፣ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. “መብቶቻችንን በህወሓት ዘረኛ አምባገነኖች አናስነጥቅም” በማለት አደባባይ የወጡ ወጣቶችን ጽናት ያደንቃል። ህወሓት የሚለውን ሳይሆን የይስሙላ ህጉ የፈቀደላቸውን ለማድረግ በመድፈራቸው በህወሓት የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የሚደረገውን ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት አራምደውታል።
እያንዳንዱ የፓለቲካ ድርጅት ከዚህ ኩነት የሚወስዳቸው ተጨማሪ ትምህርቶች ቢኖሩም የሚከተሉትን ነጥቦች ብዙዎችን ያስማማሉ ብለን እናምናለን።
1. ህወሓት በምንም ዓይነት ቢሆን የያዘውን ስልጣን ለሕዝብ ፈቃድ ማስገዛት አይፈልግም፤
2. ህወሓት አገራችን ወደ ትርምስ እየገፋት እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፤
3. ስልጣኑን የሚያሳጣው ከመሰለው እና አቅሙ እስካለው ድረስ ዘግናኝ እርምጃዎችን ከመውሰድ አይመለስም፤
ከህወሓት አገዛዝ መገላገል የሚቻለው ተገዶ ሲወገድ ብቻ ነው። ህወሓት እንዲወገድ ደግሞ የመጨቆኛ አቅሙ መዳከም ይኖርበታል። ህወሓትን የማስወገጃ አማራጭ መንገዶች ብዙ ሲሆኑ ተቀናጅተው ቢሠሩ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ ብለን እናምናለን፤ “ሁለገብ ትግል” የምንለው የትግል ስልት ጭብጥ ይህ ነው። “እምቢ ለነፃነቴ” ብሎ የተነሳ ሕዝብ ህወሓትን ምን ያህል እንደሚያስደነግጥ በተደጋጋሚ ታይቷል። ህዳር 27ን መንደርደሪያ አድርገን በመውሰድ ከዚህ በተሻለ ለተደራጀ ሕዝባዊ እምቢተኝነትና አመጽ ራሳችን እናዘጋጅ።
በዚህ አጋጣሚ ግንቦት 7፣ ለመከላከያ ሠራዊት እና ፓሊስ አባላት ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ማድረግ ይሻል። የመከላከያ ሠራዊት እና ፓሊስ አባላት እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ በህወሓት ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ የተበደላችሁ መሆኑን እናውቃለን። የህወሓት ሹማምንት ከሆኑ አዛዦቻችሁ መላቀቅና ራሳችሁን ነፃ የማውጣት ኃላፊነት የወደቀው በእናንተው በራሳችሁ ላይ ነው። ሠራዊቱ ራሱን በራሱ ነፃ ማውጣት ይኖርበታል። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ህወሓት መወገዱ የማይቀር በመሆኑ ሠራዊቱ ራሱን ነፃ አውጥቶ ከሕዝብ ጋር ካልወገደ እጣ ፈንታው የተሸነፈ ሠራዊት መሆን ነው። ከዚህ በላይ የሠራዊቱ አባል እየደበደበ ያለው የራሱን ልጅ፣ ወንድሙን ወይም እህቱን እንደሆነ ይወቅ። ይህ ወሳኝ ጊዜ ነው እያንዳንዱ የሠራዊቱ አባል በግል ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ሊሰማው ይገባል።
በሁሉም ዓይነት የትግል ዘርፎች የኢትዮጵያ ወጣቶች በስፋት እየተቀላቀሉ መሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው። ጊዜው የለውጥ ነው። የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተደጋግፈው እንዲሄዱ መደረግ ያለበት ወቅት ላይ ነን። በህዳር 27 ቀን በህወሓት ቅልብ ሰላዮችና የፌደራል ፓሊሶች አማካይነት የደረሰው ጉዳትና የፈሰሰው ደም ለፍትህና ለነፃነት የተከፈለ ዋጋ ነው። ህመማችሁ ህመማችን፤ ትግላችሁ ትግላችን ነው። የተለያዩ መንገዶች ወደ ነፃነት አደባባይ እያመሩ ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

