Friday, 30 May 2014

ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በኑር መስኪድ ደማቅ ተቃውሞ አደረጉ







የሙስሊም የድምጻችን ይሰማ የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት በፍትህ እጦት በእስር ቤት መሰቃየት መቀጠላቸውን በመቃወም በአዲስ አበባ በኑር መስጊድ በተደረገው ተቃውሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ መገኘቱን ዘጋቢያችን ገልጻለች።
ድምጻችን ይሰማ ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ የተቃውሞው ዋና አላማ የሙስሊሙን ህዝብ ጥያቄ አንግበው በመያዛቸው በእስር እየተሰቃዩ ለሚገኙት መሪዎች ድጋፍ ለመግለጽ ነው መሆኑን ጠቅሷል።
በዘገየ ፍትህና በችሎት ድራማ እየተንከራተቱ የሚገኙት መሪዎች ሲታገሉለት እና ለእስር የተዳረጉበት አላማ የሙስሊም ህዝብ መሰረታዊ የመብት ጥያቄ አካል መሆኑን የገለጸው ድምጻችን ይሰማ፣ የእነሱ መስዋትነት ለህዝቡ የሰጡትን ቦታ፣ ለሃይማኖታቸው ያላቸውን ቀናኢነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው ብሎአል።
ሙስሊም ኢትዮጵያውያኑ ” ኮሚቴው የህዝብ ነው፤ እኛም ኮሚቴው ነን፣ ፍትህ ለወኪሎቻችን ” የሚሉ መፈክሮች ከፍ አድርገው በመያዝ እንዲሁም እጆቻቸውን አጣምረው በመቆም፣ የመሪዎቻቸውን ስቃይ ከመጋራት አልፈው ከጎናቸው መቆማቸውን አመልክተዋል።
የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት የፍርድ ሂደት እንደቀጠለ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ መንግስት አባላቱን በሽብረተኝነት ለመክሰስ የሚያስችለው ይህ ነው የተባለ ማስረጃ ሊያገኝ አለመቻሉን የፍርድ ሂደቱን የሚከታተሉ ሰዎች ይገልጻሉ።
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የሙስሊሞችን የመብት ጥያቄ ለማዳከም መቻላቸውን አስመልክቶ በአንድ ወቅት መግለጫ የሰጡ ቢሆንም፣ ድምጻችን ይሰማ አሁንም ጠንካራ ደጋፊዎች እንዳሉት የሚያሳይ ተቃውሞ እየተካሄደ ነው።
ተቃውሞው ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ አንዳንድ የክልል ከተሞችም መካሄዱን ለማወቅ ተችሎአል።