Monday, 8 December 2014

መሪዎች ቢታሰሩም ትግሉ እንደማይቆም የ 9 ፓርቲዎች ትብብር አመራሮች አስታወቁ

-የምርጫ ስርዓት ለውጥ እንዲደረግ ለመጠየቅ ህዳር 27 ቀን የአዳር ተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ወደ አደባባይ በወጡት 9 የተቃዋሚ ድርጅት አመራሮች ላይ የፌደራል ፖሊስ አባላት ድብደባ በመፈጸም ወደ እስር ቤት ቢወስዱዋቸውም፣ የትብብሩ አመራሮች ግን ትግሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ኢትዮጵያውያን ለትግሉ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ሶስተኛ እየተባለ በሚጠራው እስር ቤት ውስጥ ታስረው የሚገኙት የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣  አቶ ኤርጫፎ ኤርዳሎ፣ አለሳ መንገሻና ሌሎችም አመራሮች አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፣ በጨርቆስ ታስረው የሚገኙት እነ አቶ ግርማ በቀለ ደግሞ የ7 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።
አመራሮቹ ሀግመንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድና የተከለከለ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ወንጀል መከሰሳቸውን ታውቋል።
በፍርድ ቤት አካባቢ ሆነው ጉዳዩን ከተከታተሉት መካከል ናትናኤል ያለምዘውድ ለኢሳት ሲናገር፣ አብዛኞቹ አመራሮች ሲሄዱ ያነክሱ እንደነበር ገልጾ፣ ኢ/ር ይልቃል እጁ አካባቢ መመታቱን፣ ብርሃኑ ተክለያሬድ ደግሞ እጅና እግሩ አካባቢ በጨርቅ ተጠቅሎ ማየቱን ገልጿል። ሴት እስረኞችም ሲጓዙ ያነክሱ እንደነበር በተለይ አንደኛዋ ኩላሊቷ አካባቢ መመታቱዋን እንደገለጸችለት ተናግሯል ሴት እስረኞችን ለመጠየቅ በሄደበት ወቅት ለአጭር ደቂቃዎች ራቅ ብሎ ለማናገር መቻሉን የገለጸው ዮሴፍ ተሻገር በበኩሉ፣ ሴቶች በጠንካራ መንፈስ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
ኮተቤ አካባቢ ታስረው ስለሚገኙት የድርጅት መሪዎችና አባላት ጉዳይ በስፍራው በመገኘት ለመታዘብ የቻለው አቶ እምላሉ ፍሰሃ እንደገለጸው ደግሞ ምንም እንኳ እስረኞቹ መጸዳጃ ቤት አካባቢ በመታሰራቸው እንዲሰቃዩ ቢደርግም አሁንም በጠንካራ መንፈስ ላይ መሆናቸውን ገልጿል።
መንግስት የወሰደው እርምጃ በትብብሩ የወደፊት የትግል አካሄድ ላይ ተጽአኖ ይኖረው እንደሆን የተጠየቁት የመኢዴፓ ሊቀመንበርና የትብብሩ ገንዘብ ያዥ አቶ ኑሪ ሙዲሰር ሲመልሱ ” መንግስት እስረኞች ይፈቱ አይፈቱ ወደ ሚል አታካራ እንድንገባ ቢፈልግም፣ እኛ ግን ትግሉን ወደ ፊት ከመግፋት ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም” ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለትግሉ አስፈላጊውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አቶ ኑሪ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ አንድነት ፓርቲ በ9 ፓርቲዎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ አውግዟል። ፓርቲው ባወጣው መግለጫ  ” የዘጠኙ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን ሰላማዊ ሰልፍ የማድርግ መብት ከመጠቀም ውጪ ያጠፉት ምንም ዓይነት ነገር ስለሌለ በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል።” ብሎአል።  ፓርቲው ” የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ህገወጥና አረመኔያዊ ድርጊት በዝምታ ሊያልፈው አይገባም፤ ኢህአዴግን በቃህ ሊለው ይግባል።” በማለት በመግለጫው አስታውሷል።