Tuesday, 13 May 2014

ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ የሃይለመድህን አበራን ጉዳይ ለመከታተል ወደ ጄኔቫ አመራ
May 13, 2014
13 may 2014 (EMF ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራን ጉዳይ ለመከታተል ኢትዮጵያዊው የህግ ባለሞያ ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ ባለፈው ሳምንት ወደ ጄኔቭ-ስዊዘርላንድ ተጉዟል።
Ethiopian lawyer Shakespear Feyissa in Switzerland
ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ ጄኔቭ-ስዊዘርላንድ
ሼክስፒር ፈይሳ የረዳት ፓይለቱን ጉዳይ ከሚኖርበት ከሲያትል ከተማ በቅርብ ሲከታተል ቆይቶ ነው ወደ ጄኔቭ ያመራው። ጄኔቭ እንደደረሰም የሃይለመድህን አበራን ጠበቃና ጉዳዩን ከሚከታተሉ አካላት ጋር በስፋት ተወያይቷል። በተለይ ከረዳት ፓይለቱ ጠበቃ ጋር ረጅም ሰዓታት በመውሰድ በበርካታ የህግና የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ በጥልቅ ተነጋግሯል።
ረዳት ፓይለቱ ሙሉ በሙሉ ጤነኛ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
ኢትዮጵያዊ የህግና እንዳስፈለጊነቱ የህክምና ባለሞያዎች ጋር እንዲገናኝም ዶ/ር ሼክስፒር ምክር ሰጥቷል።
የረዳት ፓይለቱ ጠበቃ የስዊስ መንግስት ሃይለመድህን አበራን ለኢትዮጵያ አሳልፎ እንደማይሰጥና ግዚያዊ የስደት ፈቃድ እንዲሰጠው ውሳኔ መተላለፉን ያረጋገጠ ሲሆን – ጉዳዩ በቅርብ ጊዜ በሚሰየመው ግልጽ ችሎት እልባት እንደሚያገኝ አመላክቷል።
የሃይለመድህን አበራን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ በአቶ አስመላሽ ወልደ-ስላሴ የተመራ ከፍተኛ የኢህአዴግ ቡድን ጄኔቭ፣ ከርሞ ጥያቄው በስዊዘርላንድ መንግስት ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።
ቡድኑ የስዊስ ፌዴሬሽን የህግ አካላትን ለማሳመን ካቀረበው ምክንያት ዋነኛው፣ ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ የአእምሮ በሽተኛ መሆኑን እና ይህንንም የራሱ ቤተሰብ አባላት እንዳረጋገጡላቸው ገልጸዋል። የስዊዝ መንግስት ግን ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል። ለዚህም የሰጠው ዋነኛ ምክንያት፤ የሞት ፍርድን ተግባራዊ ለሚያደርግ መንግስት ማንንም አሳልፌ አልሰጥም የሚል ሲሆን ይህ ባይሆንም፣ በስዊዘርላንድ እና በኢትዮጵያ መሃል ተጠርጣሪ እስረኛን የማስመለስ ውል የለም ብለዋል።
ረዳት ፓይለቱ ለግዜው ሰው ማግኘት እንደማይፈልግ የተነገረ ሲሆን: ወንድሙ ዶ/ር እንዳላማው አበራ እና በጀርመን የምትኖር እህቱ ሃይማኖት አበራ ጄኔቭ ድረስ በመሄድ ሃይለመድህን አበራን ከሚገኝበት እስር ቤት ጎብኝተውታል።
ወጣት ሃይለመድህን አበራ ባለፈው የካቲት 10፣ 2006 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን ቦይንግ 767 አግቶ ጄኔቭ ስዊዘርላንድ ላይ በማሳረፍ እዚያው የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቁ ይታወሳል። የአለም ዜና ርዕስ ሁሉ ትኩረት ስቦ የነበረው ይህ ልዩ ክስተት የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት ሁኔታና የአስተዳደር በደል አደባባይ በማውጣቱ የገዢው ፓርቲ አባላትን እጅግ እንዳበሳጨ ይነገራል።
አንዳንድ መገናኘ ብዙሃን እንደገለጹት የአጎቱ ድንገተኛ ህልፈት ርዳት ፓይለቱን አስቆጥቶት ነበር። የሃይለመድህን አበራ አጎት፤ ዶ/ር እምሩ ሥዩም ህይወት በድንገት ማለፍ ለብዙዎች ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። ዶ/ር እምሩ ሥዩም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነበሩ።
በአለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቱ ፓይለት ሃይለመድህን አበራን መደገፋቸውን እንደቀጠሉ ሲሆን በረዳት ፓይለቱ ስም የተከፈቱ ድረ-ገጾች እና የፌስቡክ መድረኮች ላይ አሁንም ሰፊ ዘመቻ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ በረዳቱ ጉዳይ ላይ ማንኛውንም ትብብር ለማድረግ ቃል የገባ ሲሆን የስዊስ ጠበቆችም በዚህ ከክፍያ ነጸ የሆነ ትብብሩ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

Friday, 9 May 2014

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞና ጸሃፊዎች መታሰር እንዳሳሰበው ገለጸ
በካተሪና አሽተን የሚመራው የአውሮፓ ህብረት የውጭ ግንኙነት ክፍል በጋዜጠኞች ፣ ጸሃፊዎችና ፖለቲከኞች ላይ እየተካሄደ ያለው እስር እንዳሳሰበው ገልጿል። የአውሮፓ ህብረት ሁሉንም ወገኖች ያቀፈ ውይይት እንዲደረግ እና የተለያዩ ድምጾች የሚሰሙበት መድረክ እንዲፈጠር ጠይቋል። ህብረቱ የጋዜጠኞችና ጸሃፊዎች መታሰር እንዳሳሰበው ከመግለጽ በተጨማሪ ጉዳያቸው በነጻ ፍርድ ቤት እንዲታይ፣ ተጠርጣሪዎቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠይቋል። ተጠርጣሪዎቹ በማእከላዊ እስር ቤት ከሰው እንዳይገናኙ ተደርጎ መታሰራቸውን የገለጸው ህብረቱ ፣ እስረኞቹ ስላሉበት ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጠውም ጠይቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በጄኔቫ ስዊዘርላንድ በመካሄድ ላይ ባለው የሰብአዊ መ...ብት አያያዝ ጉዳይ ላይ በርካታ አገሮች የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብት አያያዙን እንዲያሻሽል የሚጠይቁ አስተያየቶችን አቅርበዋል። የመከላከያ ሃይሎች በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የወሰዱት እርምጃ እንዲጣራ ኮስታሪካ፣ ፊንላንድ እና ሞንቴኔግሮ ሲጠይቁ፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂየም፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ሜክሲኮ፣ ናይጀሪያ፣ ስዊድን፣ ዩናይትድ ኪንግደምና ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ በህገመንግስቱ ያሰፈረችውን ሃሳብን በነጻነት መግለጽ፣ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብቶችን እንድታከብር ጠይቀዋል።
አውስትራሊያ፣ ኦስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፈረንሳይ፣ ሜክሲኮ ኔዘርላንድስ፣ ኖርዌይ፣ ስሎቫክ፣ ስሎቫኒያ፣ ስዊድን እና ስዊዘርላንድ ሽብረትኝነትን እንደገና እንደሚለከተው፣ የጋዜጠኝነት ስራ ከሽብረተኝነት ጋር እንዳያይዝ፣ ሲጠይቁ፣ አሜሪካ በበኩለዋ የሽብረተኝነት ህጉ ለፖለቲካ ፍጆታ እየዋለ መሆኑን ተቃውማለች። የጄክ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ያሰረቻቸውን ጋዜጠኞች በሙሉ በአስቸኳይ እንድትፈታ ጠይቋል። ኢስቶኒያ ፣ አየር ላንድና ደቡብ ኮሪያ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ላይ የምታደርገውን ስለላ እንድታቆም ጠይቀዋል። ኦስትሪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክና ፈረንሳይ ኢትዮጵያ የፕሬስ ህጓን እንድታሻሽልና አለማቀፍ መስፈርት ያሟላ እንዲሆን ጠይቀዋል። አፍሪካዊቷ አገር ቦትሰዋና በበኩሉዋ በኢትዮጵያ ዳኞች ላይ የሚደርሰው ማስፈራራት፣ ወከባና ከስራ ማባረር እንዳሳሰባት ተናግራለች። ስዊዘርላንድም የፍትህ ስርአቱ እንዲስተካከል ጥያቄ አቅርባለች። አርጀንቲና፣ ፈረንሳይ፣ ፓራጉዋይና ቱኒዚያ ኢትዮጵያ ስለሚታፈኑ ሰዎች የሚደነግገውን ህግ እንድትፈርም መክረዋል።
በርካታ አገሮች በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳሳሰባቸው የገለጹ ሲሆን፣ የቼክ ሩፐብሊክ አቋም ያልተጠበቀ መሆን ጉዳዩን አስገራሚ አድርጎታል። በሌላ ዜና ደግሞ ስቱዲዮ ከመግባታችን ጥቂት ቀደም ብሎ ዞን ዘጠኝ እየተባለ በሚጠራው የፌስ ቡክ ስም የሚጽፉ ወጣቶች ከታሰሩ ከ10 ቀናት በሁዋላ ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል። ፍርድ ቤት የቀረቡት 3 ጋዜጠኞችና 3 ጸሃፊዎች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሎአል።