እነ ግርማ በቀለና ጌታነህ ባልቻ መስቀል አደባባይ ላይ ንብረት አውድመዋል ተብለው ተከሰሱ

እነ ግርማ በቀለና ጌታነህ ባልቻ መስቀል አደባባይ ላይ ንብረት አውድመዋል ተብለው ተከሰሱ
ለአዳር ሰላማዊ ሰልፉ መስቀል አደባባይ ተይዘው ጨርቆስ ፖፖላሬ ታስረው የሚገኙት የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ፀኃፊ አቶ ግርማ በቀለ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የጥናትና እስትራቴጅ ክፍል ኃላፊ ጌታነህ ባልቻን ጨምሮ 27 ያህል የትብብሩ አመራሮች፣ አባላትና የሰልፉ ተሳታፊዎች ዛሬ ህዳር 29/2007 ዓ.ም ጨርቆስ አካባቢ የሚገኝ ፍርድ ቤት ቀርበው ‹‹መስቀል አደባባይ ላይ ንብረት አውድመዋል፡፡›› በሚል ተከሰዋል፡፡
ፖሊስ ‹‹ታሳሪዎቹ መስቀል አደባባይ ላይ ንብረት አውድመዋል፣ የጠፉ ንብረቶችና ያልተያዙ ግብረአበሮቻቻው ስላሉ ለምርመራ 14 ቀን ይሰጠኝ›› ሲል ጠይቋል፡፡ ታሳሪዎቹ በበኩላቸው ‹‹እኛ መስቀል አደባባይ ላይ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳንጀምር ነው የታሰርነው፣ ምንም ...ያወደምነውም ሆነ የወሰድነው ንብረት የለም፡፡›› ሲሉ የፖሊስን ክስ አጣጥለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በህጋዊ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በሚዘጋጁበት ወቅት መያዛቸውን በመግለጽ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ ሆኖም ዳኛው የ7 ቀን ቀጠሮ አስተላልፈውባቸዋል፡፡
በተመሳሳይ በዛሬው ዕለት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው የ14 ቀን ቀነ ቀጠሮ የተሰጠባቸውና በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙት ታሳሪዎች በደረሰባቸው ድብደባ ምክንያት ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡ ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱት መካከል ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት፣ እየሩስ ተስፋው፣ ጋዜጠናኛ በላይ፣ አቤል ኤፍሬም፣ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ስሟ ያልተጠቀሰች አንዲት ሴትና ሌሎች በርካታ ወንዶች እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ ሶስተኛ ከሚገኙት ታሳሪዎች መካከል ከሴቶቹ ንግስት ወንዲፍራውና ምኞቴ መኮንን ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው እና አብዛኛዎቹ ወንዶች ለየብቻቸው ጨለማና ቀዝቃዛ ቤት ውስጥ እንደታሰሩ ተገልጾአል፡፡

70 ኢትዮጵያውያን ቀይ ባህር ላይ ሰጥመው መሞታቸውን የየመን ባለስልጣናት ገልጸዋል

ስደትን የህይወታቸው የመጨረሻ አማራጭ በማድረግ በጅቡቲ በኩል አድርገው ወደ የመን ለመግባት የሞከሩ 70 ኢትዮጵያውያን ቀይ ባህር ላይ ሰጥመው መሞታቸውን የየመን ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ታይዝ በምትባለዋ ግዛት የሚገኙ ባለስልጣናት ለአሶሴትድ ፕሬስ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያውያኑን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረችው ጀልባ ባጋጠማት ከባድ አውሎ ንፋስና ማእበል አል ማክታ እየተባለ ከሚጠራው ወደብ ራቅ ብሎ ለመስመጥ ተገዳለች። ባለስልጣናቱ እንዳሉት ጀልባዋ 70 ኢትዮጵያውያንን ጭና የነበረ ሲሆን በደጋው ሁሉም ኢትዮጵያውያን አልቀዋል።
የመን የሚገኘው ጋዜጠኛ ግሩም ተክለሃይማኖት በበኩሉ በጀልባዋ ላይ የነበሩት 81 ሰዎች ሲሆኑ፣ 71 ኢትዮጵያውያንና 9 ሶማሊያዎች አልቀዋል። አይ ኦ ኤም የተባለው የስደተኞች ድርጅት አስከሬን ለመሰብሰብ ሙከራ ቢደረግም እስካሁን ምን ያክል አስከሬን እንደተሰበሰበ ለማወቅ አለመቻሉን ገልጿል....