Tuesday, 6 May 2014

ሂውማን ራይትስ ወች በተማሪዎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ አወገዘ

   ታዋቂው አለማፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚወሰዱት ሃይል የተቀላቀለበት እርምጃ በአስቸኳይ ሊያቆሙ ይገባል ብሎአል።
የመንግስት ባለስልጣናት በእስር ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን መፍታት እንደሚገባቸው ፣ ድርጊቱን የፈጸሙት የጸጥታ ሃይሎችና ባለስልጣናት አስፈላጊው ምርምራ እንዲካሄድባቸው የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ጠይቋል።
የድርጅቱ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሌስሊ ሌፍኮ  የአዲስ አበባን መስፋፋት ተከትሎ በከተማዋ ዙሪያ የሚኖሩ አርሶአደሮች እጣ ፋንታ አሳስቧቸው ተቃውሞ የወጡትን ንጹሃን ዜጎችን ከማጥቃት ይልቅ ፣ መንግስት ከተማሪዎች ጋር ቁጭ ብሎ በመነጋገር መፍትሄ መፈልግ ነበረበት ብለዋል።
ተማበአምቦ፣ ነቀምት፣ ጅማ እና ሌሎችም ከተሞች ተቃውሞ ማድረጋቸውን የገለጸው ሂውማን ራይትስ ወች፣ የጸጥታ ሃይሎች በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ጥይቶችን በመተኮስ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎችን ገድለዋል። መንግስት በአምቦ 8 ሰዎች እንደተገደሉ ቢናገርም፣ የአይን ምስክሮች ግን ቁጥሩ ከዚህ በላይ እንደሚሆን መግለጻቸውን ድርጅቱ  አክሎ ገልጿል።  የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃውን የወሰድኩት ዘረፋ እና ንብረት ማውደም ስለነበረ ነው የሚል ምክንያት መስጠቱንም ድርጀቱ ገልጿል።
መንግስት የነጻውን ፕሬስ እና የሰብአዊ መብት ድርጅቶችን በማዳካሙ በኦሮምያ የደረሰውን ጉዳት በትክክለኛ ለማጣራት አለመቻሉን ፣ ወደ አካባቢው የተጓዙ የውጭ አገር ጋዜጠኞችም በጸጥታ ሃይሎች እንዲመለሱ መደረጉን ድርጀቱ ገልጿል።
ኢትዮጵያ ጋዜጠኖች ከሚታፈኑባቸው አገራት መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኑዋን ሂውማን ራይትስ ወች አስታውሷል።
 መንግስት ሚዲያውንና የሰብአዊ መብት ድርጅቶችን ቢያፍንም ከተጠያቂነት ያመልጣል ማለት አለመሆኑን ምክትል ዳይሬክተሯ ሌስሌይ ሌፍኮው ገልጸዋል።